Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር መተዳደሪያ ደንቡን ከ24 ዓመታት በኋላ አሻሻለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ላለፉት 24 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን መተዳደሪያ ደንብ ወቅታዊ በማድረግ ማሻሻሉን አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ ይህንን ያስታወቀው ሐሙስ የካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ባካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ነው፡፡ በዕለቱ በርካታ የማኅበሩ አባላትና የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብ ከማፅደቅ በተጨማሪ፣ ባለፈው አንድ ዓመት የተከናወኑ የማኅበሩን ሥራዎች ሪፖርት ያደመጠ ሲሆን፣ የውጭ ኦዲተር ሪፖርትንም አድምጦ በሙሉ አፅድቆታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላላ ጉባዔው የማኅበሩ አመራር ቦርድ አባላትና የዘርፉ ተዋንያን የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች የሚመሩበት የሥነ ምግባር ደንብም አፅድቋል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አበራ በቀለ፣ ‹‹ላለፉት 24 ዓመታት ስንመራበት የቆየው መተዳደሪያ ደንባችንን ማሻሻልና ይበልጥ ወቅታዊ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፣ አሁን ያለውን አጠቃላይ የማኅበራት ሕግ ማዕቀፍ ባስታረቀ መልኩ እንዲዘጋጅ በባለሙያ አስጠንተን በቦርዱ ከተገመገመና ቦርዱም ስምምነት ላይ በመድረሱ፣ እንዲፀድቅ ለአባላቱ እናቀርባለን፤›› በማለት በስብሰባው መክፈቻ ወቅት ገልጸው ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ተሳታፊዎቹ የተወሰኑ አስተያየቶችን በማከል እንዲፀድቅ በሙሉ ድምፅ በመወሰን አዲሱን መተዳደሪያ ደንብ ተቀብለውታል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው የተገኙት የኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው፣ በዕለቱ የፀደቁት መተዳደሪያ ደንብና የአባላት የሥነ ምግባር መመርያ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ተቀራርቦ ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በዋነኛነት የሚጠቀሱ ሁለት ችግሮች እንዳሉበት የገለጹት ዶ/ር አምባቸው፣ የመጀመሪያው ችግር የአቅም እጥረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሥነ ምግባር ችግር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት ከሚስተዋልባቸው ዘርፎች አንዱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አማካሪዎች፣ ኮንትራክተሮችና ባለሙያዎች ፈቃድ ሲያወጡ የሚያስመዘግቡት ብቃት የሌለ ነው፡፡ የሐሰትና የተጭበረበሩ ሰነዶችን በማቅረብ ስለሚያስመዘግቡና ፈቃድ አውጥተው በሌለ ብቃት ከአቅማቸው በላይ ፕሮጀክት ስለሚወስዱ፣ በፕሮጀክቶች ላይ የመጓተትና የጥራት ችግር ይስተዋላል፡፡ አዲሱ የሥነ ምግባር መመርያ ይህን ከመዋጋት አንፃር የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር በ1984 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ1,500 በላይ አባላት አሉት፡፡ ማኅበሩ በዋነኛነት በኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን መቅረፍና የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠት ዓላማው አድርጐ የተቋቋመ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች