Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

​‹‹ከመንግሥትም ሆነ ከኩባንያው ኃላፊዎች ሥራ እንድናቆም የተሰጠን ትዕዛዝ የለም››

አቶ ይታገሱ ሉሌሳ፣ የቲያንስ ወኪል

አቶ ይታገሱ ሉሌሳ የዛሬ አራት ዓመት ትያንስ ተብሎ የሚጠራውን የቻይና ኩባንያ ከመቀላቀላቸው በፊት በሸራተን አዲስ ይሠሩ ነበር፡፡ ኩባንያው ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባቸውን መድኃኒትና አጋዥ የምግብ ዓይነቶችን ኔትወርክ ማርኬቲንግ በሚባለው የሽያጭ ስልት በኮሚሽን ለማሻሻጥና የተሻለ ገቢ ለማግኘት በማሰብ ነው ኩባንያውን የተቀላቀሉት፡፡ ኩባንያው የአባላት ቁጥሩንና ወኪሎችን በማብዛት ሲያከናውን በቆየው ስልት ውስጥ አቶ ይታገሱ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው መንቀሳቀሳቸውንና በድርጅቱ አሠራር መሠረትም ተሳክቶላቸው ባለ ስምንት ኮከብ የተባለው የመጨረሻ ደረጃ መድረሻቸውን ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉት የቲያንስ 15 ወኪሎች የአንዱ ባለቤት መሆንም ችለዋል፡፡ የራሳቸውን ድርጅት በመክፈት የአባላት ቁጥራቸውን በማብዛት የቲያንስን የምርት ውጤቶች በማከፋፈል ላይ ይገኛሉ፡፡ ቲያንስ የተባለው የቻይና ኩባንያ የሚከተለው የግብይት ስልት በሺዎች ከሚቆጠሩ አባላት ያለአግባብ ገንዘብ እየሰበሰበ ለጥቂቶች የሀብት ማካበቻና መበልፀጊያ አቋራጭ መንገድ ነው እየተባለ በስፋት ይወቀሳል፡፡ ባለፈው ሳምንት የንግድ ሚኒስቴር ኩባንያው ከተፈቀደለት የንግድ እንቅስቃሴ ውጪ መንቀሳቀሱን ደርሼበታለሁ በማለት የዕግድ ደብዳቤ ጽፎበታል፡፡ እንዲሁም የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ቲያንስ በሕግ በተከለከለው የፒራሚድ ስልት ተንቀሳቅሷል በሚል ጥርጣሬ ምርመራ እያደረገበት ነው፡፡ የንግድ ስልቱ ጥቂቶችን ብቻ በመጥቀም ለብዙኃን መበዝበዣ መንገድ እየሆነ ነው በሚለውና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዮናስ ዓብይ የቲያንስ ወኪል ከሆኑት አቶ ይታገሱ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡– ከቲያንስ ጋር ያለዎትን ግንኙነት ያስረዱን?  

አቶ ይታገሱ፡- በቲያንስ ውስጥ ከአራት ዓመት በላይ ቆይቻለሁ፡፡ እንደ አንድ ደምበኛ ከአራት ዓመታት በላይም ቆይቻለሁ፡፡ በተለይ ከአንድ ዓመት በፊት የቲያንስ ምርቶችን ለማከፋፈል እንደ አንድ ፍራንቻይዝ ኩባንያ (ወኪል) ለመክፈት ስምምነት ፈርመን ዛሬ የራሴን ኩባንያ በመምራት ላይ ነኝ፡፡ የቲያንስን ምርት ከማከፋፈልና በኃላፊነት የራሴን የማከፋፈያ ሱቅ ከማስተዳደር ባሻገር ከቲያንስ ቤተሰቦች ጋር ኔትወርክ በመፍጠር ለአባላት ሥልጠና እየሰጠሁ እገኛለሁ፡፡ በእኔ ስር የሆኑ አባላትንም ሆነ ሌሎችን ለማሠልጠን የሚያስችለኝ የአሠልጣኝነት ማረጋገጫ ከቲያንስ ተሰጥቶኛል፡፡ በኩባንያው መስፈርት መሠረት የስምንተኛ ኮከብ ባለማዕረግ አከፋፋይ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡– ከኩባንያው ጋር አለኝ ያሉትን ምርት የማከፋፈል ውል እንዴት ነበር የገቡት? ውል ለመግባት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ይታገሱ፡- የገባነው ውል በቀጥታ ማንኛውም ሰው ከቲያንስ ጋር ለመሥራት ሲፈልግ የሚዋዋለው ውል ነው፡፡ በተጨማሪም አንድ ሰው ምርቶችን መጠቀም ሲፈልግም ውል መዋዋል አለበት፡፡ እኛም በተዋዋልነው መሠረት አንድ ሰው ምርቱን ገዝቶ ለመጠቀም ሲፈልግ በእኛ በኩል በግዢ ያገኛል፡፡ ከሽያጩ በተጨማሪም ኩባንያውን በመወከል አስፈላጊ መረጃ እንሰበስባለን፡፡ የሰበሰብነውን መረጃም ሆነ ስለሸጥነው የምርት ዓይነትና መጠን ለኩባንያው ሪፖርት እናቀርባለን፡፡ በዚህም መሠረት ኩባንያው ከተሰበሰበው ሽያጭ ለእኛ የኮሚሽን ክፍያ ይፈፅማል፡፡ በዋናነት ለቲያንስ ቤተሰቦች አገልግሎት እንድንሰጥና አብረውን እየሠሩ ያሉ ብዙ ኢትዮጵያውያንንም ሆነ ሌሎችን እንድናገለግል ነው መብቱም ኃላፊነቱም የተሰጠን፡፡

ሪፖርተር፡– እናንተ የቲያንስ ወኪል ሆናችሁ እየሠራችሁ ነው፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ ቲያንስ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ አድርጓል በሚል በንግድ ሚኒስቴር ዕገዳ ተጥሎበታል፡፡ ይህ ዕገዳ እናንተን አይመለከትም?  

አቶ ይታገሱ፡- ንግድ ሚኒስቴር የዕገዳ ደብዳቤ ለኩባንያው (ቲያንስ) መጻፉን ሰምተናል፡፡ በዚህም ጉዳይ ማብራሪያም ሆነ መልስ መስጠት የሚችሉት የኩባንያው ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እኔም ሆንኩ እንደእኔ ያሉ ከ60 በላይ የሚሆኑ ወኪሎች፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ክልሎች ያሉ ምንም ዓይነት የዕግድ ደብዳቤ አልደረሰንም፡፡ ሥራችንንም እንደማንኛውም ቀን እያከናወንን ነው፡፡ ከኩባንያው ጋር ባለን ውል መሠረት የአልሚ ምግቦችን፣ መድኃኒቶችንና ሌሎች ምርቶችንም እየቸረቸርን ነው፡፡ እንደምታየው አገልግሎቱንም እያቀረብን ነው፡፡ ከመንግሥትም ሆነ ከኩባንያው ኃላፊዎች ሥራ እንድናቆም የተሰጠን ትዕዛዝ የለም፡፡

ሪፖርተር፡– ስለዚህ ዕገዳው አከፋፋዮችን አይመለከትም እያሉ ነው? ወይስ እናንተ በአከፋፋይነት በየግላችሁ የንግድ ፈቃድ አውጥታችሁ ነው የምትንቀሳቀሱት?  

አቶ ይታገሱ፡- እኔም ሆንኩ ሌሎች እንደእኔ የቲያንስን ምርት የሚያከፋፍሉ ይህንን ልዩ የንግድ ቦታ ከፍተን የምንሠራው የራሳችንን ንግድ ፈቃድ አውጥተን በራሳችን የግብር ከፋይ ኮድ ነው፡፡ ራሳችንን ችለን እንደ አንድ ተቋም እንጂ በቲያንስ ፈቃድ አይደለም የምንንቀሳቀሰው፡፡

ሪፖርተር፡– ታዲያ በቲያንስ ላይ የተጣለው ዕገዳ በእናንተ ሥራ ላይ ተፅዕኖ የለውም? ቲያንስ ያለአግባብ የንግድ እንቅስቃሴ እያከናወነ ለጥቂቶች የመበልፀጊያ መንገድ በመክፈት ሌሎችን ለምዝበራ ዳርጓል የሚለው ጉዳይ አይመለከታችሁም?  

አቶ ይታገሱ፡- ሰሞኑን በንግድ ሚኒስቴር ከተነሳው ነገር በተጨማሪ በተለያዩ ሚዲያዎች ስለቲያንስ የሚሠራጩ መረጃዎች አሉ፡፡ መረጃዎቹ ከእኛ ጋር እየሠሩ ያሉን የቲያንስ አባላትንና ብዙዎችን እያነጋገሩ ነው፡፡ በቅድሚያ ግን ቲያንስ ማን ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ቲያንስ በ110 አገሮች ቢሮዎችን ከፍቶ የሚንቀሳቀስ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ነው፡፡ ዋና ቢሮው በቻይና ቲያንጂን ውስጥ ይገኛል፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥም ከዓመታት በፊት ቢሮ ከፍቶ ይንቀሳቀሳል፡፡ በኢትዮጵያም ከከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ስለሚስማራባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች እየተወያየ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቲያንስ ዳታ እንደሚያመለክተው ከ200 ሺሕ በላይ አካላቶች ወይም የቲያንስ ቤተሰቦች አብረን እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡– በምን ጉዳይ ላይ ነው በዋነኝነት አብራችሁ የምትሠሩት?

አቶ ይታገሱ፡- በዋነኝነት አጋዥ ምግቦችን ያቀርብልናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የንፅህና መጠበቂያ፣ ሳሙና፣ የጥርስ ሳሙና አስገብቷል፡፡ የሚያመርተውን ለጤና ጠቃሚ የሆነ የማሳጅ ማሽን ራሱም እኛም እናከፋፍላለን፡፡ እኔና እንደእኔ ዓይነት ብዙዎች ተጠቃሚ ሆነናል፡፡ ለምሳሌም እኔ በሸራተን አዲስ ተቀጥሬ አገለግል ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ መካከለኛ ገቢ ያለው ሰው ዓይነት ነበርኩ፡፡ ቲያንስን ተቀላቅዬ የራሴን ወኪል አከፋፋይ ሱቅ መክፈት በመቻሌ ደህና ገቢና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን አገኛለሁ፡፡ ልክ እንደእኔ ሁሉ ብዙዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ከ140 በላይ ኢትዮጵያውያን የመኪና ባለቤት ለመሆን ችለዋል፡፡ ብዙዎች ኑሯቸው ተለውጧል፡፡ በሌላ በኩል ትልቅ የዓለም አቀፍ ፈተና በሆነው የስደት ጉዳይ ቲያንስ የራሱን እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ከ150 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከዓረብ አገሮች ተመልሰው ከቲያንስ ጋር በመሥራታቸው የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ማሻሻል ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል ቲያንስ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ በዓመት እስከ 27 ሚሊዮን ብር ታክስ ይከፍላል፡፡ ለሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ለአገሪቱ እገዛ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡– እርስዎ እየዘረዘሩት ያለው የቲያንስ አገራዊ አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ ኩባንያው ብዙኃንን በመበዝበዝ እያደረሰ ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይበልጣል የሚለው ሚዛን የደፋ ይመስላል፡፡ እርስዎ በቲያንስ ተሳክቶላቸው ትልቁን የስኬት ማማ ተቆናጠዋል ያሏቸውን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ሌሎች የቲያንስ ቤተሰቦች በማለት የምትጠሯቸው አባላት ከገንዘብ ኪሣራ አልፈው ቤተሰብ እስከመበተን ደርሰዋል የሚለውን አስተያየት እንዴት ያዩታል?  

አቶ ይታገሱ፡- እንግዲህ እያንዳንዱ ግለሰብ ወደ ቲያንስ መጥቶ ለመሥራት ፍላጎቱን ሲያሳይ የሚዋዋለው ውል አለ፡፡ እኛ ፈቃደኛ ሆነን ወደ ኩባንያው ስንመጣ የሚሰጠን ሥልጠና አለ፡፡ እንዴት ቢዝነሱን እንደምንሠራ፣ እንዴትስ ከሰዎች ጋር መግባባት እንዳለብን፣ የአገሪቱን ሕግ እንዴት አክብረን መንቀሳቀስ እንዳለብንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ሥልጠናው ይሰጣል፡፡ ሥልጠናዎች በነፃ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን በጥያቄው እንደተነሳው ሥራውን የጀመረ ሁሉ ይሳካለታል ማለት አይቻልም፡፡ ሩጫ የጀመረ ሁሉ ሩጫውን ይጨርሳል አይባልም፡፡ ትምህርት የጀመረ ሁሉ እንዲሁ ትምህርተን ይጨርሳል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መልክ መንጠባጠብ የማይቀር ነው፡፡ በውስጣዊም ሆነ ውጫዊ በሆነ ምክንያት ቢዝነሱን ጀምረው የሚያቆሙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሌላውም ዓለም ያለውን ነገር ብናጠና በስፋት መረጃውን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ከቲያንስ ጋር ሲሠራ የሚሠራውን ሥራ በአግባቡ ማወቅ አለበት፡፡ ለዚህም ኩባንያው በተለያዩ መድረኮች ነፃ ሥልጠና ያዘጋጃል፡፡ ጊዜውን እንዴት መጠቀም እንዳለበት፣ ምርትን እንዴት ማከፋፈል እንዳለበትና ሌሎችን አስፈላጊ ስልቶችና ሕጎች በሥልጠና ማዳበር አለበት፡፡ ይህንን ተከትለን እየሠራን ብዙዎች ከቲያንስ ጋር ስኬታማ መሆን ችለናል፡፡ አሁን እንደሚባለው ጥቂቶችን ተጠቃሚ፣ ብዙዎችን ለጉዳት ዳርጓል ሲባል እንሰማለን፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን ብዙዎች ተጎድተዋል የሚለው እውነታ አለው ወይ የሚለው በአግባቡ መታየት አለበት፡፡ እርግጠኛ ነኝ ተጎዳን ከሚሉ ሰዎች እጅግ በብዙ እጥፍ የሚሆኑት የተጠቀሙት ናቸው፡፡ ተጠቀምን የሚሉ ሰዎችን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሚዲያዎች ተጎዳን የሚሉ የጥቂት ሰዎችን ድምፅ ሲያሰሙ እየታዘብን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት በኩል ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ አገርን የሚጎዳ ነገር ቢሆን እዚህ ውስጥ መግባት አይገባንም ነበር፡፡ ብዙዎችን ተጎጂ በሚያደርግ እንቅስቃሴ ውስጥ ብንሆን እኔም ሆንኩ ሌሎች አብረን የምንሠራ ኢትዮጵያውያን የአገርን ሕግ የሚጥስና አገርን የሚጎዳ መሆኑን ብናውቅ ድርጅታችንን እንዘጋ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡– ለእርስዎ ጥቂት ቢሆኑም ተጎጂዎች እንዳሉ አልካዱም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተጎጂዎች ለጉዳት የተዳረጉት በራሳቸው ችግር ነው እያሉ ነው?  

አቶ ይታገሱ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት አንድ ሰው ወይም ደንበኛ ውል የሚፈጽመው ስለመጣ ብቻ ሳይሆን ምርቱን ገዝቶ ለመጠቀም ሲወስን ነው፡፡ በቅድሚያ ወደ ቲያንስ መጥቶ አብሮ ለመሥራት ፈቃደኝነቱን ከገለጸ በኋላ ምርቱን ወስዶ (በግዢ) ይቀምሳል ወይም ያያል፡፡ ያን የሚያደርገውን ቀምሶ ወይም አይቶ ያላወቀውን ምርት ሌላ ቦታ አስተዋውቆ መሸጥ ስለማይችል፡፡ ከዚያም ስለገዛውና ስለተጠቀመው ምርት ሄዶ ለሚያውቃቸው ሰዎች ማስተዋወቅ ቀጣዩ ሥራችን ነው፡፡ ያ ሥራችን ነው እንግዲህ በኮሚሽን ክፍያ እንድናገኝ የሚያስችለን፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለምሳሌ እኔ መጥቼ ስለምርቱ ለአንተ ነገርኩም ከዚያም አንተ መጥተህ ምርቱን ከገዛህ ኩባንያው ለእኔ ኮሚሽኑን ይከፍለኛል፡፡ ይህ እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ መሠረታዊ ሥራው አካል ነው፡፡ ለዚህም ነው በኩባንያውም በኩል ሆነ በእኔና በሌሎች በኩል ሥልጠናውን በነፃ የምንሰጠው፡፡ እንግዲህ በዚህ ጊዜ ነው ሥልጠናውን በማቋረጥ ወይም በአግባቡ ባለመከታተል አንዳንዶቹ በአቋራጭ መንገድ ለመሹለክ የሚሞክሩት፡፡ እነዚህ ለመሠልጠን ፈቃደኛ የማይሆኑ ሰዎችን ሲስተሙ በራሱ ከጨዋታ ውጪ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ወደ ስኬት ምንም ዓይነት አቋራጭ መንገድ የለም፡፡ ኔትወርክ ማርኬቲንግ ወይም Multi-level ማርኬቲንግ ወይም ቀጥተኛ የንግድ ስልት (Direct Selling Scheme) እኛ አገር ውስጥ አዲስ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ኢንዱስትሪውን በአግባቡ ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ አሠራሩን፣ ባህሪው፣ በእኛ በኩል መሟላት ስለሚኖርባቸው ጉዳዮች፣ የአገሪቱስ የሕግ ማዕቀፍ ይህንን በተመለከተ ስላለው ድንጋጌና ሌሎችን ጨምሮ ከማንኛውም ተሳታፊ ማወቅ ይጠበቃል፡፡ ይህንን ለማሳወቅ ደግሞ እኛም (ወኪሎች) ሆንን ኩባንያው ለማሳወቅ ዝግጁ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ዓይነት አሠራር ለማየት ፈቃኛ ያልሆኑ ሰዎች ላይሳካላቸው ይችላል፡፡ ይህንንም ደግሞ በተግባር አይተናል፡፡

ሪፖርተር፡– ስለዚህ ቲያንስን ‹በጠራራ ጸሐይ ዘረፈን› በማለት ጩኸት የሚያሰሙት ሲስተሙ ተፍቷቸው የወጡ እንጂ የቲያንስ ችግር አይደለም ብለው እየደመደሙ ነው?  

አቶ ይታገሱ፡- ሲጀመርም ቢሆን አንድ ሰው ከቲያንስ ምርቱን የሚገዛው ሊጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ይህን ሱፍ ለብሻለሁ አንተም እንዲሁ በተመሳሳይ ገዝተህ ለብሰሃል፡፡ ይህንን ገዝተን በመልበሳችን ከስረናል ማለት ነው? እኔ ከስሬያለሁ ሊባል አይችልም፡፡ ኩባንያው ለጤናችን ብለን በምንገዛቸው ምርቶች መሠረት፤ እንደገናም ምርቶቹን ማስተዋወቅ በመቻላችን ተጨማሪ የማካካሻ ክፍያ ይከፍለናል፡፡ ይህንን ሥራ የመሥራት ሒደት ላይ ሰዎች ሥልጠናውን መከታተል ሳይፈልጉ ሲቀሩና በራሳቸው መንገድ ለመሄድ ሲሞክሩ ላይሳካላቸው ይችላል እንጂ ቢያንስ ቢያንስ ተጨማሪ የገንዘብ ገቢ ባያገኙም ምርቱን በከፈሉት ገንዘብ ተጠቅመው ሲያበቁ በምን መነሻነት በጠራራ ጸሐይ ተዘረፍን ያስብላል? ሰው ቀምተኸው ከሮጥክ ወይም ካጭበረበርከው ነው ተዘረፍኩ ሊል የሚችለው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ሲመጣ ሕጋዊ ደረሰኝ ሰጥተን ነው የምናስተናግደው፡፡ ስለዚህ በጠራራ ጸሐይ ዘረፉ ተብሎ በሕግ እንደማንኛውም ተቋም ልንጠየቅ ይገባል የሚል እምነት አለኝ እንደስሞታው ከሆነ ማለት ነው፡፡ ይኼ በመሠረቱ የግንዛቤ ችግር ነው፡፡ በሚዲያ ተቋማትም ቢሆን በዜና ዘገባዎቻቸው ሚዛናዊ ያለመሆን ችግር አለ፡፡ ከዚህ ባለፈም አንዳንድ ተቋማት ቲያንስ እንዲዘጋ አቋም ይዘው እንደሚገፉት ገልጸውልናልም፡፡

ሪፖርተር፡– አጠቃላይ የኔትወርክ ማርኬቲንግ ላይ የግንዛቤ ችግር መኖሩን በማብራሪያዎ እንደጠቀሱት ለኢትዮጵያውያን አዲስ መሆኑ በራሱ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው የሚናገሩ አሉ፡፡ ከራስዎ ተሞክሮ ተነስተው አዋጪ ዘርፍ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ይታገሱ፡- የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ቢዝነሶችን ይሞክራሉ፡፡ በተለይም በዚህ ጊዜ ተቀጥሮ ከሥራት ይልቅ የራስን ቢዝነስ ከፍቶ መሥራቱ የተሻለ ስለመሆኑ ምሁራኖችም ሆኑ ሁላችን የምንገነዘበው እውነታ ነው፡፡ አንድ ቢዝነስ ለመሥራት ስንነሳ የሚያስፈልጉ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለመጥቀስም ያህል የመነሻ ካፒታል፣ የመሥሪያ ቦታ፣ የቢዝነስ ሐሳብ፣ የምንቀጥራቸው ሠራተኞች፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን የመሳሰሉ ነገሮችን ቀድመን መመለስ አለብን፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ነገሮች ደግሞ ቢዝነስ ለመሥራት የተነሳን ሰው የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ወደ ቲያንስ ስንመጣ እንደ ሰው ቢዝነሱን ለመቀላቀል ሲፈልግ መነሻ ካፒታልም ሆነ ከላይ የጠቀስናቸው ነገሮች ሁሉ አያስፈልጉትም፡፡ እያንዳንዱ መጥቶ ምርቱን መጠቀም ነው ያለበት፡፡ እናም ወደ ቲያንስ ስትመጣ ምርቱን መጀመሪያ ገዝተህ ተጠቀም ነው ጨዋታው፡፡ ቀላል ቢዝነስ ስለሆነ ምርቱን ለራሴ ተጠቅሜ በዙሪያዬ ላሉት ሰዎች ማስተዋወቅ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ እነዚያ ሰዎች መጥተው ምርቱን መጠቀም ሲችሉ ኮሚሽን የሚገኝ ስለሆነ ካፒታል የሚባል ነገር አያስፈልገኝም ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ካፒታል አያስፈልግም ሲሉ ግልፅ ያልሆነ ነገር አለ፡፡ ቢያንስ እናንተ ጋር በቅድሚያ አንድ ሰው ሲመጣ የመመዝገቢያ ወይም የውል ክፍያ አለ? ያ መነሻ ካፒታል ሊባል አይችልም?

አቶ ይታገሱ፡- ወደ እኛ ወደ ቲያንስ አንድ ሰው ሲመጣ ምርቱን ለመግዛት ነው፡፡ ቢያንስ በትንሹ የ3,800 ብር የሆነ አንድን ምርት ይገዛል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ምርት ሲጠቀም በቀጣይ በሚኖረው የኮሚሽን ሥራ መሠረት ኩባንያው የፈለገበት ቦታ ድረስ ሊያደርሰው ይችላል፡፡ ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ማንም ሰው ከቲያንስ ጋር ሲሠራ የቤት ኪራይ የለበትም፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ከ15 በላይ ሱቆች አሉ፡፡ በሁሉም ቦታ ማንኛውም ሰው ሄዶ በነፃ ይሠራል፡፡ ጥበቃ፣ ጸሐፊ፣ ዕርዳታ ሰጪ የመሳሰሉት የሰው ኃይልም አያስፈልገውም፡፡ ማንኛውም ሰው 24 ሰዓት መሥራት ስለሚችል እንደ አብዛኛው የቢዝነስ ዘርፍ የሰዓት ገደብ የለውም፡፡ አሜሪካ ውስጥ ይህ ሥራ ከሚወደድበት አንድ ነገሩ በቤቱ ማንኛውም ሰው ማከናወን የሚችለው መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ዋናው ነገር ሥራው የተለየ የትምህርት ደረጃና ሊህቅነት የማይጠይቅ በመሆኑ ለማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ክፍት የሆነ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች፣ ለሁሉም ፆታ፣ ከሁሉም ዘር የሆነ ሁሉ ሊሳተፍበት የሚችል ቢዝነስ መሆኑን መመስከር እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– ቲያንስ እየተወቀሰበት ያለው ሌላው ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ በተከለከለው የፒራሚድ ቢዝነስ ስልት አካላቱንና ቅርንጫፉን በማብዛት ሕግ ጥሶ መንቀሳቀስ ነው? መልስዎ ምንድነው?  

አቶ ይታገሱ፡- ፒራሚድ ስልት የተባለው የቢዝነስ ስልት ለአብዛኞቻችን አዲስ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓይነት የቢዝነስ ስልት በኢትዮጵያ ውስጥ ክልክል መሆኑ በግልጽ በሕግ ተደንግጓል፡፡ ፒራሚድ አሁን የቅርጹ ጉዳይ ሳይሆን አሠራሩ በሕጋችን በግልጽ እንደተቀመጠው አንድ ሰው ሌላ ሰውን ስላመጣ ብቻ ኮሚሽን የሚከፈለው ከሆነ ፒራሚድ ነው፡፡ ዋና ሥራውና ትኩረቱ ሰዎችን መመልመል ከሆነ ይኼም ምናልባት ፒራሚድ ያስብለዋል፡፡ ሁለተኛ ሰዎች ለምርት መግዣ ሳይሆን ለአባልነት ብቻ መዋጮ የሚከፍሉም ከሆነ ይኼም ፒራሚድ ሊያስብለው ይችላል፡፡ ኩባንያዎች ለማኅበረሰቡ የሚያቀርቡት ምንም ምርት ከሌላቸው አሁንም ፒራሚድ ሊያስብለው ይችላል ማለት ነው፡፡ ቀጥታ ሽያጭ (Direct Selling) የሚለውን ከውጪዎቹ እንደቀዳነው ሁሉ ፒራሚድ ስልት የሚለውን የእነሱን አተረጓጎም መያዝ ነው፡፡ በእርግጥ ያም ቢሆን በሕጋችን በደንብ ተቀምጧል፡፡ ግን ቲያንስን እንዴት ነው የሚሠራው የሚለውን ከተመለከትን አንደኛ ኮሚሽን የሚከፈለው ሰው ስላመጣን አይደለም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ኮሚሽን የሚከፍለን ገንዘብ በሚሊዮንና ቢሊዮን ደረጃ ባደረስን ነበር፡፡ እዚህ ኮሚሽን የሚከፈለው በዚያ ሰውዬ ስም ወይም እርሱ ወደዚህ ቢዝነስ በጋበዛቸው ሰውዬ ስም አገልግሎት ወይም ምርት ሽያጭ ሲከናወን ነው፡፡ የኮሚሽን ክፍያ ከሽያጭ በኋላ ነው ያለው፡፡ አሁንም ላሰምርበት የምፈልገው ፍሬ ጉዳይ አንድ ሰው ሌላውን አባል ስላደረገ ብቻ ኮሚሽን አያገኝም፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...

‹‹የዋጋ ግሽበቱ እንደ አቅማችን እንዳናበድርና ተበዳሪዎችም እንዳይከፍሉ እያደረገ ነው›› አቶ ፍጹም አብረሃ፣ የአሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

አሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ በተቋም ደረጃ ለመመሥረቱ መነሻው ጓደኛሞች በየወሩ በቁጠባ መልክ የሚቆርጡት ተቀማጭ ገንዘብ ነው፡፡ በ20 ሺሕ ብር ካፒታል በ20 ጓደኛሞች...