Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የተወካዮች ምክር ቤት ክትትልና ግምገማ የፀረ ሙስና ኮሚሽንንና የአገርን ገጽታ ሳያበላሽ ይከናወን

  በእ.ይ.

  የፌዴራል የተወካዮች ምክር ቤት የተወሰኑ የሕግ፣ የፍትሕና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ተቋማት የሥራ እንቅስቀሴ ላይ የሱፐርቪዥን ሥራ በመሥራት ያቀረበውን ሪፖርት በሚዲያ ተከታትያለሁ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ ሕግ አውጪ ከመሆኑም በላይ፣ የአስፈጻሚ አካላትን የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ እረዳለሁ፡፡ በመሆኑም ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣት የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ካካሄደባቸው ተቋማት  ውስጥ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አንዱ ነው፡፡

  የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እኔ እስከማውቃው ድረስ የተለያዩ የሙስና መከላከልና መዋጋት ተግባራትን በማከናወን ውጤታማ ነው ከሚላቸው ተቋማት አንዱ ነው፡፡ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርቶችን ያስተምራል፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ይከላከል፡፡ የተመራጮች፣ የተሿሚዎችና የሚመለከታቸው ሠራተኞችን የሀብት ምዝገባ ያካሄዳል፡፡ ሕዝቡን ለፀረ ሙስና ትግሉ ያነሳሳል፡፡ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን በመቀበል ይመረምራል፣ ይከሳል፣ ያስቀጣል፣ የተመዘበረ ሀብት ያስመልሳል፡፡

  እንግዲህ ይህን ለመሥራትና ስኬታማ ለመሆን በተለያዩ ሙያ ደረጃ ላይ ያሉ ሠራተኞችን መቅጠር የግድ ነው፡፡ ተቀጣሪው ደግሞ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ደቡብ፣ ትግሬ፣ ወዘተ ተብሎ ሳይሆን የፌደራል ተቋም በመሆኑ በብሔርና በፆታ ሳይለይ ቀጥሮ ማሠራት ይጠበቅበታል፡፡ ተቀጣሪ ሠራተኞች መልዓክ ሳይሆኑ የኅብረተሰቡ አካል የሆኑ ናቸው፡፡ በኮሚቴው የቀረበው ሪፖርትም ይህን በመቃኘትና ከኮሚሽኑ ከሚገኘው ጠቃሜታ አንፃር ታይቶና ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ሚዛን የሚደፋውን ተለይቶ ቢቀርብ ነበር የተሻለ የሚሆነው፡፡ የኮሚሽኑን ጓዳን በደንብ ማወቅ ያስፈልግ ነበር፡፡ ላይ ላዩን በማየትና በስማ በለው ብቻ ሪፖርት ብሎ ማቅረብ ተገቢ አይመስለኝም፡፡

  በእርግጥ ሁሉም ዜጋ የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ውጤታማ ነው የሚል ዕምነት የለውም ከእኔ ጀምሮ፡፡ ምክንያቱም የተለያየ አመለካከት ያለቸው ዜጎች ስላሉ፡፡ የመጀመሪያው ፀረ ሙስና ኮሚሽን የኢሕአዴግ ነው የሚሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በኢሕአዴግ ላይ ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ኮሚሽኑ የድርጅቱ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ እሰር የሚሉትን የሚያስር፣ ልቀቅ የሚሉትን የሚለቅ ነው ብለው ያስባሉ፣ ያስወራሉ፡፡ ሁለተኞቹ ፋይዳ ያለው ሥራ አልሠራም፣ ሙስኞችን እያየ እንዳለየ ያልፋል፣ ባለሥልጣናት ሙስና ሲሠሩ ዝም ይላል፣ ባለሥልጣናት ሕንፃ ሲገነቡ ዝም ይላል፣ ከአገር አገር ይዞራሉ፣ ሙስና ይሠራሉ፣ ልጆቻቸውን ውጭ አገር ልከው ከፍለው ያስተምራሉ፣ የገቢያቸው ምንጭ ሙስና ነው፣ ስለዚህ አያስርም፣ አይከስም፣ ይፈራል፣ በጥቅምና በሙስና ላይ ትኩረት አድርጎ ነው የሚሠራው የሚሉ ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህ በጣም ብዙ ናቸው፡፡

