- ሁለት ተገድለዋል
የኤርትራ ታጣቂ ኃይሎች በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ላይ ከነበሩ መካከል 85 ኢትዮጵያውያንን ጠልፈው ወሰዱ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ የገቡበት አልታወቀም፡፡
በቅርቡ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ (ትግሪኛ ፕሮግራም) የዓይን እማኞችን አነጋግሮ እንደዘገበው፣ በትግራይ ክልል ወረዳ ከፍተኛ ሑመራ በተለይ ልዩ ስሙ ፅርጋ ግርማይ በተባለው አካባቢ በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ላይ ከነበሩት 400 ሰዎች መካከል 85 ሰዎች ተጠልፈው ተወስደዋል፡፡
አፋኞቹ የኤርትራ ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱና ትግርኛ የሚናገሩ መሆናቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በቀትር እንደሆነና በርከት ያሉ የታጠቁ ወታደሮች መጥተው ወርቅ በማውጣት ላይ የነበሩትን በመክበብ የተወሰኑትን ለይተው በመረብ ወንዝ እንዲሻገሩ እንዳስገደዷቸው ገልጸዋል፡፡
በተለይ ከአፈናው ማምለጡን የሚናገረው ኃለፎም ግርማይ የተባለው ወጣት እንደሚለው፣ ከመካከላቸው ለማምለጥ የሞከረው አንዱ በወታደሮቹ ተተኩሶ ሲገደል፣ ሌላ ሊያመልጥ የሞከረ ታጋች መረብ ወንዝ ውስጥ ገብቶ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡
የኤርትራ የፀጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ መሰል ድርጊት እንደሚፈጽሙ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡ በተለይ በ2004 ዓ.ም. ወርቅ በማውጣት ላይ የነበሩ ከ140 በላይ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ተጠልፈው መወሰዳቸው ይታወሳል፡፡
የተጠለፉት ግለሰቦች በሕይወት ይኑሩ አይኖሩ ምንም መረጃ የለም፡፡ የትግራይ ክልል መንግሥትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ዝምታ መርጠዋል፡፡ ሪፖርተር ድርጊቱን በተመለከተ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ስለጉዳዩ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