በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ጥቁር ፕሬዚዳንት በዋይት ሀውስ ማየትን ሲያልሙ የኖሩት የ106 ዓመቷ ቨርጂንያ ማክላውሪን እሁድ የካቲት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ኦባማን በአካል ሲያገኙ በደስታ መደነሳቸው የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ አዛውንቷ መደሰትና መደነቃቸውን መደበቅ አልቻሉም፡፡ እሁድ ዕለት ምሽት ኦባማን በዋይት ሀውስ ሲያገኟቸው በመደነቅ እጃቸውን ዘግተው ሰላም አሏቸው፡፡ ኦባማም አዛውንቷ ቀዳማዊት እመቤትን ማግኘት ይወዱ እንደሁ ጠየቋቸው እሳቸውም እምነታቸውንና ይህ ለእሳቸው ትልቅ ክብር መሆኑን ገለጹላቸው፡፡ ከዚያም ሚሼል ኦባማ መድረኩን ተቀላቀሉ፡፡ አዛውንቷ ኦባማን በአካል ለማግኘት በማኅበራዊ ድረ ገጽ ዘመቻ የጀመሩት እ.ኤ.አ. 2014 ነበር፡፡ በዩቲዩብም ‹‹በሕይወት ዘመኔ ጥቁር መሪ እመለከታለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ዘወትር ለአንተ እፀልያለሁ›› የሚል የንግግር አጭር ፊልምም ለቅቀዋል፡፡ ይህ ዘመቻቸው በብዙዎች ፊርማ የታገዘና ፌስቡክ ላይም የነበረ ነው፡፡
*****************************
አካልም እንደ ቋንቋ
እጅ፤ ሥራን መደብ አድርጎ፤ ቃልን አፍን አንደበትን ኃይልን ሥልጣንን ወዘተ. ያሳያል፡፡
እጅ ቃል መባሉም አፍ ሲናገር እጅም እንደ ምላስ እየሠራን የቃል አጋዥ ረዳት ከቃል ጋር የሥራ ተባባሪነት ያለው ከመሆኑም በላይ፤ የቃል ምትክ፤ የቃል ልዋጭ፤ ስለ ቃል ሆኖ የቃል ንግግርን ወክሎ (በምልክት) የሚገልጽ የሚያስረዳ በመሆኑ ነው፡፡
አፍ፤ መደቡ በከንፈርና በከንፈር መካከል ያለው ክፍት ኅዋ ሲሆን፤ ምላስ በሱ ውስጥ ስላለ ቋንቋ ይሆናል፡፡
የፈረንጅ (የፍሬንች) አፍ፣ የእንግሊዝ አፍ፣ የመስኮብ አፍ፤ … ይባላል፡፡ አፌን ይዤ ሲል ጠበቃዬን፣ ተከራካሪ የሚሆንልኝን ወኪሌን አስተርጓሚዬን፤ ማለቱ ነው፡፡
‹‹እንዲሁም፤ አፉን ሲያሾል፣ አፉን ሲያሞጠሙጥ፣ አፍ አፉን አሉት፤ ቀንድ ቀንዱን አሉት›› ዝም እክም ጭጭ አሰኙት ማለት እንደሆነ የተሰወረ አይደለም፡፡
ምላስ፤ የአፍ ውስጥ ኅዋስ፣ የመብል የነገር መሣሪያ ሲሆን ያለእርሱ መነጋገር ስለማይቻል፤ አንደበት፤ ቋንቋ፤ ልሳን፤ ይባላል፡፡ ያለእሱ መሣሪያነት ቃልና ቋንቋም ሊኖር አይችልም፡፡
- መሸሻ ግዛው ‹‹አጋቶን›› (1963)
*********************************
ያቺ አለላ ሙዳይ….
ያች አለላ ሙዳይ….
ከሩቅ ተቀምጣ-ከቅርብ የምትታይ
ወዲህ ማዶ ሆና-አድማስ ምትታይ
ያቺ አለላ ሙዳይ…
አላት ብዙ ጉዳይ
ሰው አዳኝ-ሰው ገዳይ
ያች አለላ ሙዳይ…
አላት ብዙ ሚስጥር
ለበጎ ሚኳትን-መጥፎ ሚመሰጥር
ያች አለላ ሙዳይ….
እያየኋት በዓይኔ-አላስተውላትም
ድምጻEን እየሰማሁ-አላደምጣትም
ያች አለላ ሙዳይ…
አፍ አላት እንደሰው-አታወራበትም
ነፍስ አላት እንደ እኛ-እሷ ግን አትሞትም!
ያች
አለላ
ሙዳይ…
- ደመቀ ከበደ ‹‹አንድ ክንፍ›› (2003)
******************************
ስታለቅስ ከዓይኗ የድንጋይ ጠጠር የሚወጣው ሴት
በምሥራቃዊ ቻይና ሻንደንግ ግዛት ውስጥ ኗሪ የሆነች ሴት ላለፉት ሰባት ዓመታት ስታለቅስ ከዓይኗ የድንጋይ ጠጠሮች እንደሚወጡ ሚረር ዘግቧል፡፡ ለሰባት ዓመታት በዚህ ሁኔታ የተቸገረችው ሴትና ባለቤቷ ሐኪሞች ምንም ሊያደርጉላቸው ስላልቻሉ በመጨረሻ ወደ መገናኛ ብዙኃን ለመውጣት ወስነዋል፡፡ ይህች ሴትና ባለቤቷ እንደገለጹት ምንም ዓይነት ዶክተር ሁኔታውን ሊረዳውና ይህ ነው ሊላቸው አልቻለም፡፡ ይልቁንም በሚሔዱባቸው ሆስፒታሎች ሁሉ ሐኪሞች ነገሩን እንደማያምኗቸው ተናግረዋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከባለቤቱ ዓይን ውስጥ 30 ጠጠሮች መውጣታቸውን የተናገረው ባል የመጨረሻ አማራጭ ያደረገው ለመገናኛ ብዙኃንና ጉዳዩን አደባባይ ማውጣት ነው፡፡