ለየት ተደርጎ የተሰናዳውና የተጠራው ስብሰባ ላይ ከ1,500 ያላነሱ ታዳሚዎች ከአፍሪካና ከሌሎች አኅጉራት ተሳትፈተውበታል፡፡ ‹‹አፍሪካ 2016፤ ቢዝነስ ፎር አፍሪካ፣ ኢጂፕት ኤንድ ዘ ወርልድ›› በግርድፉ ቢዝነስ ለአፍሪካ፣ ለግብፅና ለመላው ዓለም የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ትልቅ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሰባት የአፍሪካ መሪዎች ታድመዋል፡፡
ከባድ የፀጥታ ኃይሎች ያረበቡበት ስብሰባ ዓላማውን ያደረገው ርዕሱ እንደሚገልጸው አፍሪካውያን ለንግድና ለኢንቨስትመንት እርስ በርስ መተባበር አለባቸው፣ ትብብራቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል የሚል ስሜትም ያጫረ ነው፡፡ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ ከባድ መሣሪያ ተሸካሚ ሔሊኮፕተሮች፣ በምድርና በሰማይ እያንዣበቡ ጥበቃ ሲያካሂዱ የፈጠሩት ድባብ ከባድ ነበር፡፡ ሻርም ኤል ሼክ የቀይ ባህር ዳርቻ ከተማ እንደመሆኗ በምድረ በዳ መሐል ለተመሠረተች የቱሪስት ከተማ የፀጥታ ጥበቃው ከዚህም እጅግ እንዲልቅ ያደረገው የመሪዎች መታደም ይመስላል፡፡ እንዲህ ላለው ስብሰባ እጅጉን የተጠናከረና ከተማዋን ያጠረ ሲሆን በየብስም፣ በባህርም ሆነ በአየር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሲገቱ የሰነበቱበትን ሁለት ቀናት አሳልፋለች፡፡
የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ የገነቧት ሻርም ኤል ሼክ፣ በቱሪስት መዳረሻነቷ ከፍተኛውን ቦታ ይዛ ብትቆይም ከወራት በፊት ሩስያውያን ቱሪስቶችን አሳፍሮ ሲጓዝ በነበረ የመንገደኞች አውሮፕላን በአሸባሪዎች ከተመታና ከተከሰከሰ ወዲህ ከተማዋ ወና ሆናለች፡፡ በደህናው ጊዜ የሩስያውያን መኖሪያ እስክትመስል ድረስ በሩስያ ቱሪስቶች ስትጨናነቅ ትታይ የነበረችው ሻርም ኤል ሼክ አሁን ላይ የቀሯት ቱሪስቶች በጣት የሚቆጠሩትና ሥጋት አይበገሬ ዩክሬናውያን ብቻ ናቸው፡፡
በመሆኑም በቱሪዝም ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ከባድ ፈተና ውስጥ መውደቃቸው ይነገራል፡፡ በአስጎብኝነት፣ በታክሲ ሾፌርነት፣ በሆቴል ሥራ ሙያተኝነት፣ በተለያዩ ቁሳቁስና ጌጣጌጦች ነጋዴነት፣ በሆቴል ባለቤትነት ወዘተ. የተሰማሩ የሻርም ኤል ሼክ ነዋሪዎች ከባዱን ጊዜ እየተጋፈጡት፣ ኦና በሆነችው ደማቋ ከተማ ባዷቸውን ነገን በተስፋ ይጠብቃሉ፡፡
የግብፅ መንግሥት እንዲህ ባለው ከባድ ጊዜ ቱሪስቶችን በማስተናገድ ላይ የተመሠረተ ህልውና ባላቸው ከተሞች እንደነ ሉክሶርና ሻርም ኤል ሼክ ያሉ ከተሞች ላይ ትልልቅ ስብሰባዎችን በማካሄድ ከተሞቹ አሁንም ቢሆን ለጎብኝዎች ያላቸውን ተስማሚነት፣ የፀጥታ አስተማማኝነትና ሌሎችም መልካም ገጽታዎችን ለማሳየት የፈለገ አስመስሎታል፡፡ እንዲህ ባለው ስብሰባ አማካይነት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት እግረ መንገዱን ከተሞቹን የመደጎም አካሄድ ሊሆን እንደሚችል መላምታቸውን ሲገልጹ የተደመጡ ጋዜጠኞችም አልታጡም፡፡
ሪፖርተር በግብፅ የሪዞርት ከተማ ተገኝቶ ያነጋገራቸው በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማሕሙድ ድሪር እንዳብራሩት፣ የስብሰባው ዓላማ የአፍሪካ ኅብረት ካስቀመጣቸው የልማት አጀንዳዎች ጋር የሚያያዝና በመሠረተ ልማት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በጤና እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በርካታ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ወቅቱ የምርጫ ጊዜ በመሆኑ ስብሰባው ላይ የታየው የአፍሪካውያን ተሳትፎ ደህና ሊባል የሚችል እንደሆነ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ይዛ በስብሰባው መሳተፏን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ስብሰባ ወቅት የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ መሪዎች የጎንዮሽ ስብሰባ አካሂደዋል፡፡ የመሪዎቹ ስብሰባ በአጠቃላይ በሦስቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ፍላጎት እንዳለ የሚየሳይ መሆኑን አምባሳደሩ ይገልጻሉ፡፡ በጤና፣ በትምህርት፣ በንግድ ልውውጥና ኢንቨስትመንት፣ በፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና በባህልና በሌሎችም መስኮች ላይ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ፍላጎት ማሳየታቸውንም አምባሳደር ማሕሙድ ድሪር አብራርተዋል፡፡
እርግጥ በአፍሪካ የእርስ በርስ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ይረዳል በተባለው በዚህ ስብሰባ ከታደሙት መካከል የአፍሪካ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዮጂ አዲሱና እንዲሁም ትልልቅ የግብፅ ኩባንያዎች ባለቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ባለፈው ዓመት በምሥራቅና ደቡባዊ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ)፣ በምሥራቅ አፍሪካ የጋራ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኤሲ) እንዲሁም በደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ የልማት ማኅበረሰብ (ሳድክ) አባል አገሮች መካከል የተደረገውን ስብሳባም ግብፅ ማስተናገዷ ይታወሳል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የሦስቱ ቀጣናዎች አባል አገሮች የሦስትዮች የጋራ ስምምነት በዚህችው ሻርም ኤል ሼክ ከተማ አድርገዋል፡፡ የዚህ ስምምነት ሰብሳቢም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሆነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የሦስትዮሽ ስምምነት፣ ከ600 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች የሚወከሉባቸው አገሮችን ያቀፉ 26 አገሮች የሚካተቱበት የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰቦችን ያጣመረ ነው፡፡ የእነዚህ አገሮች ጥምር የኢኮኖሚ አቋም በገንዘብ ሲተመን (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ጂዲፒ) 1.2 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚሆን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይሁን እንጂ በአፍሪካ አገሮች መካከል የእርስ በርስ የኢኮኖሚ ትስስርም ሆነ የንግድ ልውውጡ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክም ሆነ የዓለም ባንክ የሚያወጧቸው መረጃዎች የሚያሳዩት በአፍሪካውያን አገሮችና ሕዝቦች መካከል ያለው የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ከ12 ከመቶ አይበልጥም፡፡ አፍሪካ ከተቀረው ዓለም ጋር በተለይም ከአውሮፓ፣ ከእስያና ከሰሜንና ደቡብ አሜሪካውያን ጋር የምታደርገው የንግድ ልውውጥ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ይህም ሆኖ ግን አፍሪካ በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያላት ድርሻ እዚህ ግባ የሚባል ሆኖ አይታይም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ አፍሪካውያን በአብዛኛው የግብርና ጥሬ ምርቶችን ስለሚያቀርቡና ተወዳዳሪነታቸውም ዝቅተኛ ስለሆነ ነው፡፡
አፍሪካ እንደ ዳቦ ቅርጫት
በመሆኑም አፍሪካ ለራሷ ጉዳዮች ወደ ራሷ መመልከትና መፍትሔ መፈለግ፣ መተባበርና በጋራ መሥራት እንደምትችል ለማሳየት እየሞከረች ስለመሆኗ ለማሳየት የሚረዱ እንዲህ ያሉ ስብሰባዎች አካል የሆነው የግብፁ የአፍሪካ ቢዝነስ ጉባዔም ተመሳሳይ ተልዕኮ ያነገበ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡ እርግጥ ስብሰባው እንደ ቢዝነስ ስብሰባነቱ አዳዲስ ስምምነቶች በኩባንያዎች መካከል ሲደረጉበት ታይቷል፡፡ የባቡር መስመር ዝርጋታ ላይ ከሚሠሩት መካከል ሪፍት ቫሊ ሬይዌስ የተባው የኬንያ ኩባንያ፣ ከግብፁ ካላ ሆልዲንግስ ኩባንያ ጋር ያደረጉትና ሌሎችም ስምምነቶች ይጠቀሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው እየጨመሩ ከመጡ ቀጣናዎች ውስጥ ደቡብ አሜሪካ፣ ምሥራቅ አውሮፓ፣ የገልፍ አገሮች እንዲሁም እስያ ከወትሮው ከምዕራቡ ዓለም የንግድና ኢንቨስትመንት የተሻለ ተሳትፎ በማድረግ በአፍሪካ ለሚታየው የዕድገትና የለውጥ ተስፋ ስንቅ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሆነው በአፍሪካ እየተመነደገ የመጣ የገበያ ብዛትና የመግዛት አቅምን የተረዱ ኩባንያዎች ይበልጥ ወደ አፍሪካ ፊታቸውን ማዞር በመጀመራቸው ነው፡፡
አፍሪካ ኢኮኖሚ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ሲመዘን ከሁለት ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአፍሪካ 300 ሚሊዮን በላይ መካከለኛ ገቢ ያለው ሕዝብ እንደሚኖርም ይታመናል፡፡ ይህም ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ያህል የሚሸፍን መሆኑ፣ ለፍጆታና ምርቶችና ሸቀጦች አፍሪካውያን የተመቹ ገበያዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህ 300 ሚሊዮን መካከለኛ ገቢ ያላቸው አፍሪካውያን ቁጥር ግማሽ ቢሊዮን እንደሚደርስ፣ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ የነበረው የፍጆታ ወጪያቸውም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 1.4 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል፡፡
በመሆኑም በተለያዩ የኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ለዳሸቀው ዓለም አፍሪካ ትልቅ ተስፋ ሆና እየታየች ነው፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ቀጥለዋል፡፡ ከዓለም አሥር ፈጣን ዕድገት አስመዝጋቢ አገሮች ስድስቱ አፍሪካውያን መሆናቸውም ትልቅ ግምትን ሲፈጥር ሰንብቷል፡፡ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ መምጣትን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡
የግብፆች ጥርጣሬ በኢትዮጵያ ላይ
ግብፅ ያስተናገደችው የዘንድሮ ስብሰባ ምንም እንኳ በአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ያተኮረም ቢሆን በተለይ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ ግንኙነት ላይ ትኩረት በማድረግ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ሲሰጡ ታይተዋል፡፡ በተለይ ቅዳሜ በተካሄደው የመሪዎቹ ስብሰባ ወቅት ትኩረትን ስቦ የነበረው የሦስቱ አገሮች ውይይት እንደነበርም ታይቷል፡፡
ግብፆች በድፍኑ ሊባል በሚችል መልኩ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን ልትዘጋ ነው የሚል መሠረታዊ ድምዳሜ የሚያንፀባርቁ ይመስላሉ፡፡ ከተራ ታክሲ ሾፌር እስከ ትልልቆቹ ምሁራን ድረስ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ መሥራቷ ኤሌክትሪክ አመንጭታ ኤክስፖርት ለማድረግ ያለመ ፕሮጀክት መያዟን፣ በአንፃሩ ግብፃውያን ግን የሚጠጡት ውኃና ህልውናቸው የዓባይ ወንዝ መሆኑን በመተንተን ተጠምደዋል፡፡
በግብፅ ከሚታተሙ ጋዜጦች መካከል አንዱ የሆነው ኢጂፕት ኢንዲፔንደት ጋዜጣ ድረ ገጽ በኢትዮጵያ ግድብ የተነሳ የውኃ እጥረት እየተፈጠረ ስለሆነ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ የሚያትት ዘገባ አሠራጭቷል፡፡ ‹‹የውኃ እጥረት የተፈጠረው በህዳሴው ግድብ ምክንያት በመሆኑ መዘጋጀት ይገባናል፤›› ብለዋል ሲል ጋዜጣው የጠቀሳው ማሕሙድ ራስላም የተባሉ የግብፅ የውኃና የፍሳሽ ቆሻሻ ኩባንያ ዋና ኃላፊ ናቸው፡፡
እርግጥ እንዲህ ያሉት እሮሮዎች መስተጋባትና ከኢትዮጵያ ጋር መያያዝ የጀመሩት የግብፅ መንግሥት የመጠጥ ውኃና የኤሌክትሪክ ፍጆታ ታሪፍ ላይ ጭማሪ ማድረጉን ባስታወቀ ማግሥት መሆኑን የዘገባው ሐተታ ይጠቁማል፡፡ ኢትዮጵያ በአንፃሩ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ግብፅ ከዓባይ ወንዝ የምታገኘውን የውኃ መጠን እንደማይቀንስባት ደጋግማ ስታስታውቅ መቆየቷንም ጋዜጣው አስነብቧል፡፡
የግብፅ ጋዜጦችና ሌሎቹም መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የሚያስከትለው የውኃ መጠን መቀነስ የሚገነዘቡትም አይመስልም፡፡ ከዘገባቸው አኳያ፣ በአገሪቱ 12 ከመቶ የሚቆጠር ሕዝብ ውኃ በማጣቱ ምርቱ መጥፋቱን፣ የዓባይ ገባሪዎችም የውኃ መቀነስ ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም የሚነግራቸው ያለ አይመስሉም፡፡
ምንም እንኳ እንዲህ ያሉ ኢትዮጵያ ዓባይን ገድባለች፣ ውኃውን ቀንሳለች የሚሉ ፕሮፓጋንዳዎች ቢበራከቱም፣ ስለ ሕዝቡ ግን የተለየ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ አምባሳደር ማሕሙድ የግብፅ ሕዝብን የሚገልጹትም እንዲህ ሲሉ ነው፡፡
‹‹የግብፅ ሕዝብ በጣም ጨዋ ነው፡፡ ከታሪኩ፣ ከሥልጣኔው ጋር በተያያዘ ጨዋ ሕዝብ ነው፡፡ በቀልድም ይሁን በምር የውኃ ጉዳዮችን ያነሳል፡፡ ማወቅ ያለብን ግን ለሰላሳ ዓመታት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ለሚወስዱ የፕሮፓጋንዳ መልዕክቶች ተጋልጦ የኖረ ሕዝብ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ከተረዳን በምን መልኩ ከዚህ ደረጃ ወጥተን ወደ መግባባት የምንደርሰው ለሚለው የራሳችንን አጀንዳ በሚገባ በማስረዳት ነው፡፡››
ከዚህ ባሻገር ግን ‹‹በባህል ግንኙነት፣ በሕዝብ ለሕዝብ ትብብሮሽ ካለመተዋወቅና ከጨለማ ወደ ብርሃን እንወጣለን ብዬ አምናለሁ ምክንያቱም ባህል ትልቅ መሣሪያ ነውና፡፡ እስካሁን ግን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፤›› ያሉት አምባሳደር ማሕሙድ፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ልዑካን በግብፅ ያደረጉትን ጉብኝት ተምሳሌት አድርገዋል፡፡ እንዲህ ያሉት እንቅስቃሴዎች በመጠኑም ቢሆን ለውጥ ለማምጣት ስላስቻሉ ደጋግሞ ማካሄድ እንደሚጠቅም ገልጸዋል፡፡
ግብፆች ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያላቸውን ፍራቻና ሥጋት ለመቅረፍም ወደ ግድቡ ግንባታ ስፍራ በማቅናት ቢጎበኙ፣ እውነታውን ይበልጥ ሊረዱት እንደሚችሉ አምባሳደሩ ሲያስረዱ ይህንን ተናግረዋል፡፡
‹‹ግድቡ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ የሚገነባበት አይደለም፡፡ በተለይ ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ ምሁራንና የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ ይቀርጻሉ ተብለው የሚታመኑት ሄደው ቢያዩ በመሃል ያለው የኃይድሮ ፖለቲካው ፕሮፓጋንዳ በራሱ ጊዜ ይጠፋል ብዬ አምናለሁ፡፡››
ይሁን እንጂ በግብፅ ዘንድ ያለው እውነታ ለዚህ ብዙ የሚቀረው ይመስላል፡፡ በቅርቡ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን ለመዘገብ አዲስ አበባ ከተገኙ የግብፅ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ በአዲስ አበባ ስላስገረማትና ስለዓባይ ግድብ ያለውን የሕዝቡን አስተያየት በፌስቡክ ገጿ በማስፈሯ፣ እዚያው አዲስ አበባ ሳለች ከሥራ መባረሯን የሚናገሩ ተባራሪ ወሬዎችን በምንሰማበት አጋጣሚ ወቅት ከግብፃውያን ጋር የሚደረገው ግጥሚያ ቀላል እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ ይሁንና ከመሪዎች እስከ ሕዝብ ለሕዝብ ባለው ደረጃ ንግግር መዘውተሩ ቀቢጸ ተስፋን አጭሯል፡፡