Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​በሶማሌ ክልል የኢሳ ብሔረሰብ አባላት ራስን የማስተዳደር ጥያቄ አቀረቡ

​በሶማሌ ክልል የኢሳ ብሔረሰብ አባላት ራስን የማስተዳደር ጥያቄ አቀረቡ

ቀን:

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን የሚኖሩ የኢሳ ብሔረሰብ አባላት ራሳችንን የማስተዳደር መብት ተነፍገናል፣ እንዲሁም ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጪ የብሔረሰቡ ይዞታ ወደ አፋር ክልል እንዲቀላቀል ተደርጓል ሲሉ አቤቱታቸውን አሰሙ፡፡  

ብሔረሰቡ የወከላቸው 11 ግለሰቦች ይህንኑ አቤቱታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት፣ ለፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ከየትኛውም አካባቢ በላይ የተጐዳው የሲቲ ዞን መሆኑ በመንግሥትም የተረጋገጠ እንደሆነ የሚጠቁሙት ተወካዮቹ፣ ብሔረሰቡ የሚገኝበትን ዞን ማስተዳደር ባለመቻላቸው ከፍተኛ በደል እየተፈጸመ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/1 እና 3 ላይ የተደነገገው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብትን ለመሸራረፍ የሶማሌ ክልል መንግሥት “Dib u Urasho” ወይም ‹‹ህዳሴ›› በሚል ድብቅ አጀንዳ እኛ እንዲያስተዳድሩን የመረጥናቸውን የብሔረሰብ ተወላጆች ከሥራ አባረው፣ በሌሎች (የኦጋዴን ጐሳ) ተወላጆች እንዲያስተዳድሩ አድርገዋል፤›› በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

በተለይ ከድርቁ ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንግሥት ለሲቲ ዞን የሚያቀርበው ኮታ በተላኩት አስተዳዳሪዎች እየተመዘበረ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለፌዴራል የአደጋ መከላከል ኮሚሽን ያቀረቡት አቤቱታ በተወሰነ ተቀባይነት ቢያገኝም አጥጋቢ አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳን አነጋግረነው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት፣ ወደ ዞኑ የሚላከው የምግብ ዕርዳታ በዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በኩል እንዲከፋፈል ማድረግ መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡

ይሁን እንጂ የዓለም የምግብ ፕሮግራም መልሶ ለዞኑ የቀበሌና የወረዳ አመራሮች የሚያቀርብ መሆኑን፣ አመራሮቹ ደግሞ የብሔረሰቡ አባላት ባለመሆናቸው የኢሳ ብሔረሰብ የዕርዳታ ጥያቄ በአግባቡ አለመመለሱን ይናገራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢሳ ብሔረሰብ በሚኖርባቸው አዴይቱ፣ ገዳማይቱና ሁንዱፍ በተባሉ ከተሞች ላይ የአፋር ክልል ያነሳው የይገባኛል ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳይመራ፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የአፋርና የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንቶችን ብቻ በማነጋገር ከተሞቹ ለአፋር ክልል መወሰኑ ተገቢ አለመሆኑንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጥስ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ እንደቀረበለትና እንደሚመለከተው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የብሔረሰቡ አባላት ያነሱትን ብሔረሰቡን የማስተዳደር ጥያቄ በተመለከተ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትን በማኅበራዊ ድረ ገጽ ገጻቸው ምላሽ እንዲሰጡበት በውስጥ መልዕክት ቢጠየቁም፣ እንዲሁም በስልክ በተደጋጋሚ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

የፌዴራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቄ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢሳ ብሔረሰብ አባላት ራሳቸውን ለማስተዳደር ያነሱት ጥያቄ ከማንነት ጋር የሚገናኝ ስለሆነ በመጀመሪያ ለክልሉ መቅረብ እንደሚገባው፣ የክልሉ ምክር ቤት በሚወስነው ውሳኔ ላይ ተቃውሞ የሚኖር ከሆነ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአፋር ክልል አስተዳደራዊ ወሰን ተደርገው ሦስቱ ከተሞች በመከለላቸው ግን በሥፍራዎቹ ለሚኖሩ የኢሳ ማኅበረሰብ አባላት ትልቅ ጥቅም ማስገኘቱን ሚኒስቴሩ እንዳረጋገጠ አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በራሳቸው ቋንቋና ወግ እየተዳደሩ በመሆናቸው ወደ አዋሽ ወንዝ በነፃነት ተጠግተው ከብቶቻቸውን ያለግጭት እያጠጡ ነው፤›› በማለት ችግሩ የተቀረፈ ነው ብለዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...