Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተር​​​​​​​የብሔራዊ ሎተሪ የሕዝብ ተደራሽነት ይስፋ!

  ​​​​​​​የብሔራዊ ሎተሪ የሕዝብ ተደራሽነት ይስፋ!

  ቀን:

  ብሔራዊ ሎተሪ ከ50 ዓመታት በላይ ጉዞው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠው አገልግሎት ቀላል ባይሆንም፣ የሎተሪ ባለዕድለኞችን ከማብዛትና ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ግን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ የሕዝብ ተደራሽነቱን ለማስፋት ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ዘጠና ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ እንደ ሕዝቡ ብዛትም የሎተሪ ደንበኛው ቁጥርም ጨምሯል፡፡ ሎተሪ ይደርሰኛል በሚል ተስፋ ትኬት የሚገዛው ሰው በጣም አነስተኛ የገቢ ምንጭ ካላቸው ጫማ ጠራጊዎች አንስቶ እስከ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውን ጭምር ያጠቃልላል፡፡

  የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ድርጅት በሕዝብና በመንግሥት አመኔታ የተቋቋመ እንደመሆኑ፣ የብዙኃኑን ተስፋ በሚያለመልም አግባብ የአሠራር ፖሊሲውን መፈተሽ፣ እንደወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚተዳደርበትን ፖሊሲ መለወጥና ማሻሻል እንዳለበት ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡ የውጭ አገሮች የሎተሪ አሠራር ተሞክሮም ማየትና ልምድ መውሰድም ጠቃሚ ነው፡፡

  የብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት የሥራ ፕሮግራምና ዕቅድ መንግሥት ከዘረጋው የአገሪቱ ሁሉ አቀፍ መርሐ ግብር ጋር በጣም የሚጣጣምበት፣ የሚቀናጅበትና የሚተሳሰርበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ አሁን አሁን ዜጎች ከመቼውም በበለጠ ድህነትን ለማስወገድ በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞ ተደራጅተው የመሳተፍና በሥራ የመለወጥ ዝንባሌና ፍላጐት እየጨመረ ባለበት ወቅት፣ ብሔራዊ ሎተሪ የከፍተኛ ዕጣ ተጠቃሚ የመሆን ዕድልን (Probability) እንደ ሰማይ ከማራቅ ወይም እጅግ በጣም ብርቅ ከማድረግ ይልቅ፣ ወደ ሕዝቡ ዘንድ መቅረብና ሎተሪ አዘውትረው ከገዙት በአስተማማኝ እንደሚደርስና ችግር ፈቺ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ሠርቶ በማሳየት ሕዝብን ማሳመን ይገባዋል፡፡ ብሔራዊ ሎተሪ የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት በአንደኛ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ከፍተኛ ዕጣዎች ብቻ መታጠር የለበትም፡፡

  በየካቲት 2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የሚወጣው የባለዝሆኑ የሎተሪ ዕጣ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ከፍተኛ ዕጣዎች እንዳሉት ተገልጿል፡፡ ስድስተኛው ከፍተኛ ዕጣ ብር 175,000 እንደሚያስገኝም ተመልክቷል፡፡ ይህ መልካም ጅምር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝብን ከመድረስ አኳያ ያንሳል፡፡ ለምን ቢባል ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በጣም ወደ ሕዝቡ ልውረድ፣ የተሸላሚዎችን ቁጥር ላስፋ ካለ፣ አሁን እንደ ከፍተኛ ዕጣ የተቆጠረው የብር 175,000 ስድስተኛ ዕጣ ወደ 50ኛ የሎተሪ ዕጣ የማያድግበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ የሕዝብ ተደራሽነት የሚሰፋበት አንዱ መንገድም ይኸው ነው፡፡

  የሕዝብ ተደራሽነት ከማስፋት አኳያ ሌላ ጥሩ አብነት ሊሆን የሚችለው፣ ብሔራዊ ሎተሪ በቅርቡ ለህዳሴ ግድብ ያዘጋጀው ሎተሪ ነው፡፡ ይህ ሎተሪ፣ አንደኛ ዕጣ ብር 10,000,000 እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ የሕዝቡ ተደራሽነት ለማስፋት ሲባል የአራቱም ዕጣዎች ድምር የሆነውን ብር 18,000,000 ለአራት ሰዎች ከማስረከብ ይልቅ 13 ባለዕድለኞችን መጥቀም ይቻላል፡፡ እንዴት? እንደሚከተለው፡-

  1ኛ ዕጣ ብር 3,000,000 ያሸልማል

  2ኛ ዕጣ ብር 2,000,000 ያሸልማል

  3ኛ ዕጣ ብር 1,700,000 ያሸልማል

  4ኛ ዕጣ ብር 1,600,000 ያሸልማል

  5ኛ ዕጣ ብር 1,500,000 ያሸልማል

  6ኛ ዕጣ ብር 1,400,000 ያሸልማል

  7ኛ ዕጣ ብር 1,300,000 ያሸልማል

  8ኛ ዕጣ ብር 1,200,000 ያሸልማል

  9ኛ ዕጣ ብር 1,100,000 ያሸልማል

  10ኛ ዕጣ ብር 1,000,000 ያሸልማል

  11ኛ ዕጣ ብር 900,000 ያሸልማል

  12ኛ ዕጣ ብር 800,000 ያሸልማል

  13ኛ ዕጣ ብር 500,000 ያሸልማል

  በአንድ ወቅት የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ድርጅት በየዓመቱ ለመንግሥት ብር 100,000,000 ፈሰስ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ለመንግሥት የተደረገው ፈሰስ በተዘዋዋሪ ለሕዝብ ጥቅም እንደሚውል ቢታመንም፣ ከስንት ድሃና ተስፈኛ የተሰበሰበ የሎተሪ ሽያጭ ገንዘብ ለመንግሥት ካዝና ፈሰስ መደረጉ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከቀድሞ መንግሥታት የተወረሰ ተለምዶአዊ አሠራር ሆኖ ነው እንጂ የቀጠለው፣ አሁን ያለው የመንግሥት አስተዳደር ቆም ብሎ ቢያስተውለው ትክክል አለመሆኑን ይረዳል፡፡ ከሕዝብ የተሰበሰበው የሎተሪ ሽያጭ ገንዘብ አስተማማኝነቱ በተረጋገጠ ትክክለኛ አሠራር ወደ ሕዝቡ መመለስ እንዳለበት ያምናል፡፡ በሌላ አባባል፣ ብዙ የሎተሪ ባለዕድለኞች ተጠቀሙ ማለት ከብድርና ወለድ ነፃ የሆነ የመሥሪያ ካፒታል ዜጎች አገኙ ብሎም ደግሞ ድህነት ቀነሰ ማለት ስለሆነ መንግሥት ፈሰስ ከሚደረግለት ይልቅ የሚጠቅመው ይህኛው የአሠራር ስትራተጂ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

  ስለዚህ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በሕዝብና መንግሥት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ በማገልገል የመሥሪያ ካፒታል ያጣውን የሥራ ኃይል ተደራሽነት ለማስፋት የሎተሪ ተሸላሚዎችን ቁጥር ማበርከት ይኖርበታል፡፡ የከፍተኛ ዕጣ ተሸላሚዎች ቁጥር ሲበረክት፣ የሎተሪ አጓጊነት ይጨምራል፣ ብዙ የሎተሪ ደንበኞችንም ይስባል፡፡

  በመጨረሻም ብሔራዊ ሎተሪ የነጋዴ ባህሪ ጎልቶ ይንፀባረቅበታል፡፡ በአጭር ጊዜ ብዙ ትርፍ ለማስገኘት እንደ ተቋቋመ የግል ድርጅት ይመስላል፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ስለምን ድርጅቱ በሎተሪ ትኬት ሽያጭ የሰበሰበውን የሕዝብ ገንዘብ የዕጣ አወጣጥ ካላንደር በማዘጋጀት አሁን እንደሚያደርገው አስተማማኝነቱ በተረጋገጠ የዕጣ አወጣጥ ዘዴ የራሱን የሥራ ማስኬጃና የመንግሥት የሥራ ግብር ከቀነሰ በኋላ መልሶ ለደንበኞቹ ማከፋፈል ይኖርበታል፡፡ ይህን ሲያደርግ ብቻ ነው የሥራ ፍላጐቱ ላልበረደውና እየተጋጋለ ለመጣው አዲሱ ትውልድ የማያቋርጥ የገንዘብ ምንጭነቱን ሊያረጋግጥ የሚችለው፡፡ በተጨማሪም የብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት ከደንበኞቹ ጋር የሚገናኝበት የራሱ የሆነ መጠነኛ የጋዜጣ ልሳን ቢኖረው መልካም ነው፡፡    

  (ሙሉጌታ ደንበል፣ ከአዲስ አበባ)

  ********

  የቴብምርን ጉዳይ ለማን አቤት እንበል?

  ቴምብር የተለያዩ ጥቅሞች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ሰዎች ደብዳቤ ጽፈው በፖስታ ቤት በሚልኩበት ጊዜ ይጠቀሙበታል፡፡ ከዚሁም ባሻገር በአገራችን በመንግሥት መሥሪያ ቤት ለሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች ቴምብርን መጠቀም አስገዳጅ የሆኑባቸው አገልግሎቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ አገልግሎቶች መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፉ አንዱ ነው፡፡

  ዜጎች መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ወይም ለማደስ ሲፈልጉ፣ አዲስ ሰሌዳ ማውጣት ወይም ሊብሬ ለመውሰድ በዶክመንታቸው ላይ ቴምበር መለጠፍ ግድ ይላቸዋል፡፡ እኔም ሰሞኑን አዲስ ለገዛሁት መኪናዬ ሰሌዳ ለመውሰድ በመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተገኝቼ ነበር፡፡ ሰሌዳውን ለማውጣት የሚያስፈልገውን የቴምብር ቀረጥ ለመክፈል ግን አልቻልኩም ነበር፡፡ ይሄም የሆነው በመሥሪያ ቤቱ የሚሸጥ ቴምብር ባለመኖሩ ነው፡፡ ምክንያቱንም ስጠይቅ ቴምብር አልታተመም የሚል ነበር፡፡

  ለሥራ የምፈልገውን መኪና ያለሰሌዳ መንዳት የማይቻል ሲሆን፣ ሰሌዳውን ለማግኘት ደግሞ ቴምብር ማግኘት ግድ ሆነብኝ፡፡ እኔም ቴምብር የት እንደማገኝ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሠራተኞቹን ስጠይቅ፣ ደጃፍ ላይ ቴምብር እንደሚሸጥ ይነግሩኛል፡፡

  የባለሥልጣኑ ደጃፍ ላይ ግን የሚሠራው ሥራ ዛሬ ይህቺን ጽሑፍ እንድጽፍ አስገድዶኛል፡፡ መንግሥት አምስት ብር የሚሸጠውን ቴምብር ደጃፍ ላይ ያሉ ‹‹ደላሎች›› 50 ብር እና 60 ብር ይሸጡታል፡፡ እኔም ይህ ድርጊት አበሳጭቶኝ በአካባቢው ለሚገኙ የፖሊስ አካላት ባስታውቅም፣ ምላሻቸው ይሄ ጉዳይ እኛን አይመለከትም የሚል ነበር፡፡

  መንግሥት ማቅረብ የነበረበት ቴምብር አልታተመም በሚል ተልካሻ ምክንያት የመንግሥትንም ሆነ የተገልጋዩን ሥራ ማስተጓጎል ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚህም ባለፈ በዘርፉ ላሉ ደላሎች በር በመክፈት የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲሰፍን መንገድ ይከፍታል፡፡ ሕግ ያስከብራሉ የተባሉት ፖሊሶችም ይህን ሕገወጥ ተግባር አይመለከተኝም ካሉ፣ የት ሄደን አቤት እንበል? ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በጉዳዩ ላይ አፋጣኝ መፍትሔ ቢሰጡ፣ የመንግሥትም ሆነ የሕዝብ ሥራ ከመስተጓጎል ይድናል፡፡

  (አበራ ፋና፣ ከአዲስ አበባ)

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...