Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​የሰሊጥን እሴት የሚጨምር ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወደ ሥራ ገባ

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንደ ሰሊጥ ያሉ ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል የተባለ ማቀነባበሪያ ተገንብቶ ወደ ሥራ ገባ፡፡ ቫዛ የዘይትና የጣፋጭ ምግቦች ማቀነባበሪያ የሚል ስያሜ ያለው ይህ ማቀነባበሪያ 4.2 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያለው ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዱከም ከተማ የተገነባው ይህ ማቀነባበሪያ፣ ጠሂና የሰሊጥ ቅቤ በሚል የሚዘጋጀውን ምርቱን ወደ ባህር ማዶ ኤክስፖርት የማድረግ የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንዳለው ሰኞ የካቲት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ፋብሪካውን ለማስጎብኘት በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ አስታውቋል፡፡

አቅሙን አጠናክሮ በቀን እስከ 80 ኩንታል በማምረት የውጭ ገበያውን ለመቀላቀል እየሠራ መሆኑን የሚገልጸው የኩባንያው መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት ግን የጥሬ ዕቃ ዋጋው እስኪስተካከል በቀን ሰባት ኩንታል እያመረተ ይገኛል፡፡ የኩባንያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሁሴን ሰይድ እንደሚሉት፣ ኩባንያው ከሰሊጥ ቅቤ ጎን ለጎን ከሰሊጥ የሚዘጋጅ ብስኩትና ዘይት ለማምረት የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ እየተመረተ ያለውን ምርት በአገር ውስጥ ገበያ ለማስገባት አጋጥመውኛል ካላቸው ችግሮች ውስጥ ከተረካቢዎች ምርቱን በዱቤ ለመቀበል የመፈለግ አዝማሚያ በመስተዋሉ ነው ተብሏል፡፡

በዓለም ላይ በሰሊጥ ምርት ከሚታወቁ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ በከፍተኛ ዋጋ የሚሸጠው የሁመራ ሰሊጥ መገኛ ስትሆን፣ ከሁመራ ሰሊጥ ቀጥሎ በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የሚመረተው የወለጋ ሰሊጥ በዓለም ገበያ ከሚፈለጉ የሰሊጥ ምርቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአገሪቱ በስፋት የሚመረቱት የሁመራና የወለጋ ሰሊጥ 400,000 ሔክታር መሬት ይሸፍናሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ከሌሎቹ የቅባት ሰብሎች የላቀ የሰሊጥ ምርት መኖሩን ነው፡፡ ይሁንና ሰሊጥን በምግብነት የመጠቀም አጋጣሚ ከሌሎች የቅባት እህሎች በእጅጉ ያነሰ ሲሆን፣ እሴት ጨምሮ የማምረት ልምድም የለም፡፡ ይህም አብዛኛው የሰሊጥ ምርት ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ እሴት የተጨመረባቸው የሰሊጥ ውጤቶች የሆኑ ልዩ ልዩ ምርቶችም ከባህር ማዶ እንዲገቡ ሆኗል፡፡

‹‹በአገሪቱ ከፍተኛ የሰሊጥ ምርት ቢኖርም ሰሊጥ የመመገብ ባህሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህን አገራዊ አዝዕርት እሴት ጨምሮ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት እንሠራለን፤›› የሚሉት አቶ ሁሴን፣ ኩባንያው ምርቶቹን ወደ ውጭ ለመላክ በሚያደርገው ጥረት የመንግሥት እገዛ እንደሚሻ ገልጸዋል፡፡

ጣሂና በቻይናና በመካለኛው ምሥራቅ አካባቢ የተለመደ ምግብ ዓይነት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በውስጡም ፕሮቲን፣ ካልሺየም ኮፐር፣ ዚንክ፣ አይረን፣ ማንጋኒዝና ሌሎችም ንጥረ ነገሮችን ይዟል፡፡ በሰላጣ ላይ በመጨመር ከማርና ከስኳር ጋር ቀላቅሎ ዳቦ ላይ በመቀባት እንዲሁም ከተፈጨረ ቤዲንጀል ጋር በማዋሀድ ጣሂናን መመገብ ይቻላልም ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች