- ለ82 ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ
በተለያዩ ዘርፎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ 57 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት መዘጋታቸውን፣ የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ምክትል ኃላፊ አቶ አሰፋ ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከተዘጉት ማኅበራት መካከል የኢትዮጵያ ኗሪዎች በጎ አድራጐት፣ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎትና የውጭ በጎ አድራጎት ማኅበራት ይገኙበታል፡፡
ከ57ቱ የተወሰኑት በራሳቸው ጥያቄ ፈቃድ ወስደው ባለፉት ሦስት ዓመታት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለማድረግና በበጀት እጥረት ሊዘጉ መቻላቸውን፣ የኤጀንሲውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በመጥቀስ አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አስተዳደራዊ ወጪን ከፕሮጀክት ጋር ለቀላቀሉ 82 የአገር ውስጥና የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡ የኤጀንሲው ማስጠንቀቂያ ለአንዳንዶቹ የመጀመርያ ሲሆን፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸውም ጥቂት አይደሉም፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ከወጡ አወዛጋቢ አዋጆች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ላይ ይሠሩ የነበሩ ጠንካራ ማኅበራት ከአዋጁ መውጣት በኋላ ከስመዋል ተብሎ ይተቻል፡፡ ይሁንና ከአዋጁ በኋላ በልማት ላይ ያተኮሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ቁጥር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መጨመሩን በመጥቀስ መንግሥት ትችቱን ያስተባብላል፡፡