  ሦስተኛዎቹ ኮሚሽኑ ራሱ ያለጠያቂ ሙስና የሚሠራ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ ለኮሚሽኑ ሌላ ኮሚሽን ማደራጃት ያስፈልጋል፡፡ ሙስኞችን ለመልቀቅ ጉቦ የሚቀበሉ ባለሙያዎች በውስጡ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ራሳቸው ምንጩ ያልተወቃ ሀብት ያፈራሉ፣ ዝም ይባላል፣ ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡ አራተኛው ኮሚሽኑ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ላይ እርካታ ያላቸው ዜጎች ናቸው፡፡ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርት በመስጠት፣ ሙስናን በመከላከል፣ የሙስና ወንጀሎችን በመመርመርና በመክሰስ ውጤታማ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ አምስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ስለኮሚሽኑ ምንም ዓይነት ስሜት የሌላቸው፣ የሚሠራውን የማያወቁና የራሳቸውን ኑሮ የሚኖሩ ዜጎች ናቸው፡፡

  ሙስና በመፈጸም በሕግ ሥር ያሉ ሰዎችና ቤተ ዘመዶቻቸው፣ ሙስናን ለመሥራት ያሰቡና የሚያስቡ፣ ሀብት ያፈሩና የበለፀጉ ሰዎችን እያዩ የሚናደዱ፣ ዓይናቸው የሚቀላ፣ ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ በመሆኑ ፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ ላይ ጭፍን ጥላቻ ያላቸው፣ በአምስተኛ ረድፍ (በድርጅቱ ውስጥ የድርጅቱን ካባ ለብሰው የሚሽሎኮሎኩና መረጃ ለጠላት የሚያቀብሉና የመንግሥትን እንቅስቃሴ በተመቻቸው አጋጣሚ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ) የሚሰለፉ ማለትም ኢሕአዴግን መስለው ለምድ ለብሰው ውስጥ ውስጡን የሚቦረቦሩ፣ ትምክህተኞች፣ ጠባቦች፣ አክራሪዎችና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ያላቸው ክፉ ሰዎች አሉ፡፡ ኮሚሽኑ የፈለገውን ያህል ይሥራ፣ የፈለገውን ያህል ሙስና የተመዘበረ ሀብት ያስመልስ ከማንቋሸሽ ወደኋላ የሚሉ አይደሉም፡፡ እያሉም አይደለም፡፡ ሌሎች በድርጅቱ ውስጥ ከለምድ ለባሾች ጋር አውቀውም ሆነ ሳያውቁ እንደ በግ የሚነዱ ጀሌዎችም ጥቃት ለማድረስ ይሯሯጣሉ፡፡ እንደማስታውሰው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አንዳንድ የተቃዋሚ ፖርቲዎች በዶክትሪን ሰነዶቻቸው ላይ በቅድሚያ ሊያፈርሱት ወይም ሊያስተካክሉ የሚፈልጉት ተቋም ቢኖር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አንዱ ነው፡፡

  በ1993 ዓ.ም. በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የመከፋፈል ወቅት ኮሚሽኑ በመቋቋሙ ከኢሕአዴግ ውስጥ አፈንግጠው የወጡትን ሰዎች ለማጥቃት ተባለ፣ ተወራ፣ ተርገበገበ፡፡ የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ የነበሩት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል ኃላፊ ከሥራ ከተሰናበቱ በኋላ እንዲመልሱ ተጠይቀው በመመለሳቸውና ኮሚሽኑ ኃላፊውን በመሻሩ ብዙ ተወራ፣ ተርገበገበ፡፡ ለምን ከጎኑ ያለው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እንዲህ አይወራበትም? በሌላ በኩል ደግሞ ኮሚሽኑ ከመንግሥት ኃላፊዎች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቀድሞውን የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊዎችን፣ ደላሎችንና የተወሰኑ ባለሀብቶችን፣ ወዘተ በሙስና ወንጀል እንዲከሰሱ አድርጓል፡፡ ያኔ ጠላትም ወዳጅም እሰይ፣ አሁን አንበሳ ሆነ ጥርስ አወጣ ብሏል፡፡ ኮሚሽኑን የሚጠላው እሰይ ያለው ከመንግሥት ጋር አያይዞ ሲሆን፣ ወዳጅ ደግሞ አገር ወዳድ በመሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ሀብትና ንብረት መዝብረው ከአገር ወጥተው የተሰወሩትን ከአገሮች በማስመጣት እንዲቀጡ አድርጓል፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ሊፈጸሙ የሚችሉ ምዝበራዎች ለማስቆም ችሏል፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ውጤት ነው፡፡ በርታ የሚያስብል ነው፡፡  እንዲህ ሲባል ግን ኮሚሽኑ የተፈለገውን ኃላፊነት በትክክል ተወጥቷል የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ብዙ መሥራት ይችል ነበር የሚል አመለካከት ስላለኝ፡፡ ሪፖርተርም እንዲሁ የተመቻቸ ሁኔታ ቢፈጠርለት ኖር ብዙ ሊሠራ ይችል ይሆናል፡፡

  ኮሚሽኑ ቅጥር ሲፈጸም የሠራተኛውን የበስተኋላ ሥነ ምግባር ጥናት በማካሄድ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ግን ሰዎች ናቸው፡፡ ዛሬ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሀብቶችን ጨምሮ ደላላ የሚሆኑባት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ የኮሚሽኑ ሠራተኞችም ቢሆኑ ከዚሁ ኅብረተሰብ የወጡና በኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ ናቸው፡፡ ገንዘብ ቀጥ ብሎ በደላላ ሲመጣላቸው ይተውታል የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ገንዘብ ከመጣላቸው ይወስዳሉ፡፡ ጉቦ የሚፈጸመው በሁለት ሰዎች መካከል በሚፈጸም ስምምነት ስለሆነ ሲቀባበሉ ያየ በጥቆማ ካላስያዘ፣ ወይም አንድ ተቀባይ ወይም ሰጪ አፈንግጦ ወጥቶ ጥቆማ ካልቀረበ በደረሰኝ የማይወሰድ ገንዘብ ስለሆነ ይወስዳሉ የሚለው ከእኔም ጨምሮ አሉባልታ ነው እንጂ መረጃ የለም፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን እንዴት እየተቆጣጠረው ነው የሚለው ግን ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ የሱፐርቪዥን ሥራ ሠራን ያሉት ሰዎችን ይህን አጥርተው መልስ ባለማግኘታቸው ከሆነ እቀባለለሁ፡፡ ግን አይመስለኝም፡፡

  ሌላው የፍርድ ቤት ውሎ በፀረ ሙስና ላይ ያለው ድባብ ነው፡፡ ስንቶቻችሁ ፍርድ ቤት በመሄድ የፍርድ ቤት ውሎ እንደምትከታተሉ፣ ባላውቅም ፍርድ ቤት ውስጥ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎችና በደረቅ ወንጀል ላይ የፍርድ ሒደቱና በፍርድ ውሳኔ ላይ የሕዝቡን አመለካከት እስቲ እንየው፡፡ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ክርክር የሚያካሄድ ዓቃቤ ሕግን በጎሪጥ ሲያዩት ምን አልባት አንተ ምንህ ይጎዳል? ለምን አትተውም? የሚሉትን እኔ ራሴ በጆሮዬ መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሴት የደፈረ ወይም ሰው የገደለ ሰው ላይ ተከራካሪውን ምን ይሉታል? ይህን መግደል ነው፣ የሞት ፍርድ ሊሰጥ ይገባል፣ ወዘተ ነው የሚሉት፡፡ ዳኛው የፍርድ ውሳኔ ሲሰጥ ፍርድ ቤቱ በእልልታ ይቃልጣል፡፡ የሙስና ወንጀል ተጠቂ ሰው ደጋፊ እንደሌለው እኔም የተረዳሁት ዘግይቼ ነው፡፡ ዳኛው፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግና የሙስና ተጠርጣሪ ወገን ጠበቃ ጓደኛሞች እንደሚሆኑ የሱፐርቪዥን ሰዎች ተረድተውት ይሆን?

  ኮሚሽኑ ለምን ምክር ይሰጣል? ለምን ሁሉንም እስር ቤት እንዲገቡ አያደርግም? የሚለው ምክር ቤት በጣም ነው ያሳዘነኝ፡፡ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት እንዴት መጠበቅ ይቻላል? በአንድ ተቋም ውስጥ ሙስና ተሠራ ከተባለ ሁሉም የተቋሙ ኃላፊዎች ማረፊያ ቤት ማስገባት ቀላል ይሆናል፡ ግን ድርጊቱና የሰዎች ሰብዓዊ መብት መታየት አለበት፡፡ ሙስና ሚስጥራዊ ስለሆነ ትክክለኛ የሙስና ተሳታፊዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ የጠራ ምርመራ እየተካሄደ ነው ሰዎች መታሰርና መከሰስ ያለባቸው፡፡ እንደ ምክር ቤቱ ቢሆንማ በአገሪቱ ሰርቀው ሀብት እያፈሩ ናቸው እየተባሉ የሚወራባቸው ሰዎች በሙሉ ታስረው ፍርድ ቤት መቅረብ ይገባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከባድ ይመስለኛል፡፡ ከምክር ቤት ውስጥ ሁሉም ሰዎች መተሳር አለባቸው የሚል ሐሳብ ሲያራምዱ የነበሩ ተመረጮች እንደገና አጠቃላይ ጉዳዮችን በማጣራት ቢያዩት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ካልሆነ ለኮሚሽኑ ግልጽ ትዕዛዝ ይሰጥ፡፡ ሰብዓዊ መብት ገለመሌ ይቅር፣ እስር ቤቶች በስፋት ይገንቡ፣ ከዚያ ውጤቱን የምናየው ይሆናል፡፡

  መንግሥት ለሙስና ያለው አመለካከት እንመልከት፡፡ በቅርቡ ሪፖርተር ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ላይ ያስቀመጠው ካርቱን በጣም ከልቤ ነው የወደድኩት፡፡ እኔ ሪፖርተር ጋዜጣ ከርዕሰ አንቀጹ ጋር የሚያስቀምጣቸው ካርቱን ሥዕሎችን በአድናቆት እከታተላለሁ፡፡ በጣም ገላጭ ነው፡፡ በቅርቡ ስለሙስና በጻፈው ርዕሰ አንቀጽ ላይ ኮሚሽኑ በቀስት፣ ሙስኞች ደግሞ በሽጉጥ የሚፋለሙበትን ያመለከተው ካርቱን ነው ለዚህ ጽሑፍ የገፋፋኝ፡፡ በእርግጥ ሪፖርተር በጣም ትክክል ነው፡፡ መንግሥት ኮሚሽኑን በጣም ሊያግዝ ይገባል፡፡ በጀት ይመድባል፣ ተሽከርካሪዎችን ይሰጣል፡፡ ኮሚሽኑ ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ትግሉ ጠንከራ ከመሆኑ አንፃር በቂ ትጥቅ አለው ብዬ አላስብም፡፡ ደግሞም ነው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በሙስና ትግል ላይ ጠንካራ አቋም እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ የሚመሯቸው ባለሥልጣናት ግን ቢቻላቸው በአንዴ ኮሚሽኑ ድራሹን ቢያጠፉት በጣም ደስ እንደሚላቸውም አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምንጩ ያልተወቃ ሀብት እንዳያፈራ የሚከላከልን ተቋም እንዴት ይወዱታል? አቶ ሸዋፈራሁ ደሳለኝ ስለሙስና የሠራው ጭውውት አንዳንዱን ባለሥልጣን ይመለከታል ባይ ነኝ፡፡

  አሁን ደግሞ ክብር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እስከማውቃቸው ድረስ ከሙስና የፀዱና ሙስናን ለመታገል በጣም ቆርጠው የተነሱ ሰው ናቸው፡፡ እኔም ይህን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ብቻቸውን ይወጡታል ብዬ ግን አላምንም፡፡ በቅርቡ በኅዳር ወር የተለቀቀው የእሳቸው ንግግርም ይህን ያመለክታል፡፡ ደጋፊ ያስፈልጋል፡፡ አሁን መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በተባለው ዘመቻ ማነው የችግሩ ፈጣሪ? የመንግሥት ኃላፊ እኮ ነው፡፡ በቀበሌና በወረዳ ያለውን ችግር በተመለከተ ሕዝብ በቅርበት ሲነሳ እጁን ይቀስራል፡፡ በቃ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ያለው ተብሎ ከቦታው ይነሳል፡፡ በሩቅ ያለውን ማን ያንሳው? በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታየው ችግር ይህ ነው፡፡ ‘አሳ … ከጭንቅላቱ’ ይበል የለም? ለምን ከላይ አይጀምርም? መምራት አለመቻልም፣ በማይችለው ቦታ ተቀምጦ ደመወዝ መውሰድም እኮ ሙስና ነው፡፡ ግን አልተደረገም፡፡ መጀመሪያ ከላይ በማጣራት ወደ ታች ቢኬድ ኖሮ አዎ የመልካም አስተዳደር ችግር ይቀረፋል ይባላል:: አሁን እየተሠራ ያለው ግን በታቀራኒ ስለሆነ ዘላቂ መፍትሔ ይመጣል የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ መጀመሪያ ለሙስና በጣም ቅርበት ያላቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሙስና የሚሠሩ ሙሰኞች ይወገዱና እስቲ ከታች ያለው እንደማይስተካከል ይታያል፡፡ በጣም መፍትሔ ያገኛል፡፡ መሪ ለአገር ዕድገት ወሳኝ ነውና፡፡

  የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ላይ ምናልባት እርካታ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ብቻ ናቸው የሚል ድምዳሜ አለኝ፡፡

  የአገራችንን አበዳሪና ለጋሽ ድርጅቶች ጉዳይ እስቲ እንየው፡፡ እኔ እንደምረዳው አበዳሪ ድርጅቶች የፀረ ሙስና ኮሚሽን መኖርን በጣም ይፈልጉታል፡፡ ምክንያቱም ያበደሩት ገንዘብ ለልማት እንዲውል ተደርጎ ገንዘባቸው በወቅቱ እንዲመለስላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ተጠቃሽ  የዓለም ባንክ  ነው፡፡ የዓለም ባንክ ዱሮ ካበደረው ገንዘብ ላይ ግዥ ሲፈጸም  በቅድሚያ ሰነዱ ዋሽንግተን ተልኮ ዕውቅና ሲሰጥ ነው ክፍያ የሚለቀቀው፡፡ አሁን አሁን ግን የፌዴራል የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በየስድስት ወራት የተለቀቀው ገንዘብ በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጫ ሲሰጥ ቀጣዩ ይለቃል፡፡ እዚህ ላይ የኮሚሽኑን ጣልቃ ገብነት የማይፈልጉ የመንግሥት ኃላፊዎች አሉ፡፡ ገንዘቡ ላለመጣት ሲሉ ብቻ ሳይወዱ በዚህ መንገድ ላይ ነው የሚጓዙት፡፡ አባዳሪዎች የኮሚሽኑ ችግር እየተባለ ብድር ለመስጠት ይቆጠቡ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ኮሚሽኑ ያለበት ችግር ተጨባጭ ከሆነ አሁን በተካሄደበት መንገድ ሳይሆን፣ በመንግሥታዊ አሠራር ሊስተካከል ይችል ነበር፡፡ የቀረበው ችግር ኮሚሽኑ ከሚሠራቸው ሥራዎች 30 በመቶውን በሚይዘው ጉዳይ ላይ ስለሆነ በጣም የገዘፈ ችግር ያለ አይመስለኝም፡፡

  ወደ ዋና ርዕሴ ስገባ የተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ተወካዮች በቅርቡ ‘በኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ላይ የሱፐርቪዥን ሥራ ሠርተን ያገኘነው ውጤት ነው’ ብለው ያዘጋጁትን ሪፖርት ለምክር ቤት አቅርበዋል፡፡ ሚዲያዎች የቆየ ቁጭታቸውን የተወጡ እስከሚመስል ድረስ አራግበዋል፡፡ ችግር አይኖርም የሚል ግምት የለኝም፡፡ እኔ ሙስና ከአገር ይጥፋ ከሚሉት ሰዎች ጎራ ስለሆንኩ በተወሰነ ደረጃ መረጃ ለማሰባሰብ ሞክሬ ነበር፡፡ የሱፐርቪዥን ሥራ የተሠራው የተባለው የኮሚሽኑን ሠራተኞችና አመራሩን ለየብቻቸው መድረክ በማዘጋጃትና በማነጋገር ነው፡፡ ሪፖርት ብለው ያቀረቡት ግን በሠራተኞች የተነሳውን ብቻ ነው፡፡ ሚዛናዊ ለማድረግ በፍፁም አልሞከሩም፡፡ በሠራተኞች መድረክ ላይ ችግር እንዳለ ያነሱት ከመድረክ መሪው ጋር የሚቀራረቡና ቢያንስ ሁለት ሠራተኞች አራት አራት ጊዜ የመናገር ዕድል ተሰጥቷቸው በተነሱ ጉዳዮች ብቻ፣ እንዲህ ዓይነት ግኝት ብለው ሪፖርት ያቀረቡት፡፡

  ሪፖርት ከመቅረቡ በፊት የሪፖርቱ ጥቅምና ጉዳቱ አይታይም ማለት ነው? ተጨባጭስ እንዲሆን ጥረት አይደረግም? ማንን ለመጥቀም ወይስ ስውር ዓላማ ለማስፈጸም? እንዲህ ዓይነት ሥራ የሕዝብ ተወካይ ነን ከሚሉ የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ ዕውቀት ካነሳቸው መጠየቅ ነውር አይደለም፡፡ እውነት ነው ስውር ዓላማ ካለ በብዙ ትግል የተገነበውን ተቋም በአንድ ቀን ማፍራስ ይቻላል፡፡ ደግሞ አሁን ኮሚሽኑ አልፈረሰም ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንዳለ ነው የተገነዘብኩት፡፡ ሪፖርት ለአበዳሪዎች እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ እንዴት ታምነን ነው ብድር የሚሰጠን? ወዴት እየሄድን ነው? እኔ ተወካዮቹ የራሳቸው ሥውር ዓላማ አላቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ሌሎች ኮሚሽኑን ለማጥፋት ያቀዱ፣ ተነድተውና ተሞልተው የመጡ ናቸው፡፡ ለአገር ግን መታሰብ አለበት፡፡ ሠራተኞች ከሪፖርቱ መቅረብ በኋላ በጣም እንደተሰማቸውና ሁለት ሠራተኞች ልፋታቸውን ገደል እንደከተቱትና ጭቃ እንደቀቡት የነገሩኝ ብዙ ናቸው፡፡ ለምን እንዲህ ይሆናል? ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የኮሚሽኑን ገጽታ በእንዲህ ዓይነት የግምገማ ውጤት ማበላሸት ለምን አስፈለገ? ተጠቃሚው ማን ነው? ምን ታስቦ ነው? ችግር እንዳለበት አጋነው የተናገሩት ከተወካዮች ጋር ምን ዓይነት ግንኙት ነበራቸው? ኮሚሽኑን ለማፍራስ ያስቡት ለምን ነበር? ሊያፈርሱት ይችላሉ ወይ? በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ምን ይመስላል? በሚሉት ዙሪያ በመረጃ የተረጋገጠውን ጽሑፍ በቀጣይ አቀርበለሁ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡ ሙስናን ማጥፋት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ነው!

   

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

   

   

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  Related Articles