Saturday, January 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት​‹‹የአዳማ ከተማ ዕቅድ ጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ክለብ መፍጠር ነው››

​‹‹የአዳማ ከተማ ዕቅድ ጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ክለብ መፍጠር ነው››

ቀን:

አቶ ዓለማየሁ ቱሉ፣ የአዳማ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በውድድር ዓመቱ ለፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ከሚጠበቁ ቡድኖች ይጠቀሳል፡፡ በ2005 የውድድር ዓመት ወደ ብሔራዊ ሊግ ወርዶ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በ2007 የውድድር ዓመት ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው አዳማ ከነማ እስከ ዘጠነኛው ሳምንት ድረስ ሊጉን ሲመራ ቆይቷል፡፡ ልምድ ባላቸውና ወጣት ተጫዋቾች ከተዋቀሩ ቡድኖች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው አዳማ አዳዲስ የመዋቅር ለውጦችን እየተገበረ መሆኑ ይነገራል፡፡ ክለቡ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበ ለሚገኘው ውጤትም በመዋቅራዊ ለውጡ ምክንያት እንደሆነም የሚናገሩ አሉ፡፡ የአዳማ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ቱሉ ክለቡ እንደ ክለብ መቀጠል ካለበት ከቆየው ልማዳዊ አሠራር መላቀቅ የሚያስችለውን የመዋቅር ለውጥ ማድረግ ሲችል ብቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ዓለማየሁ እግር ኳስ በምንገኝበት ዘመን ከመዝናኛነት አልፎ ትልቅ የቢዝነስ አማራጭ ሆኗል፡፡ አዳማ ከነማን ጨምሮ የአገሪቱ ክለቦች በዚሁ መቃኘት እንዳለባቸው ጭምር ይጠቁማሉ፡፡ ደረጀ ጠገናው በክለቡ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዳማ ከነማ ወደ ብሔራዊ ሊግ ወርዶ ከመጣ በኋላ በፕሪሚየር ሊጉ ወጥ የሆነ አቋም ከሚያሳዩ ክለቦች አንዱ ሆኗል፡፡ በጎል ተበልጦ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የጥንካሬው ምስጢር ምንድነው? (ቃለ መጠይቁ የተደረገው የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው)

አቶ ዓለማየሁ፡- አዳማ ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከተመለሰ በኋላ ከጠንካራዎቹ ተፎካካሪዎች ተጠቃሽ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ክለቡ በ2005 የውድድር ዓመት ለምን ወረደ በሚለው የተመለከትነው በጥልቀት ተነጋግረንበት የደረስንበት ድምዳሜ ነው፡፡ በግምገማችን በዋናነት የተነሳው የአደረጃጀት ችግር መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ የባለሙያተኞች እጥረትና ከዚሁ ጎን ለጎን የስብስብ ችግርም እንደነበረበት መተማመን ላይ ደርሰንም ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ከተገመገሙ በኋላ ለ2006 የውድድር ዓመት ዝግጅት የመጀመሪያ አጀንዳችን አቅምና ብቃቱ እንደሁሉም በራሱ የሚተማመን አሠልጣኝ መቅጠር እንደሚገባን ከተስማማን በኋላ ግልፅ ማስታወቂያ ወጥቶ ሦስት አሠልጣኞች ቀረቡ፡፡ ከእነዚህ መካከል የአሁኑ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ይገኝበታል፡፡ የአሠልጣኝ ቅጥሩ ከተከናወነ በኋላም ሙሉ ኃላፊነት መሰጠት በሚለው ከተነጋገርን በኋላ ዕውን አድርገናል፡፡ ከአሠልጣኙ ጀርባ በመሆን ምንም ዓይነት ጥያቄ ሲቀርብልን በተለይ ለአሠልጣኙ ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠት በመቻላችን የመጣ የውጤት ለውጥ ነው፡፡ ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መምጣት ካለበት ዋንጫውን ጭምር በልቶ እንዲሆን አቅደን ያንንም አሳክተናል፡፡ የከተማው አመራር በሚሰጡት ልዩ ትኩረት ጭምር ነው ክለቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ሊደርስ የቻለው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለ በኋላም የነበረው ጥንካሬ ቀጣይነት ኖሮት እንዲቀጥል ስናቅድም ዝቅ ያለ ዕቅድ አላቀድንም፡፡ ለዚያም ነው በ2007 የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በአብዛኛው ዕቅድና ውጤት ተጣጥመው ሲሄዱ አይስተዋልም፡፡ ከዚህ አኳያ የአዳማ ከነማን ለየት የሚያደርገው ምንድነው?

