Sunday, December 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​የኤርትራ ባለሥልጣናት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚሳተፉ ኢጋድ አስታወቀ

​የኤርትራ ባለሥልጣናት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚሳተፉ ኢጋድ አስታወቀ

ቀን:

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥት (ኢጋድ) ተቀማጭነቱ ናይሮቢ ከሆነው ሰሃን ፋውንዴሽን ከተባለው የጥናት ማዕከል ጋር በመተባበር ባካሄደው ጥናት፣ በአፍሪካ ቀንድ በሚካሄደው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደሚሳተፉ ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡

እንደ አዲስ የተዋቀረው የኢጋድ የፀጥታ ፕሮግራም (ISSP) ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር በመተባበር ጥናት በማድረግ ያወጣው ባለ 39 ገጽ አዲስ ሪፖርት፣ በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ ከዚያም ወደ አውሮፓ በሚደረገው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በውጭ የሚገኙ የኤርትራ ከፍተኛ ዲፕሎማቶችና በአገር ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ተባባሪ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡

ባለፈው ሐሙስ የካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ የውጭ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በተገኙበት ይፋ የሆነው ይኼው ሪፖርት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት አደገኛ ንግድ እየሆነ መምጣቱን፣ የኤርትራ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ከተወሰኑ የሶማሊያ፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ዜጎች ጋር በመመሳጠር የተራቀቀና ውስብስብ ኔትወርክ መፍጠራቸውን ያስረዳል፡፡

ኤርትራ ውስጥ ሆነው የሚተባበሩትን ባለሥልጣናት ስም መጥቀስ ያልተፈለገ ቢሆንም፣ በዚህ ድርጊት ከተሳተፉትና በሪፖርት ከተካተቱት መካከል በቅፅል ስሙ ‹‹ኦባማ›› በመባል የሚታወቀው ጆን ሀብታሙና ሀብታሙ መርሃይ ይገኙባቸዋል፡፡ ጆን ሀብታሙ በአሜሪካ ክስ ተመሥርቶበት ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን፣ ሀብታሙ መርሀይ ደግሞ ባለፈው ዓመት በጣሊያን መንግሥት ለእስራት ከተዳረጉት መካከል ነው፡፡

ሀብታሙ መርሃይ የኤርትራ ባለሥልጣናት ወደ አውሮፓ ጉዞ ሲያደርጉ የሚያጅብ የኔትወርኩ ተወካይ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት ለኤርትራ ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ (የማነ ሞንኪ) አቀባበል ሲያደርግላቸው አብረው የተነሱትን ፎቶ ሪፖርቱ ይዞ ወጥቷል፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሰዎች ንግድ ብቻ ሳይሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የፀጥታና የደኅነነት ሥጋት እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት የኢጋድ የፀጥታ ፕሮግራም ኃላፊ ኮማንደር አበበ ሙሉነህ፣ ችግሩን ለመፍታት የአባል አገሮች የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ሌሎች የፕሮግራሙ ተሳታፊ የሆኑ በአዲስ አበባ የሚገኙ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችም ሥጋታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በተለይ የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ ኅብረቱ ከኢጋድና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት በሜዲትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ከገቡት 154 ሺሕ ስደተኞች መካከል፣ 39 ሺሕ ያህሉ ኤርትራውያን መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ 140 ሺሕ ኤርትራውያን ስደተኞች መኖራቸውን ያሳወቀ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱት ኤርትራውያን ቁጥር በእጥፍ እየጨመረ በመምጣት ባለፈው ዓመት ከጥር ወር እስከ ነሐሴ ብቻ 34,451 ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አዲሱ ሪፖርት ታማኝ መረጃዎች ያላቸውን ዋቢ በማድረግ ጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያና በሱዳን አነሳሽነት እንዲሁም በእንግሊዝና በጣሊያን መንግሥታት ድጋፍ የተጠናው ይኼው አዲስ ሪፖርት፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አውሮፓ የገቡ አዲስ ስደተኞችንና በመንገድ ላይ የተገኙ ሌሎች ስደተኞች ቃለ መጠይቅ ተደርገውበታል፡፡ ቀደም ሲል በአይኤስ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቤተሰቦችም ቃለ መጠይቅ በሪፖርቱ መካተቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...