Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​ዳገቱ ላይ ሆነን ቁልቁለት አይናፍቀን!

ሰላም! ሰላም! ‘እስኪ ከአንድ የዘፈን ግብዣ በኋላ ተመልሰን እንገናኝ’ ብላችሁስ ገና ከመገናኘታችን? ነገር ዓለሙ ለአዶከበሬና ሆይ ሆይታ ተላልፎ በተሰጠበት በዚህ ጊዜ መቻል እንጂ ሌላ ምንም ታመጡ ኖሯል? ብቻ ይኼ የመቻቻል ነገራችን ለምን እንደሆነ እንጃ ቀንሶብኛል። ይባስ ብሎ ነው መሰል ‘የስሪጂና የፎርጂ’ ዋጋም ቀነሰ እየተባለ ነው። አስቡት እንግዲህ! ዋጋ እየከፈልን በድረ ገጽና በየመረጃ መረቡ ላይ የምናሳየው ግልፍተኝነት የተሞላበት የንዝንዝ ሱስ ቀስ በቀስ በነፃ ሲሆን ምን እንደሚመስል ዝም ብላችሁ ማሰብ ነው። ዝም ብላችሁ ማሰብ ከቻላችሁ ነው ታዲያ! የመረብ ዘመን ሲባል ሰው አጥማጅ ኢንተርኔት መባሉ ነው! እናላችሁ ወሬው ሁሉ ‘ስሪጂና ፎርጂ’ ብቻ ሆኖብኝ ስልችት ሲለኝ ሰነበትኩ። የሌላው ሳይሆን የሚገርመኝ ሚዲያው ጭምር ታዳሽ ዜና እያለ ካላጣ ካላጣው ስለብልጣ ብልጥ ስልኮች (‘ስማርት ፎን’ . . . ትርጉም በአንበርብር) መሻሻልና መዋብ ሲያወራ ውሎ ያድራል። ምንድነው ግን የለከፈን? ደግሞ ምናለበት ለሦስትና ለሁለት ደቂቃ ጠቆም እየተደረገ ቢታለፍ? አልኳችሁ ለሰዓታት ይኼን ከመረጃ መረብ ላይ ተቃርሞ የተገኘ የቴክኖሎጂ ወሬ ሲንቶከቶኩ መዋል በቃ።

ለምሳሌ አንዱ ‘ቶከኛ’ ምን ሲል ሰማሁት መሰላችሁ? “. . .  ለምሳሌ አዳዲሶቹ የሳምሰንግ ስልኮች ውኃ ውስጥ ቢገቡብን ምንም ዓይነት ብልሽት እንዳያጋጥማቸው ሆነው ተሠርተዋል። ይኼ ትልቅ ዜና ነው። (እውነትም ትልቅ የጠፋበት ዘመን እላለሁ ከአየር ክልል ውጪ) ካስፈለገ አዲሱ የሳምሰንግ ‘ብልጥ ስልክ’ ተጠቃሚዎች ቤታችሁ ውስጥ በውኃ ዘፍዝፋችሁ ማየት ትችላላችሁ፤” አይልም?! መቼስ ማንጠግቦሽ የዋዛ አይደለችም። እኔ በትዝብት እንደማዳምጠው እሷም አዳምጣው ኖሯል። “አይ . . . ልፉ ብሏቸው እንጂ እንኳን ስልክ የሚያበላሽ ጥም የሚቆርጥ ውኃ አለ ብላችሁ ነው?” ብላ እንደተለመደው ሰሞኑን በሠፈራችን የተከሰተውን የውኃ መቆራረጥ በስላቅ ተረበች። ‘የላጭን ልጅ ቅማል በላው’ ብንል ታዲያ እየኖርን ያለነውን እንጂ በጭፍን ተቃውሞ ፖለቲካዊ ትኩሳቱን ለማባባስ አይደለም። ካስፈለገ ጀርባችንን ማጥናት ይቻላል። ደግሞ ለሚስቱ አገዘ ብላችሁ በተባባሪነት እኔንም እንደ ውኃ እንዳታዘጉኝ ፕሊስ! ታዲያ ምን ልላችሁ ነው  . . . እእእ . . . ያው ያልኳችሁን ማለቴ ነው። ‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቃሚ’ ጣቢያዎች አሰለቹኝ ለማለት ነው እዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ መግባቴ። ጣጣዬ አያልቅ!

እናስ? ይኼው ሰሞኑን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቆጠራ ይካሄዳል ተብሎ አልኳችሁ መቆሚያ መቀመጫ ጠፋ። ያም ሲደውልልኝ ያም ዌቲንግ እየገባ ‘አውጣኝ’ ሲለኝ ከስንቱ ልሁን። ቆይ ግን እኔ እምለው መጀመርያውኑ ሰው ምን እያሰበ ነው ገደል የሚገባው? ያላግባብ የማይገባውን ንብረት የራሱ የሚያደርገው? እውነቴን እኮ ነው። ሺሕ ቀን ቢደላ አንድ ቀን ስቅለት እንዳለ ምነው እምነቱን ትተን ከመስቀለኛው ታሪክ ትምህርት ብንቀስም? ‘ይኼ እንደሚመጣ ልቤ መቼ አወቀ’ ማለት እኮ እዚህ እዚህ ላይ አያስኬድም። “አሁን ሻጭ ፈልግ . . . በወረደ ዋጋ ቢፈልጉ . . .  የአምስት መቶ ሺውን ስቱዲዮ በመቶ ሰማንያ ሺሕ መውሰድ ይችላሉ . . .” ቅብጥርሶ በቃ ተውኝ የነበረው ምልጃና ግርግር። እህ ታዲያ እኔ ምኔ ሞኝ ነው? እንዳጋዛኋቸው የቻልኩትን ያህል አሻሽጬ ‘ይወሰዳል ከተባለው ያልታወቀ ዕርምጃ’ የገላገልኳቸው፣ በስሜ በየሰንበቱ ጧፍ እንደሚለኩሱ አልጠራጠርም።

 ሳንሞት ሰማዕት መሆን በእኛ ነው የተጀመረው? እሱን እኮ ነው የማወራው። “እንዲያው ዝም ብዬ ሳስበው ይኼ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጣጣ ገና በሚመጣው ደግሞም በሚመጣው ትውልድ የሚያልቅ አይመስለኝም፤” ብዬ የባሻዬን ልጅ ሳጫውተው፣ “እንደ አደራረቡን እነሱው ይወጡት፤” ብሎ ዝም አለ። ይኼ እነሱና እኛ እውነቴን ነው የምላችሁ ብዙ ጊዜ አይገባኝም። “ምንድነው የምታወራው?” ስለው፣ “ሁሌም ከፈሰሰ ወዲያ ማፈስ ይወዳሉ። ካልደከማቸው ምን ጨነቀን እኛን። ሕዝብ በእነዚህ የጋራ ቤቶች ዙሪያ የሚደረገውን አይቶ፣ ተባባሪም ሆኖ ተቃዋሚም ሆኖ ኡኡኡ ያለው መቼ ነው? መቼ ነው ንገረኝ?” ሲለኝ መልስ አጣሁ። ‘ኡኡኡታ አያስከፋም ሲለዩ ተዋዶ’ ያለው ጥላሁን ገሠሠ አሁን ቢሆን ኖሮ ምን ብሎ ይዘፍነው ነበር? እናንተ ደግሞ አይገባችሁም እንዴ? ያው እግረ መንገዴን ጫጫታ መቀነሴ (ማስቀየስ ብሎም መተርጎም ይቻላል) እኮ ነው! ወይ ነዶ!

 እንደ ነገርኳችሁ ይኼን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕጋዊ ባለይዞታነት ጉዳይ የፈጠረው ትርምስ በፈጠረልኝ የሥራ ዕድል ስሯሯጥ ውዬ ምሳዬን ለመብላት ቤቴ ጎራ እላለሁ። የምሳ ዕቃ ቋጥሮ በዋሉበት ጥግን ይዞ መብላት እንደሆነ ድሮ ቀርቷል። ለነገሩ አቆጣጠሩ ተለያየ እንጂ ቋጥሮ የሚያግበሰብሰውስ ልቋል። ግን እኛ የሰማይም የምድርም መንግሥት ያልቆጠረውን ሆድ ለምን እንቆጥራለን ብለን ነገሩን ትተነው ነው። እና ማንጠግቦሽ ተፍ ተፍ ብላ ያቀረበችልኝ ጎራርሼ ልወጣ ስል አምፖል ተቃጥሎ ኖሮ፣ “ሳትቀይርልኝ አትሄድም!” አለች። ቤታችን ደግሞ የዛሬን ባለሦስትና አራት ፎቅ ቤተ ሠሪዎች አስቀድሞ በራዕይ ባየ አናጢ ስለተሠራ ሰማይን አይታችሁ ጣራውን ስታዩ ያው ነው። ስለዚህ አምፖል ለመቀየር መሰላል ያስፈልጋል። የዘንድሮ ሰው ደግሞ መሰላል ቢኖረውም አለኝ አይልም። አለኝ ቢልም አያውስም።

