የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር ዘርፍ ላይ እያከናወነ ባለው ምርመራ፣ የሊዝ ግምቱ 22 ሚሊዮን ብር የሆነ መሬት ከሊዝ ውጪ ያስተላለፈ የመሬት አስተዳደር ሠራተኛ እንደሚገኝበት መረጃዎች አመለከቱ፡፡
ከፀረ ሙስና ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለኮሚሽኑ በቀረበ ጥቆማ መሠረት በተደረገው የመጀመርያ ምርመራ የሊዝ ግምቱ 22 ሚሊዮን ብር የሆነ ቦታ ከሊዝ ውጪ በመፈቀዱ መንግሥት ሊያገኘው የሚገባውን ገቢ ማጣቱ እንደተደረሰበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የተጠረጠረውን ግለሰብ ማንነት፣ የሥልጣን ደረጃና በየትኛው ክፍለ ከተማ የተፈጠረ መሆኑን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ጉዳዩ ገና በምርመራ ደረጃ ላይ በመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ከ4,500 ካሬ ሜትር በላይ የሆነ መሬት ያላግባብ ወረው በያዙና በፀደቀላቸው ሠራተኞች ላይ የተለያ ምርመራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም፣ ከሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ በፀደቀው የሊዝ አዋጅ መሠረት መሬት ማስተላለፍ የሚቻለው በሊዝና በምደባ ነው፡፡ በምደባ የሚተላለፈው ለኢንዱስትሪ፣ ለሃይማኖት ተቋማትና ለሌሎች አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፍላጎቶች ነው፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር በማዕከልና በክፍላተ ከተሞች ውስጥ በመሬት ልማትና በማኔጅመንት መዋቅሮች በሚሠሩ 600 ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን ሰሞኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ለአብነት ያህል በማዕከል ደረጃ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር በሚገኙ ሰባት ኤንሲዎች ውስጥ ከሚሠሩ ሠራተኞች መካከል፣ በ43 ያህሉ ላይ ዕርምጃው እንደተወሰደ ለማወቅ ተችሏል፡፡