አቶ ዓለማየሁ፡- ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ክለቡ በተፈለገው መጠን ውጤት ማምጣት አለበት የሚለውን ስናስብ በተቻለ መጠን ዕቅዶቻችን ወደ መሬት መውረድ እንዳልባቸው አምነንና ተማምነን ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ትርፉ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጊዜ ማጥፋት እንደሚሆን እምነት ወስደናል፡፡ ለዚህም ነው በ2007 የውድድር ዓመት በክለቡ ታሪክ ጥሩ ውጤት መመዝገብ የቻለው፡፡ ለአሠልጣኙና በስሩ ለሚገኙ የአሠልጣኞች ስብስብና ተጫዋቾች ጭምር በየድርሻቸው ኃላፊነቶቻቸውን ቆጥረን ስለሰጠናቸው የመጣ ውጤት ነው፡፡ ዘንድሮም የአምናውን መሠረት አድርገን ለዋንጫ እየተጫወትን እንገኛለን፡፡ እንዳደረግነው ዝግጅት የሊጉ መቆራረጥ ባይፈጠር ኖሮ አሁን ካለን ውጤት በላይ ማስመዝገብ በቻልን ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ አሁንም እንደ ስኬት የምንወስደው ሥራዎችን በጥንቃቄና በተጠና አግባብ መሥራት እንደሚኖርብን ነው፡፡ የመደገፍና ትኩረት የመስጠት ተግባር ቀጣይነት ካላቸው ውጤት የማይመጣበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለዚህ ዋናዎቹ ተዋንያን ደግሞ ተጫዋቾቹና አሠልጣኞቹ በመሆናቸው ኃላፊነታቸውንም ከመወጣት ወደኋላ አላሉም ወደፊትም አይሉም፡፡

ሪፖርተር፡- በተጨባጭ ለተጫዋቾቹና አሠልጣኞቹ የተደረገ ነገር ካለ ቢጠቅሱልን?

አቶ ዓለማየሁ፡- ለአዳማ ከነማ ለመጫወት የተስማሙ ተጫዋቾችና አሠልጣኞች መደበኛውን ዝግጅት ከመጀመራቸው በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ በግልፅ ተነጋግረናል፡፡ የአመራሩ ድርሻ የተጫዋቾችና የአሠልጣኞች ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት ማለቴ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ነው ሥራ የጀመርነው፡፡ እያንዳንዱ ተጫዋች ክለቡ ምን እንደሚፈልግ ብትጠይቋቸው የሚሰጡዋችሁ ምላሽ ግልፅ ነው፡፡ እኛም በገባነው ቃል መሠረት ምንም ሳናጓድል ማሟላት የሚገባንን እያሟላን ነው፡፡ በክለቡ ውስጥ መተማመን አለ፡፡ ምንም ነገር ተናግረን ያልፈጸምነው ምንም ነገር ስለሌለ ማለቴ ነው፡፡ ዘንድሮም ያስቀመጥነው ግብ አለ፣ ተጫዋቾቹ ያንን ማሳካት ከቻሉ ልዩ ሽልማት ይጠብቃቸዋል፡፡ ክለቡ የአዳማ ከተማ ብቻ ሳይሆን በፕሪሚየር ሊጉ ብቸኛው የኦሮሚያ ክልል ተወካይ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥትም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ቡድኑ በየጨዋታው ሲያሸንፍና አቻ ሲወጣ የገንዘብ ማበረታቻ እየተሰጡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዳማ ከነማ በጎል ክፍያ ተበልጦ ፕሪሚየር ሊጉን በሁለተኛነት ይመራል፡፡ ወቅቱ የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር እየተጠናቀቀ ያለበት ነው፡፡ ሁለተኛው ዙር ከመጀመሩ በፊት በሚኖረው የተጫዋቾች የዝውውር ገበያ ውስጥ ለመግባት በእናንተ በኩል ምን የታቀደ ነገር አለ?

አቶ ዓለማየሁ፡- ይኼ የአሠልጣኙ የማይገሰስ መብት ነው፡፡ እንደ አመራር አሠልጣኙ በቡድኑ ውስጥ ያለውን ክፍተት ተመልክቶ በሚያቀርብልን ሪፖርት መሠረት የምንፈጽም ነው የሚሆነው፡፡ እንደሚታወቀው ያለን ስብስብ ሰፊ ነው፡፡ ክፍተት ግን የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ለሁሉም ነገር የአሠልጣኙ ሪፖርት ነው ወሳኝ የሚሆነው፡፡ ወደ ክለቡ ሊመጣለት የሚፈልገው ተጫዋች ካለና ከጠየቀ ለመፈጸም ዝግጁ ነን፡፡ ምክንያቱም የአዳማ ከተማ ዕቅድ ጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ክለብ መፍጠር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዳማ ከነማ እያስመዘገበ ካለው ውጤት በመነሳት ለሻምፒዮንነት ከሚጠበቁ ቡድኖች ተርታ ተመድቧል፡፡ ቡድኑ ውጤቱን አስጠብቆ መቀጠል ይችል ዘንድ በዋናነት የአዳማ ከተማ ነዋሪና ሌላውም የክለቡ ደጋፊዎች የሚኖራቸው ድርሻ ወሳኝ ነው፡፡ ይህን አቀናጅቶ በማስኬድ ረገድ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ዓለማየሁ፡- የከተማችንም ሆነ የክልላችን ኅብረተሰብ የሚሰጠው ድጋፍ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ቡድናችን በየትኛውም አጋጣሚ ውድድር ሲኖረው 12ኛው ተጫዋች ሆኖ እያገዘ ያለው ይኼው ኅብረተሰባችን ነው፡፡ ይህንን በጠንካራ መሠረት ላይ አጠናክሮ ለመቀጠልም እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ የእኔነት ስሜት ተፈጥሯል፡፡ ጠንካራ የደጋፊዎች ማኅበርም አለን፡፡ ኅብረተሰባችን በሐሳብ ብቻ ሳይሆን በፋይናንስ ጭምር እየደገፈ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከቡድኑ አደረጃጀት ጋር በተገናኘ ደጋፊዎች የመሸሽ ዓይነት ጅምሮች ነበሩ፣ አሁን ግን ችግሮቹ እንኳ ቢኖሩ በቅርበት በመነጋገር የጋራ መፍትሔዎችን በማመቻቸት ደጋፊዎቻችንን እያበዛንና እያጠናከርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደሚነገረው በተለይ በአሁኑ ወቅት ወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል በስፖርት የማሳተፍ እንቅስቃሴ እየተዳከመ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አዳማ ከተማ በአገሪቱ በርካታ ቁጥር ያላ       ቸው ወጣቶች ከሚገኙባቸው ከተሞች አንዷ ነች፡፡ ችግሩን ለመፍታት በእናንተ በኩል ምን የታቀደ ነገር አለ?

አቶ ዓለማየሁ፡- በተለይ ታዳጊ ወጣቶች ላይ ከመሥራት አኳያ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈው በስፋት እየተሠራባቸው ነው፡፡ በከተማችን ከ600 በላይ ታዳጊ ወጣቶች በዚህ ፕሮግራም ታቅፈው በተለያዩ ስፖርቶች እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በዋናነት እግር ኳስ ጎልቶ ቢወጣም በአትሌቲክስ ክልሉ በሚያዘጋጀው ሻምፒዮና ከተማችን ተጠቃሽ ነው፡፡ በሁሉም ስፖርቶች እንሳተፋለን፣ ዘንድሮ በተለይ በሴቶች ቮሊቦል (መረብ ኳስ) በፕሪሚየር ሊግ እየተወዳደርን እንገኛለን፡፡ በአዳማ በስፖርቱ ከፍተኛ የሆነ አብዮት እየተፈጠረ ነው፡፡ በእግር ኳስ ከዋናው ቡድን ስር ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታችና ተስፋ ቡድኖች አሉ፡፡ ቅርጫት ኳስና አትሌቲክስ ቡድኖች አሉን፡፡ በተለይ በአትሌቲክስ በአገሪቱ አዳዲስ ክብረወሰን ያስመዘገቡ አትሌቶች ማፍራት የቻልንበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በሌሎች ስፖርቶች ካራቴ፣ ባድሜንተንና በመሳሰሉት ጭምር እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- አዳማ ከተማን ጨምሮ በብዙ የአገሪቱ ከተሞችና ክልሎች የማዘውተሪያ ችግር እንዳለ ይታመናል፡፡

አቶ ዓለማየሁ፡- እንደተባለው የማዘውተሪያ ቦታዎች ክፍተት የመላ አገሪቱ ነው፡፡ ይኼ አዳማ ከተማንም ይመለከታል፡፡ ያም ሆኖ ግን በከተማችን የአበበ ቢቂላ ስታዲየምን ጨምሮ ባሉን ማዘውተሪያዎች በተለይ በትምህርት ቤቶች በቂ ማዘውተሪያዎች ስላሉን በእነዚያ እየተጠቀምን እንገኛለን፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን አዳዲስና ዘመናዊ ስታዲየሞችን ለመገንባት እየተንቀሳቀስንም ነው፡፡ በዚህ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ አንድ ዘመናዊ ስታዲየም ለመገንባት የበጀትና ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ቦታው ተዘጋጅቷል፡፡ ከቤት ውስጥ ውድድሮች (ኢንዶር ጌምስ) ጋር የተያያዙ ማዘውተሪያዎች በመገንባት ላይ ናቸው፤ የተጠናቀቁም አሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን የማዘውተሪያ ስፍራ ከፍተኛ እጥረት መኖሩ እውነት ነው፡፡ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም በቂ ግን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዲሲፕሊን ጋር ተያይዞ በክለቡ ውስጥ በተለይ በአንዳንድ ደጋፊዎች አማካይነት ችግሮች ተፈጥረው እንደነበር፣ በዚህም ዋና አሠልጣኙ የሥራ መልቀቂያ እስከማስገባት መድረሱ ተሰምቷል፡፡ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

አቶ ዓለማየሁ፡- እንደሚታወቀው በስፖርት ሚዳ እንደእነዚህ የመሰሉ ክስተቶች ይፈጠራሉ፡፡ በክለባችን በተለይም በአሁኑ ወቅት ተፈጠሩ የተባሉት ችግሮች ተወግደው ሰላማዊ ድባብ ነው ያለው፡፡ ብዙዎቹ ደጋፊዎች እነዚያን ጥቂት በጥባጮች እያወገዙ  ነው፡፡ እግር ኳስን ተወዳጅ ከሚያደርጉት ነገሮች መሸነፍና ማሸነፍ መኖሩ ነው፡፡ አዳማ ከነማም የዚህ አንድ አካል ነው፡፡ ይህንን እውነታ የማይቀበሉ በጣም ጥቂት ግለሰቦች ናቸው፡፡ ተቃውሞ መቼና በምን አግባብ እንደሚነሳ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች ቡድናችን ውጤት እያመጣ ባለበት በዚህ ወቅት ለማስነሳት የፈለጉት ብጥብጥ ግልፅ አይደለም፡፡ ምናልባትም እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች የራሳቸው ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል የሚል በእኛ በኩል ጥርጣሬ አለ፡፡ በዚህ መነሻነት ጥርጣሬው በዚህ ሳይወሰን ግለሰቦቹን ከሕግ አካል ጋር በመሆን የከተማው ከንቲባ ጭምር ግልፅ አቅጣጫ ያስቀመጡበት አግባብ ነው ያለው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር በድጋሚ እንዳይፈጠር፣ ከተፈጠረም ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ጭምር የተሄደበት አግባብ አለ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በአሁኑ ወቅት ተግባብተን ሰላም ወርዷል፡፡ እንደተባለው በችግሩ ምክንያት አሠልጣኙ መልቀቂያ ማስገባታቸው እውነት ነው፡፡ ከአሠልጣኙ ጋር ተነጋግረን መግባባት ላይ በመድረሳችን በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅማቸው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ጥፋተኛ የተባሉትም ተለይተው የታወቁበት አግባብ አለ፡፡ ይህን በአዲስ መልክ የሚዘረጋውን ዕቅድ ቆጥሮ ሰጥቶ ቆጥሮ መረከብ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት እየተዘረጋ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...