Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት አበድሮ ያልመለሰለት ገንዘብ 92.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ንግድ ባንክ በኮርፖሬት ቦንድ የሰጠው ብድር 152 ቢሊዮን ብር ደርሷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለፌዴራል መንግሥት በጀት መሸፈኛ ካበደረው ገንዘብ ውስጥ ያልተመለሰለት 92.1 ቢሊዮን ብር መድረሱን ከባንኩ የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት በጀት መሸፈኛ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው መንገዶች አንዱ ቀጥታ ብድር ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በቦንድ ሽያጭ ከኢኮኖሚው የሚሰበሰበውና ለመንግሥት ግምጃ ቤት የሚያስገባው ናቸው፡፡

ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው የባንኩ እ.ኤ.አ. የ2014/15 ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ ከላይ በተጠቀሱት ሁለት የማበደሪያ ሥልቶች ለማዕከላዊ መንግሥት ያበደረው 115.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ መንግሥት የተወሰነውን የመለሰ ቢሆንም፣ 92.1 ቢሊዮን ብር ግን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ያልተከፈለ መሆኑን የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ባንኩ በቀጥታ ለማዕከላዊ መንግሥት አበድሮ ያልተመለሰለት ገንዘብ 83.2 ቢሊዮን ብር ወይም 90.3 በመቶ ሲሆን፣ ቀሪው 9.7 በመቶ ደግሞ በቦንድ ተበድሮ ያልተመለሰለት ነው፡፡

በተመሳሳይ ባንኩ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያበደረው ገንዘብ በዓመቱ መጨረሻ ላይ 23.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ15.3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለማዕከላዊ መንግሥት እየሰጠ ያለው ቀጥታ ብድር በእጅጉ እያደገ መምጣቱን የሚገልጹት ባለሙያዎች፣ የብድሩ መጠን እያደገ በሄደ ቁጥር የዋጋ ግሽበት ግፊትን የሚያመጣ በመሆኑ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በጥቅምት ወር ባወጣው ሪፖርትም ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት እየሰጠ ያለውን ቀጥታ ብድር ሊያቆም ይገባል በማለት ምክረ ሐሳቡን ለግሷል፡፡ ለዚህ የሰጠው ምክንያትም በአገሪቱ ውስጥ እያቆጠቆጠ የሚገኘው ባለ ሁለት አኃዝ የዋጋ ንረትን ከግምት ማስገባቱን ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ ለአይኤምኤፍ በሰጠው ምላሽ በቀጣዮቹ ዓመታት የቀጥታ ብድር መጠኑን እየቀነሰው እንደሚሄድ በመጠቆም፣ የዋጋ ግሽበት ተፅዕኖ እንደማይኖረው ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት በአገሪቱ ያለውን የኮርፖሬት ቦንድ ሽያጭ በመገምገም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮርፖሬት ቦንድ ግዥ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህ የማበደሪያ ሥልትም እ.ኤ.አ. በ2014/15 የበጀት ዓመት ንግድ ባንክ የገዛው ኮርፖሬት ቦንድ (ለኮርፖሬሽኖች በመንግሥት ዋስትና ያበደረው ገንዘብ) 48.3 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ይህም ካለፈው ዓመት 50.2 በመቶ ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡

በመሆኑም በዓመቱ መጨረሻ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገዙ ኮርፖሬት ቦንዶች 152.7 ቢሊዮን ብር መድረሳቸውን አመልክቷል፡፡

ከዚህ ውስጥ 75 በመቶው ወይም 85.9 ቢሊዮን ብር ዕዳ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሲሆን፣ 15 በመቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ 8.5 በመቶ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ እንዲሁም 0.7 በመቶ የክልል መንግሥታት ዕዳዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች