Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​​​​​​​የጣሊያኖች ኩባንያዎች ገዝፈው የወጡበት 20ኛው የንግድ ትርዒት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ዝግጅት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚያዘጋጀው “አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት” ቀዳሚ ስም አለው፡፡

የተለያዩ መሪ ቃሎችን ይዞ በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ የንግድ ትርዒት፣ ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ ከየካቲት 17 እስከ የካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ይካሄዳል፡፡ 20 ዓመታት ባለማቋረጥ የዘለቀው የንግድ ትርዒት የዘንድሮ መሪ ቃሉ ‹‹ዲቨሎፕመንት ኦፍ ኢንዱስትሪ ዞንስ ፎር ኢንዱስትራላይዜሽን ድራይቭ›› የሚል ነው፡፡

የዘንድሮውን የንግድ ትርዒት ዝግጅት አስመልክቶ ትናንት የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. የንግድ ምክር ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ፣ የዘንድሮው የንግድ ትርዒት ዝግጅት በተለየ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህም 20ኛውን የንግድ ትርዒት በተለየ መንገድ ማሰናዳት በማስፈለጉ እንደሆነ የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ገልጸዋል፡፡

በ20ኛው የንግድ ትርዒት ከ18 አገሮች የሚመጡ 130 ኩባንያዎች ተሳታፊ ይሆኑበታል ተብሏል፡፡ 71 የአገር ውስጥ ኩባንያዎችም በዚህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ታዳሚዎች ይሆናሉ ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በጥቅሉ 201 ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

በየደረጃው ዕድገት እየታየበት የመጣ የንግደ ትርዒት ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ ጌታቸው፣ የንግድ ምክር ቤቱ ትርዒት ከ20 ዓመት በፊት ሲጀመር ስለንግድ ትርዒት ሐሳብም ሆነ አስፈላጊነት ራሱ ግንዛቤው አናሳ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የኤግዚቢሽን ማዕከል በዓመት ብቻ 44 የተለያዩ የንግድ ትርዒቶች የሚካሄዱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ ለዚህ ሁሉ የንግድ ትርዒቶች መነሻም ይህ የንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒት ነው ይላሉ፡፡

ንግድ ትርዒቱ በተለያዩ መመዘኛዎች ዕድገት እየታየበት ለመሆኑም የተለያዩ መገለጫዎች እንዳሉት የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ ቀድሞ በተካሄዱት የንግድ ትርዒቶች አነስተኛ የሸቀጣ ሸቀጥ አምራች የሚበዛበት ነበር ይላሉ፡፡ አሁን ግን ትላልቅ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት መሆኑ አንድ ማሳያ ይሆናል ብለዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒቶች ዝግጅት ኃላፊ አቶ ጋሻው አባተም እንደገለጹት፣ 20ኛው የንግድ ትርዒት የተለየ የምንልበት ሌላው መገለጫ የኩባንያዎች ተሳትፎን የሚመለከት ነው፡፡ በጥቅሉ 201 ኩባንያዎች የሚሳተፉ ቢሆንም፣ ይህ የተሳታፊዎች ቁጥር ከቀድሞው ተሳታፊዎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው፡፡ ቀደም ያሉ የንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒቶች ከ250 በላይ ተሳታፊዎችን የያዙ ነበር፡፡

አቶ ጋሻው ግን በዘንድሮው ዝግጅት የተሳታፊዎች ቁጥር ቢቀንስም በዚህ ዝግጅት በርካታ ኩባንያዎች ከቀድሞ በተለየ ሰፋፊ ቦታዎችን በመያዛቸው፣ ለተሳትፎ ጥያቄ ያቀረቡትን ኩባንያዎች ማስተናገድ ባለመቻሉ የተፈጠረ እንጂ ተሳታፊ በማጣት አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ የጣሊያን ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ካሉት አዳራሾች አንዱን ሙሉ መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የኢራን ኩባንያዎችም 30 ካሬ ሜትር ቦታ ይዘዋል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው አሠራር ግን 30 ካሬ ሜትሩን ቦታ ሦስትና አራት ኩባንያዎች ይወስዱት እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች 71 ብቻ መሆናቸው ተሳታፊዎች ጠፍተው ሳይሆን በተፈጠረው የቦታ ጥበት ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ በዘንድሮ ንግድ ትርዒት ከጣልያን 45 ኩባንያዎች ይዘው በመምጣት ቀዳሚውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ከጣሊያን መንግሥትና ኤምባሲ ጋር በመነጋገር በጣልያን መንግሥት ስፖንሰር የሚደረጉና ከተለያዩ የጎረቤት አገሮች ጎብኚዎችን ይዘው በመምጣታቸው የጣሊያን ተሳትፎ እንደጎላው ታውቋል፡፡

በዘንድሮ የንግድ ትርዒት የጣልያን መንግሥት በተለየ የሚወከልበት ነው የሚሉት የንግድ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች፣ ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር ለመነጋገር ከተያዘላቸው ልዩ ፕሮግራም ውጭ በኢግዚቢሽኑ ማዕከል ለሦስት ቀናት የቢዝነስ የውይይት መድረክ አዘጋጅተዋል፡፡ አብረዋቸው ሊሠሩ ከሚችሉ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ለመነጋገር ሰፊ ጊዜ ሰጥተዋል፡፡

የጣልያን ኩባንያዎች የዘንድሮ ተሳትፎ በተለየ የሚታይበት ነው የሚል እምነት እንዲኖር ያደረገበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ፣ ከተሳትፊ ኩባንያዎቹ ውስጥ አብዛኛዎች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራትም ፍላጎት ያላቸው ሆኖ መገኘቱ ነው ተብሏል፡፡

በዚህ የንግድ ትርዒት ከጣልያን ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ኩባንያዎች የምታሳትፈው ቱርክ ናት፡፡ እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ በንግድ ትርዒቱ ከ20 በላይ የቱርክ ኩባንያዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ የኩባንያዎቹ ተወካዮችና ሌሎች የቢዝነስ ሰዎችን ጨምሮ 73 ልዑካን የያዘ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል፡፡ ግብፅ ከ15 በላይ ኩባንያዎችን በማሳተፍ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ እነዚህ አገሮች ከ30 በላይ የንግድ ልዑካንም ይዘው ይመጣሉ፡፡

ከኩባንያዎቹ ተሳትፎ ባሻገር ይህንን ያህል ቁጥር ያለው የልዑካን ቡድን ሲመጣ ለቱሪዝምና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በኬንያ የፕሮሞሽን ኤጀንሲም ከአሥር የሚበልጡ ኩባንያዎችን ይዞ ይመጣል፡፡ በዘንድሮው የንግድ ትርዒት ኢራን በተለየ መንገድ የምትወክል መሆኑ አዲስ ክስተት ተደርጎ ተወስዷል፡፡

አቶ ጋሻው እንደገለጹትም ኢራን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጥሎባት ከነበረው ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ አንፃር እንዲህ ዓይነት ትርዒቶች ላይ ተሳትፎዋ ቀዝቃዛ ነበር፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒት ላይ በዓለም ደረጃ በትልቅነቱ የሚታወቅ አንድ ኩባንያ ይሳተፋል፡፡ ይህ ኩባንያ ከተሳትፎ ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ ለመሳተፍ ያለውን ፍላጎት አሳይቷል፡፡ ፍላጎቱን ወደ ተግባር ለመቀየርም ከንግድ ትርዒቱ ዝግጅት ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋርም ተገናኝቷል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በንግድ ትርዒት ዝግጅት የተሻለ አዘገጃጀት ቢኖረውም የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ገፅታን ያልተቀየረ መሆኑ የዝግጅቱ ከቀድሞው ገፅታ ለውጥ ላይኖረው ይችላል የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል፡፡

አቶ ጌታቸውም ይህ ትክክል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ለማስተካከልና ለመሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ዲሲፒሌይን በተመለከተ ተሳታፊ ኩባንያዎች ራሳቸው ቴክኖሎጂውን ይዘው የሚመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለምሳሌ የቱርክ ፕሮሞሽን ኤጀንሲ ስታንዱንና የመብራት ቴክኖሎጂውን ይዘው ይመጣሉ፡፡ የጣልያንና የግብፅ ኩባንያዎችም የራሳቸውን ቦታ ይዘው በሚመጡት ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ ተብሏል፡፡ ሌላው ትልቅ ችግር ሆኖ የቀረበው ጉዳይ ደግሞ የጎብኚዎች ቁጥር ማነስ ነው፡፡ እንዲህ ካሉ የንግድ ትርዒቶች በተሻለ ባዛሮች የተሻለ ጎብኚ አላቸው፡፡ በቀን 40 ሺሕ ጎብኚዎችን የሚያገኙበት ዕድል ቢኖርም፣ የቻምበሩ የንግድ ትርዒትን በአራትና አምስት ቀናት ቢበዛ ከአሥር ሺሕ ያልበለጡ ጎብኚዎች ብቻ የሚጎበኙት መሆኑ ችግር አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የሥራ ኃላፊዎች፣ ችግሩ መኖሩን አምነዋል፡፡ ነገር ግን ወሳኝ የሚባሉት አካላት እንዲጎበኙት የሚደረግ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒት ታሪክ ከፍተኛ ጎብኚ የተገኘበት ተብሎ የተመዘገበው 13 ሺሕ ነው፡፡

20ኛውን የንግድ ትርዒት በማስመልከት በአገሪቱ የሚከፈቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የሚያተኩር ጥናታዊ ጽሑፍ ለውይይት ይቀርባል፡፡ ከዚህም ሌላ በንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒት ላይ ከ10 እና ከ15 ዓመታት በላይ በተከታታይ የተሳተፉ ኩባንያዎች ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡ ንግድ ትርዒት ብቻውን ውጤታማ ስለማይሆንም የንግዱ ኅብረተሰብ ከውጭ ከመጡት ኩባንያዎች ተወካዮች ጋር ቁጭ ብለው የሚወያዩበት የገበያ ፓርትነርሽፕ የሚፈጥሩበት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ተብሎም ይጠበቃል፡፡    

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች