[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- ሪፖርቱ ነዋ፡፡
- የትኛው ሪፖርት?
- ሰሞኑን የወጣው፡፡
- በምን ላይ?
- በሕገወጥ ዝውውር፡፡
- የሕገወጥ ዶላሩን ነው?
- እ…
- ለእነዚህ ኒዮሊብራሎች ግን የት እንሂድላቸው?
- ምን እያሉ ነው?
- ዶላር ከአገር ሸሸ ነው የሚሉት?
- ኧረ እኔ ሕገወጥ የሰው ዝውውሩን ነው የምልዎት፡፡
- እእእ…
- ምነው ደነገጡ?
- የምን ሕገወጥ ዝውውር ነው?
- በአፍሪካ ቀንድ የሚደረገው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነዋ፡፡
- ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተባለ እንዴ?
- በዚህ ወንጀል ላይ ባለሥልጣናትም ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
- እኛ?
- አይ የለም የኤርትራ ባለሥልጣናትን ነው፤ ምነው ደነገጡ?
- እኔን ያልከኝ መስሎኝ ነዋ?
- እርስዎማ በዚህኛው ዝውውር መቼ ይጠረጠራሉ?
- በየትኛው ዝውውር ነው የምጠረጠረው?
- እ…
- ለመሆኑ ምንድን ነው ባለሥልጣናቱ የሚያደርጉት?
- ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ከአገራቸው እንዲፈልሱ ያደርጋሉ፡፡
- እኮ ለምን?
- ዶላር ለማግኘት ነዋ፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- በቃ ከሰዎቹ ዶላር ይቀበላሉ፡፡
- ዕቃ ኤክስፖርት ማድረግ ሲያቅታቸው ሰው ኤክስፖርት ማድረግ ጀመሩ ማለት ነው?
- እንደዚያ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዘዴኛዎች ናቸው ባክህ፡፡
- እንዴት?
- ያው በተዘዋዋሪም ቢሆን እያገኙት ነዋ፡፡
- ምኑን?
- ዶላሩን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይህ እኮ ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡
- ማነው ያለው?
- የሰዎች ዝውውር እኮ ነው፡፡
- ቢሆንስ?
- ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ይኼ የኒዮሊብራሎች ትምክህት ነው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- እነሱ በገንዘብ ሰው ያዘዋውራሉ አይደል እንዴ?
- መቼ ነው ያዘዋወሩት?
- ይኼው እግር ኳስ ተጫዋቾቹ ከአንድ ክለብ ወደ ሌላው ክለብ በከፍተኛ ገንዘብ አይደል እንዴ የሚዘዋወሩት?
- እሱ እኮ ሕጋዊ ነው፡፡
- ይኼኛውስ?
- ሕገወጥ ነዋ፡፡
- ለምን እኛ አንሞክረውም ግን?
- ምኑን? ዝውውሩን?
- ሕጋዊ ዝውውሩን፡፡
- በኳስ ተጨዋቾቻችን?
- በእነሱ ሳይሆን በአትሌቶቻችን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አያውቁም እንዴ?
- ምኑን?
- በአትሌት ስም ስንቱ በርካታ ገንዘብ እየከፈለ ከአገር እንደሚወጣ፡፡
- ምን?
- ትንሽ ዘገዩ፡፡
- ለምኑ?
- ለዚህኛው ቢዝነስ፡፡
- እንዴት?
- በሌሎች ተቀድመዋል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ቦታ ከሾፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]
- እዚህ ጋ አቁም!
- ኧረ አይቻልም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምንድነው የማይቻለው?
- የተከለከለ ቦታ ነው፡፡
- ማን ነው የከለከለው? አቁም!
- ኧረ የእንጀራ ገመዴን ያስበጥሱብኛል፡፡
- ከእኔ ውጪ ማን ነው የአንተን የእንጀራ ገመድ የሚበጥሰው?
- አዲስ ሕግ ወጥቷል፡፡
- ምን የሚል?
- ተደጋጋሚ ጥፋት ያጠፋ ይቀማል የሚል፡፡
- ምኑን ነው የሚቀማው?
- መንጃ ፈቃዱን?
- መፍጃ ፈቃዱን ነው ያልከኝ?
- በሉት፡፡
- በል አሁን አቁም፡፡
- ኧረ ይኼ ሦስተኛ ቅጣቴ ነው የሚሆነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሕጉን ያወጣነው እኛው አይደለን እንዴ?
- የሚተገበረው እኛ ላይ ነዋ፡፡
- እንዲያውም ትራፊኩ ያውና ንገረውና አቁመው፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ትራፊኩን ክላክስ አድርጐ ጠራው]
- እዚህ ጋ ላቁም?
- አዲስ የወጣውን ሕግ ታውቃለህ አይደል?
- በሚገባ፡፡
- እዚህ ጋ ላቁም ብለህ በማሰብህ ራሱ ልቀጣህ እችላለሁ፡፡
- ይቅርታ እንግዳ ስለያዝኩ ነው፡፡
- አይደለም እንግዳ ለምን ባለሥልጣን አትይዝም?
- ምን አልከኝ?
- የእንጀራ ገመድህን እንዳልበጥስልህ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከኋላ የመኪና መስታወታቸውን አወረዱት]
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- እዚህ ጋ አንድ ቀጠሮ ነበረኝ፡፡
- ምን ላድርግልዎት ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
- እዚህ ጋ ብናቆም ብዬ ነው፡፡
- አይደለም ማቆም አዝለህ ውሰደኝ ቢሉኝ አልወስድዎትም እንዴ?
- እንዲህ ነው እንጂ፡፡
- ሊጋልቡኝ ይችላሉ ስልዎት፡፡
- እሱን ሌላ ጊዜ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔም እፈልግዎት ነበር፡፡
- ቢሮ ና፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋ ወሬያቸውን ቀጠሉ]
- እኔ እኮ አይገባኝም፡፡
- ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- የመልካም አስተዳደር ችግር አለ የሚባለው፡፡
- እንዴት?
- ከዚህ በላይ መልካም አስተዳደር አለ?
- መልካም አስተዳደር ያለው እኮ ለእኛ አይደለም፡፡
- ለማን ነው ያለው ታዲያ?
- ለእናንተ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀጠሯቸው የውጭ ዜጐች ጋር ተገናኙ]
- ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር ብዙ ሥራ መሥራት እንፈልጋለን፡፡
- የሚሠራን ሰው እናበረታታለን፡፡
- አገራችሁን እንደ አገራችን ለማሳደግ ቆርጠን ተነስተናል፡፡
- አገራችሁ አድጋለች እንዴ?
- ለዓለም ሁሉ ዕቃ የምናቀርበው እኛ አይደለን እንዴ?
- ለነገሩ እውነታችሁን ነው፡፡
- እዚህ አብዮት ማስነሳት ነው የምንፈልገው፡፡
- ኒዮሊብራሎች ናችሁ እንዴ? የምን አብዮት ነው?
- የለም የለም፤ የገበያ አብዮት ነው የምልዎት፡፡
- እሱኛውን አብዮት ማስነሳት ትችላላችሁ፡፡
- አገሪቷን እናስመነድጋታለን ስልዎት፡፡
- ለልማት በራችን ክፍት ነው፡፡
- አንዳንድ ነገሮች ግን አስቸግረውናል፡፡
- ምን ዓይነት አንዳንድ ነገሮች?
- ቀረጥና ፈቃድ ማውጣት የመሳሰሉት፡፡
- ያስቸገሯችሁ ከሌላ ጋር እየሠራችሁ በመሆኑ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ወሳኝ መሆንዎት ገብቶን እኮ አሁን ወደ እርስዎ የመጣነው?
- ቢሆንም ዘግይታችኋል፡፡
- አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች አሳስተውን ነው፡፡
- ለማንኛውም እነዚህን ነገሮች እኔ እጨርሳቸዋለሀ፡፡
- ምን እናድርግ ታዲያ?
- በአስቸኳይ እንፈራረማ፡፡
- ስለእሱ አያስቡ፤ አሁኑኑ ድርጅቱን እንመሠርታለን፡፡
- እኔም ሌላውን እጨርሳለሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር…
- አቤት፡፡
- ልንሠራው ያሰብነው ቢዝነስ ግን ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀደ ነው፡፡
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- እኛ የውጭ አገር ዜጐች ነና፡፡
- ኢትዮጵያውያን ትሆናላችኋ፡፡
- እንዴት?
- በእኔ በኩል!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ቁጭ ብለው በሞባይላቸው ካንዲ ክራሽ የሚባለውን ጌም ሲጫወቱ ጸሐፊያቸው ገባች]
- ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ፈለግሽ?
- እንግዳ ይፈልግዎታል፡፡
- ሥራ ይዟል በይ፡፡
- ኧረ ስድስት ወር ሙሉ ሲመላለስ ነበር፡፡
- በቃ ሌላ ስድስት ወር ይጠብቃ፡፡
- ምን እየሠሩ ነው ግን?
- ከባድ ሥራ ይዣለሁ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ካንዲ ክራሽ እየተጫወቱ ነው እንዴ?
- ትጫወቻለሽ እንዴ አንቺም?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት አዕምሮ የሚያሠራ ጌም መሰለሽ?
- አውቃለሁ ስንተኛው ሌቭል ላይ ነዎት?
- 100 ደርሻለሁ፡፡
- እርስዎና ኢሕአዴግ ግን ይኼን ቁጥር ትወዱታላችሁ፡፡
- የቱን ቁጥር?
- 100!
[ክቡር ሚኒስትሩ የጌሙን ሌቭል ማለፍ አቅቷቸው ተክዘው ቁጭ ብለው ሚስታቸው መጡ]
- ምን ሆነህ ነው የተከዝከው?
- ኧረ ተይኝ እባክሽ፡፡
- ምን ሆንክ?
- ማደግ አቃተኝ እኮ፡፡
- ያቺ 11 ፐርሰንቷ ቀረች እንዴ?
- እሷማ እንደቀጠለች ነው፡፡
- የሥራ ዕድገት ጠየቅክ እንዴ ታዲያ?
- ሕይወት ተቀጥፎብኝ ነው፡፡
- ምን ሆነሃል ሰውዬ? ሁላችንም ሰላም ነን እኮ፡፡
- አይ እኔ መቼ የእናንተ ሕይወት አሳሰበኝ?
- የማን ሕይወት ነው ያሳሰበህ ታዲያ?
- የጌሙ ነዋ፡፡
- የምን ጌም?
- ምን ይቺ ልጅሽ ጊዜ ሲኖርህ ተጫወተው ብላ አንድ ጌም አሳይታኝ ይኸው ሱስ ይዞኝ አርፏል፡፡
- ጌም ነው ያልከኝ?
- አዎን፡፡
- ሥራውን ትተህ ጌም?
- እንዴት ጭንቅላት የሚጠይቅ ጌም መሰለሽ?
- ምን የሚሉት ጌም ነው?
- ካንዲ ክራሽ፡፡
- በል ተጠንቀቅ፡፡
- ምኑን?
- አንተ ካንዲ ክራሽ ስታደርግ …
- እ…
- አንተ ራስህ ክራሽ እንዳትደረግ፡፡
- በማን?
- በሕዝቡ!