Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለም​አይኤስና አል ኑስራን ያገለለው የሩሲያና የአሜሪካ ስምምነት

​አይኤስና አል ኑስራን ያገለለው የሩሲያና የአሜሪካ ስምምነት

ቀን:

በሶሪያ ላለፉት አምስት ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ፅንፍ ይዘው ሲወጋገዙ የከረሙት ሩሲያና አሜሪካ ወደ ሰላም መድረክ መጡ፡፡ ሩሲያ የሶሪያን ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ፣ አሜሪካ ደግሞ በሶሪያ አብዮት የቀሰቀሱትን የአል አሳድ ተቃዋሚዎች በመደገፍ ይዘውት የነበረውን አቋም በማለዘብ፣ በሶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ተስማምተዋል፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነቱም ከዓርብ የካቲት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. እኩለ ለሊት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም አል አሳድም ሆኑ ተቃዋሚዎቻቸው በተኩስ አቁም ስምምነቱ ቢካተቱም፣ አይኤስና የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው አል ኑስራ በስምምነቱ አለመግባት የተኩስ አቁሙ ተፈጻሚ እንዳይሆን ያደርገዋል ተብሏል፡፡ 

አልጄዚራ እንደዘገበው፣ አሜሪካና ሩሲያ በሶሪያ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲስማሙ፣ በሶሪያ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ኃይሎች ስምምነቱን እስከ ዓርብ የካቲት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ፈርመው፣ እኩለ ለሊት ላይ ደግሞ ተኩስ አቁሙን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ሆኖም አይኤስና የአል ኑስራ ግንባር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ በመግባታቸው በስምምነቱ አይታቀፉም፡፡ ይህ ደግሞ በሶሪያ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት በፖለቲካዊ መፍትሔ ለመዳኘት እንቅፋት ይሆናል እየተባለ ነው፡፡

- Advertisement -

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው የተመዘገቡት ሁለቱ ቡድኖች በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነቱ እንዲፋፋምም ሆነ እልቂቱ እንዲያይል ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ የአል አሳድ መንግሥትንም ተፈታትነዋል፡፡ ሩሲያ የአሳድን መንግሥት በመደገፍ የአየር ድብደባ ከመጀመሯ በፊትም በተለይ አይኤስ በሶሪያ የተለያዩ ግዛቶችን ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ ዛሬ ከይዞታው ቢያፈገፍግም በቁጥጥሩ ሥር የሚገኙ ይዞታዎች አሉ፡፡ አል ኑስራም እንዲሁ፡፡

በሌላ በኩል ለተኩስ አቁም ከተቀመጠው ቀንና ሰዓት በፊት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ይዞታ ለመቀራመት በሚል የከፋ ጦርነት ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ሥጋት ነግሷል፡፡

የአልጄዚራ ዲፕሎማቲክ ኤዲተር ጄምስ ቤይስ እንደሚለው፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተፈጻሚ እስከሚሆንባት ሰዓት ድረስ በሶሪያ ብዙ ደም መፋሰስ ይኖራል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ወገኖች ከስምምነቱ በፊት ይዞታቸውን ማስፋፋት ይፈልጋሉና፡፡

መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው ሞኒተሪንግ ቡድንም፣ አሜሪካና ሩሲያ ከስምምነት ከደረሱ በኋላ የአየር ድብደባው ቀጥሏል ብሏል፡፡

ዋናው የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚና ባለፈው ወር በጄኔቫ በተካሄደውና ባልተሳካው የሰላም ስምምነት ላይ የተካፈለው የሶሪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስማሚ ኮሚቴ (ኤችኤንሲ)፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚቀበል፣ ሆኖም የሶሪያ መንግሥትና አጋሮቹ ሩሲያና ኢራን ይተገብሩታል የሚል እምነት እንደሌለው አሳውቋል፡፡

‹‹የአሳድ መንግሥት ለአምስት ዓመታት በዘለቀው አገሪቷ ጦርነት ውስጥ ስላለች ነው፡፡ አገሪቷ ላይ ሰላም ከሰፈነ የአሳድ መንግሥት ስለሚያበቃለት፣ አል አሳድና አጋሮቻቸው ስምምነቱን ያከብራሉ የሚል እምነት የለኝም፤›› ሲሉ የኮሚቴው አስተባባሪ ሪያድ ሂጃብ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የአሜሪካና የሩሲያ ፌዴሬሽን በሶሪያ የሚገኙ ሁሉም ኃይሎች፣ የውጭ አካላትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱ የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲተገብሩና ለተፈጻሚነቱ እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡

አል አሳድ ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚቀበሉት፣ ሆኖም አሸባሪ ብለው የሚፈርጇቸው ተቃዋሚዎቻቸው አጋጣሚውን ጊዜ የሚገዙበትና ሲመቻቹ መንግሥትን ለመውጋት የሚጠቀሙበት ከሆነ እንደማይተገብሩት አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም አል አሳድ ስምምነቱን የሚተገብሩት ተቃዋሚዎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለሰላም መውረድ ሲያውሉት ነው፡፡

ቢቢሲ ማክሰኞ ዕለት እንደዘገበው፣ የሶሪያ መንግሥትና ዋናው የአል አሳድ መንግሥት ተቃዋሚዎች ስብስብ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ የአሳድ መንግሥትም አሜሪካና ሩሲያ ባስቀመጡት ዕቅድ መሠረት ተኩስ አቁሙን እንደሚተገብር አሳውቋል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት በበኩሉ የአሳድ መንግሥት የሚያደርገውን የአየር ድብደባና በሰላማዊ ዜጐች ላይ የሚፈጽመውን ወከባ ካቆመ ስምምነቱን እንደሚፈጽሙ አስታውቋል፡፡ አሜሪካም ብትሆን እንደ ከዚህ ቀደሙ አል አሳድ ከሥልጣን ይውረዱና የሰላም ድርድር ይጀመር አላለችም፡፡ አሳድ ባሉበት ድርድሩ እንዲጀመር ተስማምታለች፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን ስምምነቱ ባለፈው ወር በጄኔቫ ተጀምሮ የተደናቀፈውን የሶሪያ መንግሥትና የተቃዋሚዎች ድርድር ዳግም እንዲያንሰራራ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በሶሪያ ከአምስት ዓመታት በፊት አብዮት የተጀመረው በሰላማዊ ሠልፍ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ ነበር፡፡ ሆኖም አብዮቱ ባልተጠበቀ መንገድ ወደ እርስ በርስ ጦርነት በመቀየሱ ከአራት ሚሊዮን በላይ እንዲሰደዱ፣ 250 ሺሕ ያህል እንዲሞቱ፣ የአገሪቱ መሠረተ ልማት እንዲወድምና የተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሽብርተኛ መፈንጫ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

ለአምስት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት አሜሪካ፣ ቱርክና ከሳዑዲ ዓረቢያ የአል አሳድ ተቃዋሚዎችን ሲደግፉ ነበር፡፡ ሩሲያ፣ ኢራንና የሊባኖስ ሒዝቦላህ በሽር አል አሳድን ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የእርስ በርስ ጦርነቱ ከመለዘብ ይልቅ ተቀጣጥሎ አገሪቷን አውድሟታል፣ ሕዝቦቿን አንኮታኩቷል፡፡

የአል አሳድ ተቃዋሚዎች ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚተገብሩ ቢያሳውቁም፣ በሌላ በኩል አይኤስና አል ኑስራ በሰላም ስምምነቱም ሆነ በተኩስ አቁሙ ባለመካተታቸው ጦርነቱ ዘላቂ መፍትሔ ላያገኝ ይችላል፡፡

ሩሲያና አሜሪካ የሩሲያ መንግሥትንም ሆነ ተቃዋሚዎችን በየጎራቸው ደግፈው የሚያካሂዱት የአየር ድብደባ በስምምነቱ መሠረት የሚቆም ቢሆንም፣ አሸባሪ የተባሉትን አይኤስም ሆነ አል ኑስራን ይዋጋሉ፡፡ የእነዚህ ቡድን አባላት ደግሞ አሌፖ፣ ኢድሊብ፣ ደማስቆና ሌሎችም ከተሞች በግልጽም ሆነ በስውር ከነዋሪው ጋር ተቀላቅለው መኖራቸው ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለሶሪያ መንግሥት ወታደሮችና ጥምር ኃይሉ፣ እንዲሁም ለመንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች ‹‹ራስን ለመከላከል ተመጣጣኝ ኃይል መጠቀም ይችላሉ›› ይላል፡፡ ይህ ደግሞ የአየር ድብደባን ጨምሮ ሌሎች ጥቃቶች እንዲፈጸሙ በር ይከፍታል፡፡ ሽብርተኛ የተባሉትን ያላሳተፈ ውይይትና የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ይሆን ይሆን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡        

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...