Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመድረክ ሠልፍ የማድረግ መብቱ እንዲከበር ጠየቀ

መድረክ ሠልፍ የማድረግ መብቱ እንዲከበር ጠየቀ

ቀን:

በአምባገነኖች አፈና፣ በደኅንነትና በስለላ መዋቅር ጥንካሬ ተደግፎ የሚቆም ሥርዓት ሰውን ወደ አመፅና አገርንም ወደ አለመረጋጋት ይመራል፣ ሲል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አስታወቀ፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብቱም እንዲከበር ጥያቄ አቀረበ፡፡

መድረክ ይህን ያስታወቀው ዓርብ የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ‹‹ኢሕአዴግ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በሕገወጥነት በመጣስ እየፈጸመ ያለውን ወንጀል በአስቸኳይ ያቁም›› በሚል መሪ ቃል ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

‹‹አንድ አምባገነን ሥርዓት ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እያሰረ፣ እያዳከመና እየጨፈለቀ በሄደ ቁጥር ዜጐች በውስጣቸው የሚቀጣጠለው ስሜት ይበልጥ እየጠነከረና እየጐለበተ፣ ጥያቄያቸውም እያደገ ስለሚመጣ ፍላጐታቸውን በአመፅ ከማራመድ ወደኋላ አይሉም፤›› በማለት መድረክ በመግለጫው አትቷል፡፡

የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መንግሥት ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በመድረክ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ዕገዳ በመጣል፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳይችሉ አድርጓል በማለት ኮንነዋል፡፡

በዚህም መሠረት ታኅሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. መነሻውን አፍንጮ በር አካባቢ ከሚገኘው ዋና ጽሐፈት ቤቱ ተነስቶ በራስ መኮንን ድልድይ፣ በመሀል ፒያሳና በቸርችል ጎዳና አድርጐ ድላችን ሐውልት ደርሶ የሚጠናቀቅ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያደራጅ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢያሳውቅም፣ አስተዳደሩ ዕውቅና አልሰጥም በማለቱ ሠልፉ ሳይካሄድ ቀርቷል በማለት ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ጥር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. መነሻውን ግንፍሌ አካባቢ አድርጐ በቤልኤር ሆቴል በህንድ ኤምባሲ በመታጠፍ፣ ወደ አዋሬ አደባባይ አድዋ ቁጥር 2 ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ በሲግናል አድርጐ ድንበሯ ሆስፒታል በኩል የካ ወረዳ 8 ታቦት ማደሪያ ደርሶ የሚጠናቀቅ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ቢያቅድም፣ እንደገና በመከልከሉ ሠልፉ ሳይካሄድ ቀርቷል በማለት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሠልፉን ለማከናወን አትችሉም የሚለው ምላሽ የተሰጣቸው ደግሞ፣ ‘በምታልፉበት ሥፍራ ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አሉ’ የሚል እንደነበር አስታውሰው፣ ‹‹እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እሑድ ዕለት ትምህርት ቤቶችም ሆነ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ እንደሆኑ ነው፤›› በማለት ምላሹ አጥጋቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ሠልፉን በመተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝቡ ጋር ለመወያየት በመስቀል አደባባይ ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ስብሰባ ለማካሄድ ቢታቀድም፣ እንዲሁ ተከልክሏል በማለት ፕሮፌሰር በየነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት በመድረክ ላይ የጣለውን የሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ የማደራጀት ኢ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀብ በማንሳት፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን እንዲያከብርና እንዲያስከብር አበክረን እንጠይቃለን፤›› በማለት የመድረክ መግለጫ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...