Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​በታክስ ማጭበርበር የተደረሰባቸው የቻይና ኩባንያዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እየተወሰደ አለመሆኑ ጥያቄ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በታክስ ስወራና ማጭበርበር የደረሰባቸው የቻይና ኩባንያዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እየወሰደ አለመሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

የባለሥልጣኑ የኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬትና የኢንስፔክሽን ኦዲት ዳይሬክቶሬት በሚያደርጉት ምርመራ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በታክስ ስወራና ማጭበርበር ቢደርስባቸውም፣ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ የሚገባው የባለሥልጣኑ የሕግ ማስከበር ዘርፍ ግን ተግባራዊ ዕርምጃ በመውሰድ ላይ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

የባለሥልጣኑ የኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ግሬት ቃል ኮንስትራክሽን ማቴሪያል ማኑፋክቸሪንግ የተባለ የቻይና ኩባንያ ላይ ባገኘው የታክስ ማጭበርበር የምርመራ ኦዲት እንዲደረግ ባዘዘው መሠረት፣ የባለሥልጣኑ የኢንስፔክሽን ኦዲት ዳይሬክቶሬት የኦዲት ምርመራ አድርጐ በየካቲት ወር 2007 ዓ.ም. የደረሰበትን ውጤት እንዳቀረበ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ኩባንያው በተጠረጠረበት ወንጀል 8.1 ሚሊዮን ብር እንደተገኘበት፣ ይህንንም የሚያስረዳ ማስረጃ አባሪ በማድረግ ለሕግ ማስከበር ሥራዎች ዘርፍ ጽሕፈት ቤት መምራቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ዜንግ ሮንግ የተባለ ማሽነሪ አከራይ የቻይና ኩባንያ ላይ የምርመራ ኦዲት እንዲሠራ የኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ባዘዘው መሠረት፣ የኢንስፔክሽን ኦዲት ቡድኑ ኩባንያው የተጠረጠረበት ወንጀል እርግጥ መሆኑንና 6.1 ሚሊዮን ብር እንደሚፈለግበት በመግለጽ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ከአባሪ ማስረጃዎች ጋር ሪፖርት ማድረጉን ምንጮች አክለዋል፡፡

በተጨማሪም ሸዋንግሎንግ የተባለ የቻይና ኮንስትራክሽን መሣሪያዎች አከራይ ኩባንያ ላይም በተደረገ ተመሳሳይ የምርመራ ኦዲት፣ 66.45 ሚሊዮን ብር የግብር ስወራና ማጭበርበር መከናወኑን የኦዲት ቡድኑ አረጋግጦ ለሕግ ማስከበር ሥራዎች ዘርፍ ከአባሪ ማስረጃ ሰነዶች ጋር መምራቱን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ መረጃዎች ማሳያ መሆናቸውን የሚጠቅሱት ምንጮች፣ ሆን ተብሎ በተከናወነ የግብር ስወራ ወንጀል ኩባንያዎቹ ቢደረስባቸውም እስካሁን ድረስ ዕርምጃ እንዳልተወሰደባቸው ይገልጻሉ፡፡

ባለሥልጣኑ በርካታ የአገር ውስጥ ኩባንያዎቻችን በታክስ ማጭበርበር ለፍርድ እያቀረበ ሳለ፣ በቻይና ኩባንያዎች ላይ ዳተኛ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ይገልጻሉ፡፡

አያይዘውም አንዳንዶቹ ኩባንያዎች ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ በተፈቀደ የማሽን ኪራይ ንግድ ላይ ተሳትፈውና የታክስ ማጭበርበር ተግባር ተገኝቶባቸው፣ ባለሥልጣኑ ዕርምጃ አለመውሰዱ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተርና የሕግ ማስከበር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለባቸው ንጉሤን ለማነጋገር በተደጋጋሚ የተደረገው ጥረት ‹‹ከእንግዶች ጋር ነኝ››፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ስብሰባ ላይ ነኝ›› በማለታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች