Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​በኢንቨስትመንት ስም ያስገቡትን የአርማታ ብረት ለገበያ ባቀረቡ 232 ባለሀብቶች ላይ ምርመራ ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኢቨስትመንት ምክንያት ያገኙትን የቀረጥ ነፃ መብት ተጠቅመው፣ ከውጭ ያስገቡትን የአርማታ ብረት በሸጡ 232 ባለሀብቶች ላይ ምርመራ ጀመረ፡፡

ባለሥልጣኑ ምርመራውን የጀመረው ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ባገኘው መረጃ ላይ ተንተርሶ መሆኑን  ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢቨስትመንት ባለሥልጣን የቀረጥ ነፃ መብታቸውን ከታለመለት ዓላማ ውጪ ያላግባብ ተጠቅመዋል ያላቸውን 11 ድርጅቶች ለባለሥልጣኑ ካሳወቀ በኋላ፣ ምርምራው መጠናከሩን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባለሥልጣኑ እያካሄደ ባለው ምርመራ 232 ባለሀብቶች በተለይም በሆቴል ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የቀረጥ ነፃ መብታቸውን ያላግባብ ተጠቅመዋል ተብለው ተጠርጥረዋል፡፡ እስካሁን በተደረገው ማጣራት ከ109 ሺሕ ቶን በላይ የአርማታ ብረት ከታለመለት የኢንቨስትመንት ዓላማ ውጪ ለገበያ በመቅረቡ፣ የአገር ውስጥ ብረት አምራቾች ላይም ሆነ ሕጋዊ አስመጪዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ምርምራው እየተደረገባቸው ካሉ ባለሀብቶችና ተባባሪዎቻቸው መካከል የባለሥልጣኑ ሠራተኞችም የሚገኙበት መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በመሆኑም ባለሥልጣኑ ምርመራውን በቅርቡ አጠናቆ ከባለሥልጣኑ ሠራተኞች ጋር የተመሳጠሩትን በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀል እንዲከሰሱ የምርመራ ፋይሉን እንደሚያስተላልፍና የተቀሩትን ደግሞ በራሱ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ክስ ሊመሠርትባቸው እንደሚችል ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን የቀረጥ ነፃ መብት ጥያቄን ተቀብሎና ገምግሞ በሚሰጠው የድጋፍ ደብዳቤ መሠረት፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቀረጥ ነፃ ጥያቄውን ፈቅዶ የሚያስተናግድበት ሕጋዊ አሠራር ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ሲባል ተዘርግቷል፡፡

በዚህ አሠራር መንግሥት በየዓመቱ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘት የሚገባውን ታክስ እንደሚያጣ የሚገመት ቢሆንም፣ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚዎች ግን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የቀረጥ ነፃ መብት ከተፈቀደ በኋላ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን በተመለከተ ኃላፊነት ያለው ተቋም ገቢዎችና ጉሙሩክ ወይም ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ሕጉ ላይ በግልጽ የተቀመጠ ባለመሆኑ፣ ቁጥጥር ለማድረግ ችግር መፍጠሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ባለፈው ጥቅምት ወር ለኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምክረ ሐሳብ፣ መንግሥት ኢቨስትመንትን ለመሳብ በፈቀደው የቀረጥ ነፃ መብት ሥርዓት ከሚያገኘው ጥቅም ይልቅ የሚያወጣው ገንዘብ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሊሸፍን እንደሚችል በመጥቀስ፣ የቀረጥ ነፃ መብት ሥርዓትን እንዲያጥፍ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች