Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​ቲያንስ የተባለው የቻይና ኩባንያ መታገዱን በተመለከተ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር እየተደራደርኩ ነው አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ምርመራ ጀመረ

ቲያንስ ኢትዮጵያ የተባለው የቻይና ድርጅት ከተፈቀደለት የንግድ አሠራር ውጪ ሲንቀሳቀስ ተገኝቷል ተብሎ የንግድ ፈቃዱ ቢታገድም፣ ከመንግሥት ጋር እየተደራደረ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኩባንያው የተለያዩ የቻይና ተጨማሪ ምግቦች፣ የባህል መድኃኒቶችና የተለያዩ ቁሳቁሶችን አገር ውስጥ በማስገባት በአባላትና በወኪሎች አማካይነት ሽያጭ ያካሂዳል፡፡

የካቲት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. የንግድ ሚኒስቴር ትያንስ የተባለው ድርጅት የአባላቱን ቁጥር በማብዛት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ እየገለጸ ሲሠራ የነበረውን ድርጅት አግደዋለሁ ቢልም፣ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ አለማቆሙንና ችግሩን በቀናት ውስጥ በመቅረፍ መደበኛ ሥራውን እንደሚቀጥል ኃላፊዎቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የድርጅቱ ምክትል የአስተዳዳር ኃላፊ አቶ መኮንን ወርቁ ለሪፖርተር ሲያስረዱ፣ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ያፈነገጠ ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት አለመፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም በንግድ ሚኒስቴር የእግድ ደብዳቤ መጻፉ ግራ እንዳጋባቸው  ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ ከአሁን በፊት የወሰደው ፈቃድና እያከናወነ ያለው ተግባር የማይመጣጠን በመሆኑ እንዲያስተካከል ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም፣ ከስህተቱ ሊታረም አለመቻሉን ነበር የንግድ ሚኒስቴር የእግድ ደብዳቤ የገለጸው፡፡

ነገር ግን አቶ መኮንን በንግድ ሚኒስቴር የተጠቀሰባቸው የሕግ ጥሰት ድርጅቱ ባለመፈጸሙ፣ ሚኒስቴሩን ማብራርያ ጠይቀው መልስ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንና ድርድሩም እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

ቲያንስ ኢትዮጵያ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ2006 ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2007 ጀምሮ በኢትዮጵያ የቻይና የባህል መድኃኒቶች መሠረት አድርጎ የሚቀምማቸውንና የሚያመርታቸውን ምርቶች ለማሰራጨት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን የድርጅቱ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

ሆኖም ኩባንያው የምርት ሽያጩን ለማከናወን ‹‹ፒራሚድ›› ተብሎ የሚጠራውን የአባላት ቅርንጫፍ የማብዣ ሥልት መጠቀም ከሚከለክለው የአገሪቱ የንግድና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ በማይጣጣም ሆኔታ እየሠራ ነው የሚል ወቀሳ በስፋት ይሰነዘርበታል፡፡

ነገር ግን የድርጅቱ ኃላፊዎችም ሆኑ በሥሩ ያሉ አገር በቀል ወኪሎቹ ይህን ወቀሳ በተደጋጋሚ በፍጹም ‹‹በፒራሚድ›› ሥልት ኩባንያው ሥራውን እንደማያከናውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሕጉ (የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ) የፒራሚድ ቢዝነስ እንደማይፈቅድ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ እኛም ምርቶቻችን በአባሎቻችን እንደ ኮሚሽን ኤጀንት በቀጥታ ቢዝነስ ነው የምናከናውነው፤›› ሲሉ አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ቲያንስ በኢትዮጵያ አሉኝ ከሚላቸው 15 ወኪሎች ውስጥ የአንዱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ይታገስ ሉሌሳ፣ ‹‹የቲያንስን አሠራር ብዙዎች ጠጋ ብለው ባለመረዳታቸው የተነሳ በፒራሚድ ቢዝነስ እንደሚሳተፍ ያላግባብ ይወቅሳሉ፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡

ነገር ግን የተለያዩ ሰዎች የቲያንስ ዓይነት የንግድ አሠራር፣ እሴት የማይጨምርና ከበርካታ ሰዎች ገንዘብ በመሰብሰብ ጥቂቶችን ብቻ የሚጠቅም መሆኑን ክርክር ያቀርባሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴራል የንግድና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መርከብ ዘለቀ፣ በቲያንስ አሉ የተባሉ ጥርጣሬዎችን ለመመርመር ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ‹‹የፒራሚድ›› አሠራር በተባለው ጉዳይና በንግድ ሚኒስቴር ቢታገድም ሥራ ባለማቆሙ ሳቢያ ክስ ለመመሥረት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ አንቀጽ 22 የተከለከተለ ድርጊቶች በሚል ርዕስ ሥር ንዑስ አንቀጽ 6 ላይ፣ ሸማቾች አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎትን የሚገዙ ወይም በሽያጭ ሥልት ውስጥ የሚገቡ ከሆነ፣ በሸማቹ ቁጥር ልክ የገንዘብ ወይም የዓይነት ጥቅም እንደሚያገኝ የሚል ፒራሚዳዊ የሽያጭ ሥልትን ተግባራዊ ማድረግ የተከለከለ ነው ይላል፡፡

ቲያንስ ኢትዮጵያ ይኼንን ሕግ በመጣስ ይንቀሳቀሳል የሚል ወቀሳ እየተሰነዘረበት ነው፡፡ በዋናነት አልሚ ምግቦችን ከውጭ አገር የማስመጣት ፈቃድ በመጠቀም የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ አካላትን በማብዛት፣ የገንዘብና የውጭ አገር ሽርሽር ጥቅም እንደሚያገኙ በመግለጽ ጥቂቶች የሚበለፅጉበትን ሥርዓት ማዘጋጀቱን ደርሼበታለሁ፣ ሲል የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ቲያንስ ኢትዮጵያ ግን ወቀሳውን በፍጹም እንደማይቀበለው ይልቁንም ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሀብት፣ የሥራ ምንጭና ዜጎችን ከስደት መታደግ መቻሉን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ200 ሺሕ አባላት ያሉት መሆኑን፣ በዓመት ለኢትዮጵያ መንግሥት እስከ 27 ሚሊዮን ብር ታክስ እንደሚከፍል ይናገራል፡፡ ይሁንና የተጀመረበት ምርመራ ግን ቀጥሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች