ለአገር ውስጥ አምራቾች ቅድሚያ ተሰጥቶ ግዥ እንዲፈጸም በቃል የተሰጠ ትዕዛዝ ብቻ በመቀበል፣ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ የአርማታ ብረት ግዥ ሲፈጽሙ የቆዩ ኃላፊዎች ያደረባቸውን ሥጋት በተደጋጋሚ በመግለጻቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የቃል ትዕዛዙን በጽሑፍ የሚቀይር መመርያ አወጣ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በጽሑፍ ባስተላለፉት መመርያ፣ መንግሥት የሚፈጽማቸው ግዥዎች ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ያደሉ እንዲሆኑ አዘዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ መመርያ በፌዴራል ደረጃ የመንግሥትን ግዥ ለሚያከናውነው የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎትና ለአዲስ አበባ አስተዳደር የተላለፈ ሲሆን፣ በቃል ትዕዛዝ ብቻ ግዥ ሲፈጽሙ የቆዩት የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ኃላፊዎች የመመርያውን መውጣት በአዎንታዊ ጎኑ እንዳዩት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹እጅግ ጠቃሚና መሠረታዊ ውሳኔ ነው፤›› በማለት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ተቋማት በቀጥታ ትዕዛዝ የሚቀበሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሚመራው ኮማንድ ፖስት ነው፡፡ ከንቲባ ድሪባ ኩማና ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ ስጦታው በተለያዩ መዋቅሮች የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶችን በቅርብ ይከታተላሉ፡፡
የፌዴራል መንግሥት የአገር ውስጥ ፋብሪካዎችን ለማበረታታት በተለይ አርማታ ብረት አገር ውስጥ ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ በቃል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህ የቃል ትዕዛዝ ከመንግሥት የግዥ ሕግጋት ጋር የሚጋጭ ቢሆንም፣ የቤቶች ልማት ኃላፊዎች ትዕዛዙን በመቀበል የ1.6 ቢሊዮን ብር አርማታ ብረት ግዥ መፈጸማቸውን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ በግልጽ ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ኃላፊዎቹ ጨምረው እንደገለጹት ከበላይ አለቆች በጽሑፍ ሳይሆን በቃል ትዕዛዝ እንደሚሰጣቸው ጠቁመው፣ ይህ አሠራር ሕጋዊ ባለመሆኑ ሰርኩላር እንዲተላለፍላቸው ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሕገወጥ ግዥ እየተፈጸመ መሆኑ ጥቆማ ደርሶት ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ምርመራ ለመጀመር ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ መረጃ መውሰዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ይህ የፀረ ሙስና ኮሚሽን አካሄድ ያሳሰባቸው የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዎች፣ ሰርኩላር እንዲወርድላቸው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ በመሩት ስብሰባ ላይ ጠይቀዋል፡፡ በመጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መመርያ በማስተላለፋቸው ሥጋት ላደረባቸው ኃላፊዎች ዕፎይታ ሰጥቷል ተብሏል፡፡
መንግሥት ይህንን ሰርኩላር በጥልቀት ለመጠቀም የሚያስችል የግዥ ሕግጋት ማሻሻያዎችን አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ መሠረት ቀደም ሲል የአገር ውስጥ አምራቾች ከውጭ በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ 35 በመቶ እሴት ጨምረው ካቀረቡ 15 በመቶ ልዩ የዋጋ ጥቅም እንዲያገኙ ደንግጎ ነበር፡፡
በተዘጋጀው አዲስ ማሻሻያ ተጨማሪ እሴቱ ከ35 በመቶ ወደ 20 በመቶ ዝቅ ማለቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለአገር ውስጥ አቅራቢዎች መንግሥት የሚያወጣው ጨረታ እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ ከዘለለ ዓለም አቀፍ ጨረታ ይወጣል፡፡ በተሻሻለው መመርያ ግን ለአገር ውስጥ አቅራቢዎች እስከ 150 ሚሊዮን ብር ድረስ ከፍ እንዲል ማሻሻያ ቀርቧል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ማሻሻያዎች በአሁኑ ወቅት ፀድቀው ሥራ ላይ ባለመዋላቸው አምራቾች ቅሬታ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
የአገር ውስጥ አምራቾች ከሚያቀርቡት ቅሬታ መካከል የመንግሥት የግዥ ፖሊሲ ለአገር ውስጥ ያደላ እንደሚሆን ቢገለጽም፣ በተለያዩ የአሠራር መሰናክሎች የብረት አቅርቦቱን የውጭ ኩባንያዎች እየተቆጣጠሩት ነው የሚል ነው፡፡
ይኼም የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ከአቅማቸው በታች እንዲሠሩና ሠራተኞቻቸውም እንዲበተኑ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው የሕንፃ ዕቃዎች አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ሐጎስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት የአገር ውስጥ ፋብሪካዎችን የሚደግፍበት ሕግጋት በቶሎ አፅድቆ ሥራ ላይ ማዋል አለበት፡፡
አቶ ፋንታሁን እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት በተለይ ብረት አምራቾች የአቅማቸውን ያህል ማምረት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በበቂ ሁኔታ ገበያ ባለመፍጠሩ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ ነው፡፡
‹‹መንግሥት ከአምራቾቹ ጋር በቅርበት እየተነጋገረ በሕጉ መሠረት ግዥ የሚፈጽም ከሆነ አገሪቱ በርካታ ጥቅም የምታገኝ ከመሆኑም በላይ በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ይቻላል፤›› በማለት መንግሥት ለአገር ውስጥ ብረት አምራቾች ትኩረት እንደሚሰጥ አቶ ፋንታሁን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