Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​በአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት 600 ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ ተወሰደ

​በአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት 600 ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ ተወሰደ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ600 በላይ ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ ወሰደ፡፡ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ሠራተኞች በማዕከልና በክፍላተ ከተሞች ባሉ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት መዋቅሮች ውስጥ የሚሠሩ ናቸው፡፡

አስተዳደሩ በእዚህ ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ የወሰደው በሥነ ምግባር፣ በሙስናና በብቃት ማነስ ምክንያቶች መሆኑ ታውቋል፡፡ በተጠናቀቀው ሳምንት የተጀመረው ዕርምጃ ከዚህ ቀደም ከተወሰደው የተለየ ነው፡፡ ዕርምጃውም ከሥራ መታገድ፣ ወደ ሌሎች ቦታዎች መዛወርና በሕግ መጠየቅን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለአብነት ያህል በማዕከል ደረጃ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር በሚገኙ ሰባት ኤጀንሲዎች ውስጥ ከሚሠሩ ሠራተኞች 43 ያህሉ የዕርምጃው ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ሠራተኞች ውስጥ ስድስቱ በሕግ የሚጠየቁ ሲሆን፣ የተቀሩ ከሥራ የሚታገዱና ወደ ሌሎች ቦታዎች የሚዛወሩ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በክፍለ ከተማ ደረጃ ደግሞ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በመሬት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ 89 ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ከእነዚህ ሠራተኞች ውስጥ 17 የሚሆኑት በሕግ እንዲጠየቁ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን፣ የተቀሩት ከሥራ ገበታቸው እንዲታገዱና ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲዛወሩ ተወስኗል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማም እንዲሁ 69 ሠራተኞች መታገድ፣ ከቦታ መዛወርና በሕግ የመጠየቅ ዕርምጃ ተላልፎባቸዋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ 40 ሠራተኞች ከሥራ የታገዱ ሲሆን ስድስት ሠራተኞችን በሕግ ለመጠየቅ የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ያፀደቀው ይህ ውሳኔ በተጠናቀቀው ሳምንት በአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታው አመራር ሰጪነት ተግባራዊ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከአስተዳደሩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱ በተለያዩ መንገዶች ባካሄደው ግምገማ ሲሆን፣ እነዚህ ሠራተኞች በሰነድ አልባ ይዞታዎች፣  በሊዝ በሚተላለፉ ቦታዎች የይዞታ ባለቤትነትና ስም ዝውውር ወቅትና በመሳሰሉት የመሬት ሥሪት ሥራዎች ሕገወጥ ተግባራትን አከናውነዋል በሚል ምክንያት ነው፡፡  ኅብረተሰቡም ባገኘው አጋጣሚ በዘርፉ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ሲጠቁም የቆየ በመሆኑ ጭምር ነው ተብሏል፡፡ የተቀሩትም በአቅም ማነስ ምክንያት ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ታውቋል፡፡ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን አልቻሉም የሚለው ምክንያት የአስተዳደሩን ሠራኞች ያስገረመው፣ እነዚህ ሠራተኞች በፌዴራል ደረጃ ተዘጋጅቶ የተሰጠውን የብቃት መመዘኛ ሥልጠናና ፈተና ተፈትነው የመጡ መሆናቸው ነው፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተቋቋመው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ 900 የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ሠራተኞች ይህንን ሥልጠና ወስደዋል፡፡ ሥልጠናው ከግል፣ ከሙያ ማኅበራትና ከክልል ከተሞች ለተወጣጡ 4,800 ሠራተኞች ጨምሮ የተሰጠ ነው፡፡ ለዚህ ሥልጠና መንግሥት 132 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡

የአስተዳደሩ 900 ሠራተኞች ይህንን ሥልጠናና ፈተና ወስደው ወደ ሥራ ከተሰማሩ ብዙም ሳይቆዩ በተካሄደ ግምገማ 600ዎቹ ጥፋተኛ ናቸው ተብሎ የተወሰደ ዕርምጃ በመሆኑ፣ ሥልጠናውና ለሥልጠናው የወጣው ወጪ ከስሯል በሚል ነው የሠራተኞቹ አግራሞት መነሻ፡፡

ቢያንስ ግምገማው ቀደም ብሎ ቢካሄድና መንግሥት ለመረጣቸው ሠራተኞች ብቻ ሥልጠናው ቢሰጥ መልካም ነበር በማለት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአስተዳደሩ ሠራተኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ ከአራት ወር በፊት በወረዳ መወቅሮች ውስጥ የነበሩ ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸው አመራሮችና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸውን 630 አመራሮች መቀነሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...