እሱን ተውትና በገዛ መሰላላችን ሽቅብ ስንወጣጣ ስንቱ ነው በጠረባ ብሎ ከሥር ሊጥለን ሲትጎለጎል የሚውለው? ‘ዲድ አይ ሰይ ሰምቲን ሮንግ?’ ይላል አሉ ፈረንጅ። አይዟችሁ የዘመኑ አንዱ መሰላል ‘ሊበሏት ያሰቧትን ምንትስ በእንግሊዝኛ ማጣደፍ’ ስለሆነ ወጥሬ እየተማርኩ ነው። ታዲያ ማን ነው መሰላል የሚያውሰኝ እያልኩ ሳስብ ባሻዬ ትዝ አሉኝ። የሩቅ እያሰብን ደግሞ ይገርማችኋል የቅርብ ደጋጎችን ስም አብረን ማጉደፍም እኮ ለምደናል። ባሻዬ ያው እንደተለመደው ባለቤታቸው በሕይወት እያሉ ሸጋ አርገው የጠለፏትን ዳንቴል አልብሰው ሬዲዮናቸውን ጆሯቸው ላይ ለጥፈው ደረስኩ። “ባሻዬ መሰላል . . .”  ብዬ ሳልጨርስ በሌባ ጣታቸው ከንፈራቸው ላይ መስቀል ሠርተው “እሽ!” አሉኝ። ምናለበት አንዳንዶቻችንም በሩቅ ሰምተን ያልጨረስነውን ለማጣጣልና እንዲህ ነው ለማለት ከመሽቀዳደም ቢያንስ እንደ ባሻዬ ታንቡራችን እስኪቀደድ የምንሰማውን እንኳ አስተካክለን የመስማት ፀጋ ቢያድለን? ‘ምናለበት ነበር … ነበር ባይሰበር’ አሉ አሉ ማናቸው ስማቸው?!

መሰላል ለመዋስ የሄድኩት ሰውዬ ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ለ75 ዓመታት እውነተኛ ደስታን በተመለከተ ያካሄደውን ጥናት ውጤት ላዳምጥ ከባሻዬ ጎን ቁጭ ብዬ ቀረሁ። መቼም ይኼ ሁሉ ትርምስ፣ ግፍ፣ ንጥቂያ፣ ቅሚያ፣ ገንዘብና ሀብት ማካበት ሁሉ ግቡ ደስተኛ ለመሆን አይደል? የሰው ልጅ ደስታን ለማግኘት ያልሞከረውና ያልፈነቀለው ነገር የለም። ይኼ እስከኛ ዘመን የእውነተኛ ደስታ ምንጩ በግለሰብ ደረጃና በሃይማኖታዊ ቀኖና ላይ ካልሆነ በቀር፣ በሳይንሳዊ ምርምር ላይ የተመረኮዘ መግባባት የለም። አተኩሬ ባሻዬን ሳያቸው ዕድሜያቸው ከጥናቱ ጥቂት ዓመታት ብቻ ቢበልጥ እንደሆነ ተረዳሁ። በዚያ ላይ ጥናቱ ከ750 ሰዎች በላይ የተሳተፉበት እንደሆነ ተናጋሪው ይለፍፋል። ውጤቱ እንደ ሳይታለሙ የሚፈቱትና (አርሰናልን ይመለከቷል) እንደ ማንቸስተር ውጤት አጓጓኝ።

የእውነተኛ ደስታ ምንጩ እንደ ሐርቫርድ የ75 ዓመታት ጥናት ውጤት . . .  ላገቡ ከትዳር አጋር ጋር ያለ እውነተኛ ፍቅር ግንኙነት ሲሆን፣ ላላገቡ ከቤተሰብና ከማኅበረሰብ ጋር ያለ ጤናማ ግንኙነት ነው ሆነ። ባሻዬ አገር ይያዝልኝ አሉ። “ወይኔ ልጄ ወይኔ ልጄ! ማረኝ! ማረኝ!” እያሉ ጮሁ። “ኧረ ይረጋጉ ብላቸው ሊሰሙኝ ነው? ኋላ በጥሞና ስረዳቸው ግን ለካ ባሻዬ ልጃቸው ሐርቫርድ ኦክስፎርድ ወዘተ፣ ዓለም አቀፍ ዝናቸው የናኘላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ እንዲማርላቸው ህልም ነበራቸው። “ታዲያ ይኼ አባት ለልጁ የሚመኘው ጥሩ ምኞት አይደለም እንዴ?” ስላቸው፣ “እኮ ጠቢቡ ሰለሞን ምዕራፍ በማይሞሉ መስመሮች ያብራራውን የእውነተኛ ደስታ ምንጭ 75 ዓመት ለመፈለግ? ማረኝ ልጄ ማረኝ!” ሲሉ መሰላሌን ይዤ ውልቅ አልኩ። ከፀሐይ በታች አዲሴ ነገር ባይኖርም በበኩሌ ከጣራዬ በታች አዲስ አምፖል አብርቼ የአባወራነት ግዴታዬን ተወጥቻለሁ። መሰላሉን ግን ለመመለስ ከሳይንስ አኳያ ስንት ዓመት፣ ከእምነት አኳያስ ምን ያህል  ቅፅበት እንደሚወስድብኝ ማወቅ ተስኖኛል!

በሉ እንሰነባበት። ተፍ ተፉን ጨርሼ ከአገሬ የኢኮኒሚ ዕድገት መሳ ለመሳ የቁጠባ ባህሌን አሻሽዬ፣ ጥቂት ገንዘብ ባንክ ወርውሬ፣ ከባሻዬ ልጅ ጋር ወደተለመደችዋ ግሮሰሪ ጎራ አልኩ። ጨዋታው ቀልጧል። “አሁን በትራፊክ አደጋ ቀዳሚ ያደረገን መንስዔ ፍጥነት ነው? መሪ በሁለት እጅ ጨብጦ አለማሽከርከር?” ብሎ አንዱ  መጠይቁን ይነዛል። “የለም ፍጥነትም አይደለም እጅም አይደለም . . . መንገዱ ነው የሚያጉላላን፤” ይላል ሞቅ ያለው ጠጪ ልዝዝ ባለ አነጋገር። “መንገድ ምን አገባው ደግሞ? በለማ? በታደሰ? በሰፋ? መንገድ ምን አደረገ?” ሲለው አጠገቡ ያለው፣ “አንድ መንገድ ብቻ ስለምን ታስባላችሁ? ብዙ መንገዶች እኮ አሉ መንገድ የሚተረጎምበት…” ብሎ ግራ የገባው ሰካራም ታዳሚውን ግራ አጋባው። “ይልቅ እሱን ተውትና ምንድነው ይኼ አዲስ ወጣ የሚባለው ሕግ?” ብሎ ከባሻዬ ልጅ ጎን የተቀመጠ ትልቅ ሰው በጥሞና ጠየቀ። “ሕግ ነዋ! እንደ አብዛኛዎቹ የአገራችን ሕጎች ከመገልገል ይልቅ የምንሸከመው…” ብሎ ያ ጉደኛ ጠጪ ሲናገር፣ “ኧረ እንዳታስቀጣን ሰውዬ ቀስ እያልክ አሽከርክር…” ባዩ አሽሟጣጭ ከጎኑ የተቀመጠው ነው።

ይኼኔ የባሻዬ ልጅ ወደኔ ጠጋ ብሎ፣ “ታውቃለህ አንበርብር፣ ያ ሰው ሳያስበው የተናገረው ሀቅ አለው። ጥፋት ብቻ የሚመዘግብ ሕግ፣ ከአስተማሪነቱ ይልቅ አጥብቆ ተከታታይነቱና አደናጋሪነቱ የበዛ ሕግ፣ ከሳሽና ተከሳሽን እኩል የማያዳምጥ፣ መንገድ አገናኝቶ መንገድ የሚለያይ፣ ይግባኝ የሚሰማበት ሸንጎ የሌለው ሕግ አደጋውንም አይቀንስም፣ ጉቦኛውንም አያሸማቅቅም፣ ሥጋታችንንም አያበርድም፤” ብሎኝ አረፈው። ብዙ ላስወራው አልፈልግም እንጂ ለማለት የፈለገው በአጭሩ፣ “አገልጋይ እንጂ ቀንበር ሕጎች ሰልችተውናል፤” ነው። እኔ ደላላው አንበርብር በሕግና በሕግ የበላይነት ባምንም፣ የሰው ልጅ የሕግ ተገልጋይ እንጂ አዋኪ ሲሆን ማየት ምቾት አይሰጠኝም። እስኪ ቀንበሩን ለዘብ አገልግሎቱን ላቅ የሚያደርገው ላይ እናተኩር። ዳገቱ ላይ ሆነን ቁልቁለት አይናፍቀን! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት