Tuesday, October 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለኦሮሚያ ክልል ችግሮች ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ ይሰጣቸው!

ለወራት መፍትሔ ያልተገኘለት የኦሮሚያ ክልል ሁከት የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ አካል እያጎደለና ንብረት እያወደመ ቀጥሏል፡፡ ተረጋጋ ሲባል እያገረሸበት ነው፡፡ ችግሮች ሲከሰቱ በሰከነና በሚያግባባ መንገድ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ በኃይል የታጀቡ ግብግቦችና አላስፈላጊ ጥፋቶች እየበዙ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች የሚከሰቱት ደግሞ ለዓመታት ሲድበሰበሱና እንደሌሉ ተቆጥረው ችላ ስለሚባሉ በመሆኑ፣ የታመቀው ሲገነፍል ለማቆም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከሥር ከመሠረቱ በአግባቡ ተነጋግሮና በችግሮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ፣ በመታየት ላይ ያለው የሰው ሕይወት ቅስፈት ነው፡፡ የሰላምና መረጋጋት መጥፋት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሥፍራዎች ለሚታዩ ችግሮች ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ ዋና ዋና የሚባሉትን እንያቸው፡፡

ሰላማዊ የሆነ ከባቢ መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ከአገር ሽማግሌዎችና ኅብረተሰቡን በተለያዩ መስኮች ከሚወክሉ አካላት ጋር መሠረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ግልጽና አሳታፊ የሆነ መድረክ ያዘጋጅ፡፡ በመንግሥትም ሆነ በፖለቲካ ድርጅቱ ላይ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች ድምፅ ተሰምቶ  የሕዝቡ ፍላጎት በግልጽ ይታወቅ፡፡ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች ረቂቅ የጋራ ማስተር ፕላን ላይ የነበረው ተቃውሞ ከተሰማ በኋላ፣ ረቂቅ ማስተር ፕላኑ ተሰርዞ እንደገና አመፅ ሲያገረሽ ችግሩ ምን እንደሆነ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ከማስተር ፕላኑ ስረዛ በኋላ የቀሩ ነገሮች ካሉ ፍርጥርጥ ብለው መነገር አለባቸው፡፡ ከፊት ለፊትም ሆነ ከበስተጀርባ ያሉ ጉዳዮች ይታወቁ፡፡  

የክልሉ መንግሥት በዋነኝነት ለችግሩ መፍትሔ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ላለፉት አራት ወራት የዘለቀው ብጥብጥ የአገሪቱን ትልቅና ከ35 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርበትን ክልል ሲያምስ፣ ከዚያ አልፎ ተርፎ በአገር ደረጃ አሳሳቢነቱ ጎልቶ ሲወጣ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይቻልም፡፡ ይልቁንም በተደጋጋሚ መግለጫ ከማውጣትና ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዳልሆኑ ከመግለጽ ይልቅ፣ በየጊዜው አድማሱን እያሰፋ ያለው ችግር መፍትሔ የሚያገኝባቸውን አማራጮች ማየት ተገቢ ነው፡፡ ከሰላማዊ ሠልፈኞች አልፎ የፀጥታ ኃይሎች ጭምር እየሞቱ ነው ሲባል በየአካባቢው የጦር ቀጣና የተመሠረተ ይመስላል፡፡ ይህንን ዓይነቱን አድማሱ እየሰፋ የመጣን ሁከት በኃይል ብቻ ለማቆም መሞከር አደጋው የከፋ ነው፡፡ ይልቁንም ለሰላማዊ መፍትሔ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ይበጃል፡፡ ሞትና ጉዳቱ እየከፋ በሄደ ቁጥር አደጋውም እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ከዚህ ቀደም በክልሉም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የሚሠሩ ነባር ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ከሕዝብ ጋር በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፣ በየደረጃው ካሉ አደረጃጀቶችና የሥርዓቱ ደጋፊዎች ጋር ብቻ የሚደረግ ውይይት ዋጋ የለውም፡፡ የሕዝቡን የልብ ትርታ ለማዳመጥ ከተፈለገ ከአደረጃጀት ውጪ ያለውን የሕዝብ ፍላጎት የማወቅ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ አደረጃጀቶች ውጤታማ ቢሆኑ ኖሮ ከተቃውሞው ባልተናነሰ ሁኔታ የእነሱም ድምፅ ይሰማ ነበር፡፡ የክልሉን መንግሥትም ሆነ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦሕዴድ አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸውን ችግር በግልጽ አምነው፣ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች የሚሰጡት ምላሽ ፍላጎቶችን መሠረት ያድርግ፡፡ የአመራር ክህሎትና ብቃት ችግርም ከሆነ በየደረጃው ያሉ መዋቅራቸውን ይፈትሹ፡፡ የተቀባይነት ደረጃቸውንም ኦዲት ያስደርጉ፡፡ ይህ የፌዴራሉን መንግሥትንም ሆነ ገዥውን ፓርቲ ኢሕአዴግን ጭምር ይመለከታል፡፡

መንግሥት በሕዝብ ተመርጦ በመሥራት ላይ እንደሆነ ሲናገር የመረረ ተቃውሞ ከተነሳበት፣ ሥር የሰደደ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በተለይ በምርጫ 2007 መቶ በመቶ የፓርላማውን መቀመጫዎች በቁጥጥር ሥር ያዋለ መንግሥት፣ በወራት ጊዜ ውስጥ ኃይል የተቀላቀለበት ተቃውሞ ከገጠመው የችግር አፈታቱን ዘዴ ማወቅ አለበት፡፡ ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን በመከተል በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕዝብ ዘንድ ምን እንደተፈጠረ ሊያውቅ ይገባል፡፡ በግልጽም ማወቅ አለበት፡፡ አለበለዚያ በየቦታው የተነሱ ተቃውሞዎች እየበረቱ በሄዱ ቁጥር በዓረብ የፀደይ አብዮት ወቅት ያጋጠሙ ዓይነት ቀውሶች ይከሰታሉ፡፡ ግብፅን ከወታደራዊ አምባገነን ወዳልተረጋጋች ወታደራዊ አገዛዝ፣ ሊቢያን ወደበለጠ ትርምስና እልቂት፣ ሶሪያንና የመንን ወደ እልቂትና ውድመት የከተተው ዓይነት መከራ እንዳይከሰት በአስቸኳይ ሁሉንም ወገን የሚያግባባ መፍትሔ ይፈለግ፡፡ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ገና በማራገፍ ላይ ያለች አገር የሚያንኮታኩታትና ሕዝቧንም ለበለጠ ስቃይ የሚዳርግ ነውጥ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ይፈለግ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ የሚታዩትን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት፣ የንግድና የግብርና እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዝ፣ ዋይታዎች፣ ሥጋቶችና የመሳሰሉትን ማስወገድ የሚቻለው ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰላማዊ ተቃውሞዎች በሚገባ እንዲሰሙ፣ በትጥቅ የሚደገፉ ካሉ በሕግ እንዲዳኙ፣ በመሣሪያ የተደገፉ መንግሥታዊ ምላሾች እንዳይኖሩ፣ መብቶቻቸውን በመጠየቃቸው ምክንያት ብቻ የታሰሩ ካሉ እንዲፈቱ፣ ሕገወጦች በሕግ እንዲጠየቁ፣ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከፈቱ፣ መደበኛ ተግባራት በሰከነ መንገድ እንዲከናወኑ፣ የደረሱት ጥፋቶች በገለልተኛ ወገኖች እንዲጣሩና የመሳሰሉትን ለማስፈጸም የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል አመፁን በተለያዩ መንገዶች በማፋፋም በእሳት ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፉ ወገኖች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ ወጣቶችንና ሕፃናትን ሳይቀር ከአደጋ ጋር እያጋፈጡ በሥርዓት የማይመራ ብጥብጥ ማጋጋም ትርፉ ጥፋት ነው፡፡ ለሥልጣንና ከባዕዳን ለሚገኝ ጥቅማ ጥቅም ተብሎ አገር ማተራመስ ወንጀል ነው፡፡ ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ አመፆችን ማስፋፋት አደጋ አለው፡፡ ሕዝቡም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት መንግሥት ላይ ጫና ሲያደርግ፣ ኃላፊነት የማይሰማቸውንና ለሥልጣን ያሰፈሰፉትን ወገኖች ደግሞ መገሰጽና ማሳፈር አለበት፡፡

መንግሥት ሕገ መንግሥቱን በመጀመሪያ ራሱ ያክብር፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩትን መሠረታዊ መብቶች አክብሮ ያስከብር፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ መሆኑንና ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የይስሙላ ድርጊቶች ይብቃቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ያክብር፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያስተናግድ፡፡ ዜጎች በአገራቸው ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸው ይረጋገጥ፡፡ ለአገራቸው ጉዳይ ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸው በተግባር ይታይ፡፡ ጥቂቶች እየጠገቡ ብዙኃን አይቆራመዱ፡፡ አድርባዮችና አስመሳዮች በአገር ላይ አይቀልዱ፡፡ ሌብነትና ዝርፊያ ይቁሙ፡፡ ለብጥብጥና ለጥፋት በር የሚከፍቱ ድርጊቶች በአስቸኳይ መላ ይፈለግላቸው፡፡   

በሌላ በኩል ለሥልጣን ጥም ማርኪያ ሲባል በሕዝብና በአገር ላይ አደጋ የሚደቅኑ ወገኖች ከድርጊታቸው ይታቀቡ፡፡ በሕዝብ ብሶትና ምሬት ተከልለው በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ወገኖች፣ አገርን ለውድመት ሕዝብን ለእልቂት በመዳረግ ውጤት እንደማይገኝ ከእነ ሶሪያ ይማሩ፡፡ ለሥልጣን ብቻ ሲባል አገርን ማተራመስና ሕዝብን መከራ ውስጥ መክተት ተቀባይነት የለውም፡፡ በአጠቃላይ በግራም ሆነ በቀኝ የተሠለፉ ኃይሎች ሥልጣንን ለማስጠበቅ ወይም ሥልጣን ላይ ለመቆናጠጥ ሲሉ ሕዝብና አገርን መከራ ውስጥ ከመክተታቸው በፊት ቆም ብለው ያስቡ፡፡ የባዕዳንን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚራወጡም አደብ ይግዙ፡፡ የኦሮሚያ ከልልም ሆነ የመላ አገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሰላማዊ አማራጮችን ይመልከቱ፡፡ ሕዝቡም ቢሆን ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጥ በሁሉም ወገኖች ላይ ጫና ያድርግ፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለኦሮሚያ ክልል ችግሮች ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ ይሰጣቸው!      

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...