Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​እንቅፋቶች የበዙበት የደብረ ብርሃን አዋሽ አርባ የመንገድ ፕሮጀክትና የቱርኩ ኮንትራክተር ስንብት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በትላልቅ የመንገድ ኮንስትራክሽን ግንባታ ሥራ ላይ ከተሰማሩ የውጭ ኮንትራክተሮች ውስጥ የቱርክ ኩባንያዎች ይገኙባቸዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ  እስካሁን ድረስ ከሁለት የቱርክ ኮንትራክተሮች ጋር የመንገድ ግንባታ ውል ተፈርሟል፡፡ ከሁለቱ የቱርክ ኮንትራክተሮች መካከል አንዱ የሆነውና ረዥም መጠሪያ ስም ያለው አታዩል አስፓልት ኮንትራክቲንግ ኮንስትራክሽን ሊኪዊድ ኢነርጂ ኢንዱስትሪ ትሬድ ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ሥራ ለመሳተፍ ዕድል ያገኘው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲንቀሳቀስ ነበር የተባለው ይህ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የቻለው ደግሞ ከአንኮበር አዋሽ አርባ ያለውን መንገድ ለመገንባት በወጣ ዓለም አቀፍ ጨረታ ለመሳተፍ ነበር፡፡ በወቅቱ ኩባንያው አብረውት ከተወዳደሩ ዘጠኝ ከሚሆኑ ኮንትራክተሮች አነስተኛ ዋጋ በማቅረብ አሸናፊ መሆን ችሎ ነበር፡፡

በአማራ ክልል ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ደብረ ብርሃን ተነስቶ አዋሽ አርባ ድረስ ከሚዘልቀውና በሦስት ተከፋፍሎ ከሚሠራው ፕሮጀክት መካከል አንዱ የሆነውን ከአንኮበር እስከ አዋሽ አርባ ድረስ የሚዘልቀውን 55 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመሥራት አታዩል 595 ሚሊዮን ብር በማቅረብ አሸናፊ ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህ ጨረታ ከፍተኛውን የጨረታ ዋጋ የሰጠው ሌላኛው የቱርክ ኩባንያ አታዩል ከሰጠው በእጥፍ ብልጫ እንደነበረው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ኩባንያ ሰጥቶት ነበር የተባለው 1.27 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከእነዚህ ሁለት ኩባንያዎች ሌላ ቪል የተባለው የህንድ ኩባንያ 598.3 ሚሊዮን ብር፣ ሐዋክ ኢንተርናሽናል ፋይናንስና ኮንስትራክሽን የተባለው የየመን ኮንትራክተር ደግሞ 639 ሚሊዮን ብር ሰጥተው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከአምስት በላይ በሆኑ የመንገድ ግንባታዎች ላይ በመሳተፍ የሚታወቀው የቻይናው ቻይና ሬልዌይ ቁጥር (ሦስት) ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ኩባንያ ደግሞ 685.3 ሚሊዮን ብር ዋጋ በመስጠት ጨረታውን ሳያሸንፍ ቀርቷል፡፡

የህንዱ ሲምኖሌክስ ኢንፍራስትራክቸር ሊትድ 710.9 ሚሊዮን ብር፣ የስፔኑ አልስሜክስ ኤያቴቪ 731.3 ሚሊዮን ብር፣ ሲው ኢንፍራስትራክቸራል የተባለው የህንዱ ተቋራጭ ደግሞ 774.6 ሚሊዮን ብር፣ የስዊድኑ ኤከቢአይ ኢንተርናሽናል ሆልደር ኤጂ 905.4 ሚለዮን ብርና የዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ አል አሰብ ጄኔራል ትራንስፖትና ኮንሰልቲንግ 766.9 ሚሊዮን ብር ዋጋ በመስጥታቸው፣ አታዩል ይህንን ጨረታ በቀላሉ እንዲያሸንፍ አድርጎታል፡፡

የአታዩል ውጤት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ቦርድ ከፀደ በኋላ እንኳን ደስ ያለህ ተብሎ የመንገዱን ግንባታ ለመጀመር የሚያስችለውን የኮንትራት ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ፣ በጥቂት ወራት ልዩነት የመንገድ ግንባታ ሥራውን ይጀምራል፡፡ ይሁን እንጂ ግንባታው መጀመሩ ከተነገረ በኋላ መንገዱን በባለቤትነት የሚያሠራው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የቱርኩን ኮንትራክተር የኢትዮጵያ ቆይታ የሚያሳጥር ደብዳቤ ይደርሰዋል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚገልጹት የባለሥልጣኑ ቀጭን ትዕዛዝ ምክንያታዊ ነበር፡፡ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች ለሪፖርተር የሰጡት አስተያየትም ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ ከኮንትራክተሩ ጋር የነበረው የሥራ ውል የተቋረጠው በሥራው ላይ የታየበት የሥራ አፈጻጸም ደካማ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ በውለታው መሠረት መንገዱን እየገነባ አለመሆኑን አረጋግጫለሁ ያለው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ለውጥ ባለመሳየቱ የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ገልጿል፡፡

የኮንትራት ውሉ መቋረጥም የግንባታ ሥራው እንዲስተጓጎል አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአንኮበር አዋሽ አርባ መንገድ ሥራ ከጅምሩ እንዲቋረጥም አስገድዷል፡፡ እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ገለጻ፣ ኮንትራክተሩ ሥራውን እስከተነጠቀ ድረስ የሠራው ሥራ አምስት በመቶ እንኳን የማይሞላ ነው፡፡ ይጠበቅበት የነበረው ግን ከዚህ በላይ ነበር፡፡  ከሁለት ዓመት በፊት የኮንትራት ውሉ ሲፈረም በሁለት ዓመት ተኩል ያልቃል ተብሎ የተባለው ሥራ፣ በጅምር ቀርቶ ሥራው ለሌላ ኮንትራክተር ሳይሰጥም ሁለት ዓመታት ሊቆጠሩ ችለዋል፡፡

የቱርኩ ኩባንያ ውል ከተቋረጠ በኋላ ሥራውን በሌላ ኮንትራክተር ለማሠራት ለምን ይህንን ያህል ጊዜ ፈጀ? የሚል ጥያቄ ማስነቱም አልቀረም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ግን ሥራውን ለሌላ ኮንትራክተር ለመስጠት ቀድሞ መከናወን የሚገባቸው ሥራዎች ስለነበሩ ነው ይላሉ፡፡ መንገዱ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር ጭምር የሚሠራ በመሆኑ ኮንትራክተሩ ሥራውን መሥራት የማያስችል ስለመሆኑ ማረጋገጥና የእነሱንም ይሁንታ መጠበቅ ግድ ማለቱ አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም የጨረታ ዝግጅቱም የራሱ የሆነ ጊዜ ስለሚጠይቅ በድጋሚ ለሌላ ኮንትራክተር የመስጠቱ ሒደት ሊዘገይ ችሏል ተብሏል፡፡

የባለሥልጣኑ ዕርምጃ ሲወሰድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የመንገድ ግንባታው ሥራ መስተጓጎሉ እንደማይቀር ታሳቢ መደረጉንም ኃላፊዎቹ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑ ወደዚህ ዕርምጃ ከመግባቱ በፊት ብዙ ጥረቶችን ማድረጉንም ያስረዳሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚጓተቱ ሥራዎች ላይ  ትችት የሚቀርብ መሆኑን የገለጹት የባለሥልጣኑ ኃላፊ፣ አንድን የመንገድ ፕሮጀክት ሥራ ከመንጠቅ ይልቅ ለኮንትራክተሩ ድጋፍ ሰጥቶ እንዲቀጥል የማድረግ አሠራር የሚከተለው አሁን እንደታየው ዓይነት መዘግየት እንዳይኖር ጭምር ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የቱርኩ ኩባንያ ብዙ ድጋፍና ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም፣ ሥራውን ሊያሻሽል የማይችል መሆኑ በመረጋገጡ ዕርምጃ መወሰዱ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

ባለሥልጣኑ ጅምር ሥራዎችን ከኮንትራክተሮች ነጥቆ ለሌላ መስጥቱ የሚያስወጣው ወጪና ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ከታሰበው ጊዜ በላይ ሊወስድ ይችላል የሚል እምነት ያለው መሆኑ፣ ኮንትራክተሮች አቅማቸውን አጎልብተው እንዲቀጥሉ የማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ውል ማቋረጦች ግን ሌላ ሥጋት ያስከትላሉ፡፡ ይኽም ከዚህ በኋላ ያለውን ግንባታ ማናራቸው ነው፡፡ ከቱርክ ኩባንያ ጋር የነበረው ውል መቋረጥና አዲስ ኮንትራክተር ለመቅጠር እየወሰደ ያለው ጊዜ ግን፣ ግንባታውን ከማጓተት አልፎ ከዚህ ቀደም ለመንገዱ ግንባታ ከተያዘው በጀት በላይ ወጪ እንዲወጣ ማድረጉ እንደማይቀር ባለሥልጣኑም ያምናል፡፡

ምክንያቱም ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የገበያ ዋጋና አሁን ሊኖር በሚችለው የገበያ ዋጋ መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩ ስለማይቀር ነው፡፡ ዋጋው የሚጨምር ቢሆንም የመንገዱን ሥራ ለማስቀጠል ግን አዲስ ጨረታ ለማውጣት የተጫራቾች ሰነድ እየተፈተሸ ስለሆነ፣ በቅርቡ አሸናፊ የሚሆነው ኩባንያ ታውቆ ሥራው ይጀመራል ተብሏል፡፡

በሦስት ተከፋፍሎ ከደብረ ብርሃን እስከ አዋሽ አርባ ድረስ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት ከሌሎች በተለየ ስንክሳሮች የበዙበት ነው የሚል አስተያየት የሚሰጥበት ሆኗል፡፡ የቱርኩ ኩባንያ ካቋረጠው መንገድ ሌላ በዚሁ የደብረ ብርሃን አዋሽ አርባ ፕሮጀክት አካል የሆነው የአንኮበር ዱለቻ መንገድ ሥራም በተመሳሳይ በታሰበለት ጊዜ ሊጀምር ያልቻለ ነው፡፡ የዚህን መንገድ ሥራ በተያዘለት ጊዜ ገደብ ያለመጀመር ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት ይህንን መንገድ ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የነበረው የህንዱ ቪል ኩባንያ የኮንትራት  ማስከበሪያ የባንክ ማረጋገጫ ባለማቅረቡ ጨረታው በመሰረዙና ሥራውን ለሌላ ተቋራጮች ለመስጠት ለአዲስ ጨረታ ጊዜ በመውሰዱ ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በኋላ በተደረገ የድጋሚ ጨረታ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን አሸንፎ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ የቱርክ ኩባንያ ይዞት እንደነበረው ፕሮጀክት ሁሉ ይኽም ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ቢባልም፣ ሳይካሳ ቀርቶ ድጋሚ ጨረታ በማውጣት ሥራው እንደ አዲስ እንዲጀመር ለሌላ ኮንትራክተር የተሰጠው ባለፈው ሳምንት በመሆኑ በማጠናቀቂያው ጊዜ ሥራው እንዲጀመር አስገድዷል፡፡

የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነው ሌላው ፕሮጀክትም ቢሆን ግንባታው አልተጀመረም፡፡ ባለሥልጣኑ ሰሞኑን እንደገለጸው ሦስተኛው ፕሮጀክትን ለመገንባት ጨረታ ወጥቶ የተጫራቾች የመወዳሪያ ዶክመንት እየተመረመረ ሲሆን፣ በቅርቡ ለጨረታው አሸናፊ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ የመንገድ ኮንስትራክሽን ግንባታ ውስጥ እያጋጠሙ ያሉ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ግን ለግንባታ ወጪን መናርና አገልግሎቱን በሚፈለገው ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ እንቅፋት መፍጠሩም አልቀረም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች