Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​ፍትሕ ሚኒስቴር ለአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ስለሰጣቸው ዋስትና እንደማያውቅ ፖሊስ ተናገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች የምርመራውን ሒደት ተቃወሙ

የአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ ለነበሩት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ በአካውንታቸው በቂ ስንቅ (ገንዘብ) ሳይኖራቸው ደረቅ ቼክ በመጻፋቸው የተጀመረባቸው ምርመራ ወይም ክስ ካለ እንዲቋረጥ ፍትሕ ሚኒስቴር ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ስላስተላለፈው (ስለበተነው) የዋስትና ደብዳቤ እንደማያውቅ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የካቲት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ገለጸ፡፡  

መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ለአቶ ኤርሚያስ ደረቅ ቼክን በሚመለከት ስለሰጣቸው ዋስትና እንደማያውቅ የተናገረው፣ በአቶ ኤርሚያስ ላይ ቀሪ ምርመራዎች እንደሚቀሩትና አንድም በቂ ስንቅ ሳይኖራቸው ለተለያዩ ሰዎች ከ80 በላይ የጻፏቸው ደረቅ ቼኮች መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ ከአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች ስለዋስትና ደብዳቤው በመጥቀስ በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት ነው፡፡ የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ አቶ ኤርሚያስ ደረቅ ቼክ ጽፈዋል ተብሎ ሊጠረጠሩ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ደረቅ ቼኩን በሚመለከት የተጀመረ ምርመራና ክስ ካለ እንዲቋረጥ ፍትሕ ሚኒስቴር ዋስትና ሰጥቷቸዋል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የሰጣቸውን ዋስትና ባላነሳበትና ይፋ ባላደረገበት ሁኔታ ሊጠረጠሩበት እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡ በፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ፊርማ ለሁሉም ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የዋስትና ደብዳቤው መበተኑንና ለፍርድ ቤቱም ማሳየት እንደሚችሉ ጠበቆቹ ገልጸው፣ ተቃውሞአቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡

የጠበቆቹን ተቃውሞ የተቃወመው መርማሪ ቡድኑ እንዳስረዳው፣ ደረቅ ቼክን በሚመለከት ፍትሕ ሚኒስቴር ስለሰጠው ዋስትና መረጃ የለውም፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር እሳቸውን ለማቅረቢያ ወይም ለማምጫ ዘዴ ተጠቅሞ ይሆናል፡፡ ፖሊስ ግን በተሰጠው የመመርመርና የማጣራት ሥልጣን እየሠራ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ፖሊስ ከየካቲት 3 እስከ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ በተሰጡት አሥር ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ ከአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ቤት ገዢዎች የዘጠኝ ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን ገልጿል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ግዥና ሽያጭ ጋር የተገናኙ የሰነድ ማስረጃዎችን ሰብስቧል፡፡ ከአቶ ኤርሚያስ ዘንድ አክሲዮን የገዙ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተዋዋሉበትን ሰነድ እንዲልኩ በደብዳቤ መጠየቁን፣ ከተጠርጣሪው አቶ ኤርሚያስ የተወሰነ ተጨማሪ ቃል መቀበሉንና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን አስረድቷል፡፡

ከቤት ገዢዎችና ከሌሎችም የምስክርነት ቃል መቀበል እንደሚቀረው፣ የአክሰስን ገንዘብ ያለቦርዱ ዕውቅና አቶ ኤርሚያስ እያወጡ ለተለያዩ ድርጅቶች ማቋቋሚያ ማዋላቸው ጥቆማ ስለደረሰው እያጣራ መሆኑን፣ ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያዩ አገሮች በራሳቸው ስም የገዟቸው ድርጅቶች እንዳሉ መረጃ ደርሶት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እያፈላለገ መሆኑን፣ ያለምንም ደረሰኝ ከአቶ ኤርሚያስ ገንዘብ የወሰዱ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ተከታትሎ መያዝ እንደሚቀረው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ቀደም ብሎ ለተለያዩ ተቋማት የተበተኑ ደብዳቤዎችን መሰብሰብ፣ የተገዙ ቦታዎች ሕገወጦቹን ከሕጋዊዎቹ የመለየትና ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ፣ እንዳይሸጡና እንዳይለወጡ በማሳገድና በማጣራት ላይ መሆኑንም የምርምራ ቡድኑ ገልጿል፡፡

ከ80 በላይ ደረቅ ቼኮች ላይ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተከፈለ የተጻፈ ቢሆንም፣ ይከፍላል በተባለው ባንክ ውስጥ በቂ ስንቅ (ገንዘብ) አለመኖሩ ስለተመታበት በማጣራት ላይ መሆኑንና የምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው፣ በርካታ ቦታዎችንና ቤቶችን ሲገዙ በቅድሚያ እንደሚከፍሉና ቆየት ብለው ገንዘብ ሳይመለስ ውሉን በማፍረስ ገንዘቡ እንዲቀር የተደረገ በመሆኑ እየተከታተለ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ ከአክሰስ ጋር በጋራ ለማልማት ቤት የሸጡ፣ መሬት የሸጡና ገንዘብ የተቀበሉትን፣ እንዲሁም ምን ያህል ገንዘብ ተከፍሏቸውና ምን ያህል ገንዘብ ቀርቷቸው ባለድርሻ እንደሆኑ አድራሻቸውን በማፈላለግ እያጣራ መሆኑንም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ የአክሰስ አክሲዮን ማኅበር ሒሳብ ከዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባለሙያ ተመድቦ እየተሠራ በመሆኑ ውጤቱን እየተጠባበቀ መሆኑን፣ አክሲዮን ማኅበሩ ሲቋቋም ለማስታወቂያ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ግብረ አበሮች ከፍተኛ ገንዘብ የተከፈለ በመሆኑ እነሱን አፈላልጎ በማግኘት ቃል የመቀበል ሥራ እንደሚቀረው፣ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ያናጋ ድርጊት ከመፈጸማቸው አንፃር ሥራው ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት አመልክቷል፡፡

‹‹ይቅርታ ይደረግልንና ፖሊስ እየሠራ ያለው የኦዲት ሥራ ነው፡፡ ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዳው ወይም ቀሪ ምርመራ እንዳለው እያስረዳ ያለው ሥራ በሙሉ ኦዲተር የሚሠራውን ወይም መሥራት ያለበትን ሥራ ነው፤›› በማለትም ከአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች አንዱ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበውን የምርመራ ሒደት ተቃውመዋል፡፡

የአንድን መሥሪያ ቤት ሒሳብ ኦዲተር ከሠራ በኋላ ግኝቱ ወንጀል ከሆነ እንዲመረመር ወደ ፖሊስ እንደሚልክ ወይም የአሠራር ስህተት ከሆነ ወደ አስተዳደር እንደሚመራ ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡ አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ጠቅላላ ጉባዔው ተስማምቶበትና የቦርድ አባላቱ ፈርመው ባሳለፉት ስምምነት መሠረት የማኅበሩ ሒሳብ ኦዲት መደረጉንም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ የተጠረጠሩት በ1.4 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ የማኅበሩ ሒሳብ ሲሠራ ግን የአክሰስ ሀብት 4.5 ቢሊዮን ብር መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ይህም ሪፖርት ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ባለድርሻዎችና የተጋበዙ የቤት ገዢዎች በተገኙበት ሪፖርት መቅረቡን፣ ምን ያህል ገንዘብ ለምን እንደወጣ፣ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በቦርድ አመራሮቹ ሲቀርብ አንድም ተቃውሞ እንዳልገጠመውና በሚዲያ ታትሞ መውጣቱንና እነሱም የስብሰባው ተሳታፊ እንደነበሩ ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በባለድርሻዎች ጥያቄ የቀረበውን የኦዲት ሪፖርትና ያለምንም ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ የፀደቀውን ሪፖርት ፍርድ ቤቱ አስቀርቦ ሊመለከተው እንደሚችል የተናገሩት ጠበቆቹ፣ መርማሪ ቡድኑ በቀላሉ ማግኘት የሚችለውን የምርመራ ውጤት ገና ኦዲት እያስደረገ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበውን ማመልከቻ ተቃውመዋል፡፡

የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ማንኛውም ማለትም ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት (ሚኒስትሮች) የሚመራው አብይ ኮሚቴ መታገዱ የሚታወቅ መሆኑን ያስታወሱት ጠበቆቹ፣ በተደጋጋሚ መርማሪ ቡድኑ ‹‹ንብረት ማሳገድ ይቀረኛል›› እያለ የሚጠይቀው ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቤት ገዢዎች ውል የፈጸሙት ከአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ጋር እንጂ ከአቶ ኤርሚያስ ጋር አለመሆኑን ደጋግመው ያነሱት ጠበቆቹ፣ አክሰስ በገባው ውል መሠረት ውሉን አፍርሰው በፍትሐ ብሔር ክስ በመመሥረት ከነኪሳራው ከመጠየቅ ባለፈ፣ ‹‹አቶ ኤርሚያስ የሚጠየቁት በየትኛው ሕግ ነው? ሕግ አለ ካለ ፖሊስ አሁኑኑ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳልን፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ ‹‹ጉዳዩ ፍትሐ ብሔር ነው›› ብሎ መዝገቡን እንዲዘጋም ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ባለፉት 41 ቀናት (እስከ የካቲት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ) አቶ ኤርሚያስን እየመረመራቸው ቢሆንም፣ እያቀረበ ያለው ሪፖርት ግን ተመሳሳይ መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ እስካሁን የነበረው የምርመራ ጊዜ በቂ መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ደረቅ ቼክን በሚመለከት የመንግሥት አካል የሆነው ፍትሕ ሚኒስቴር ዋስትና የሰጣቸው መሆኑንና ለሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማት እንዲያውቁት መደረጉን፣ 1.4 ቢሊዮን ብር የተባለውም አቶ ኤርሚያስን ሳይሆን የሚመለከተው አክሰስ ሪል ስቴትን መሆኑን፣ ቦርዱ ሳይፈቅድ በራሳቸው ፈቃድ ገንዘብ እያወጡ ለሚፈልጉት ነገር ማዋላቸውን በሚመለከትም፣ ጠቅላላ ጉባዔ የሰየመው ቦርድ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ኃላፊነት የሰጣቸው መሆኑን፣ ይጠየቁ ቢባል እንኳን ማኅበሩ የተቋቋመው በንግድ ሕግ በመሆኑ በንግድ ሕጉ ሊጠየቁ እንደሚገባ፣ ነገር ግን መጠየቅ ካለበትም ጠቅላላ ጉባዔው የሰየመው ቦርዱ መጠየቅ እንዳለበት ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ አስረድተው፣ አቶ ኤርሚያስ በወንጀል ተገደው ሊጠየቁ እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡

በጠበቆቻቸው አማካይነት ከበቂ በላይ መናገራቸው ቢነገራቸውም ዝም ብለው የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ፣ የማኅበሩ ሰነዶች ከአራት እስከ ስምንት ዓመታት የቆዩና ኦዲት ተደርገው ዕገዳ የተጣለባቸው በመሆኑ፣ እሳቸው ሊደርሱባቸው እንደማይችሉ፣ ምርመራም ሆነ ሌላ ሒደትን ሊያደናቅፉና ምስክርም ሊያባብሉ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሌለ ገልጸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዳይፈቀድም ጠበቆቹ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በድጋሚ በሰጠው ምላሽ እንዳስረዳው፣ አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ኦዲት እንደሠራ ቢገልጽም ኦዲቱን የሠራው ድርጅት ለምርምራ የሚበቃ እንዳልሆነና የተጠቀሰውን 1.4 ቢሊዮን ብር እንደማያሳይ እንደነገረው ገልጿል፡፡ የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ ቤት ገዢዎች እንደተገኙ መገለጹ ስህተት መሆኑን ቡድኑ አስረድቶ፣ አቶ ኤርሚያስ ገንዘብ እንዳልወሰዱ ጠበቆች ቢናገሩም ገንዘቡን እንደፈለጋቸው ሲያደርጉ እንደነበር መረጃ እንዳለው ተናግሯል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ሳይሆኑ መጠርጠር ካለበትም ማኅበሩ ስለመሆኑ በጠበቆቹ የተገለጸውን በሚመለከት፣ አቶ ኤርሚያስ ክህደት መፈጸማቸውን፣ በደረቅ ቼክ ማታለላቸውንና የእምነት ማጉደል በመሆኑ ወንጀል ስለሚሆን ለመጠርጠራቸው በቂ ምክንያት መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በተሰጠው ጊዜ እየሠራ መሆኑንና ድርጊቱ ከውስብስብነቱ አንፃር ተመሳሳይ ቢመስልም ቡድኑ ግን ሥራ እየሠራ መሆኑን አስረድቶ፣ አቶ ኤርሚያስ በአየር ላይ ዲዛይን ብቻ እየሸጡ የብዙዎችን ገንዘብ በማባከናቸው ሰፊ ምርመራ ማድረግና እውነትን ማፈላለግ ተገቢ በመሆኑ የጠየቀው ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት በድጋሚ አመልክቷል፡፡ በመርማሪ ቡድኑ (ፖሊስ) እና በጠበቆች መካከል አለመግባባቶችም ሲፈጠሩና የፍርድ ቤቱ የማስቻያ ጊዜ ሲጓተትም ተስተውሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናትን በመፍቀድ ለየካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡        

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች