በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ አገልግሎት የአንድ መቶ ዓመታት ዕድሜ እንዳለው ይነገራል፡፡ በቅርቡ 40ኛ ዓመቱን ያከበረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ያሠራጨውን መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ አገልግሎት በባህር ላይ በሚደረግ ጉዞ ለሚደርስ የእሳት አደጋ ዋስትና በመስጠት የተጀመረ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው የሚታመነው ይህ የቢዝነስ ዘርፍ በኢትዮጵያ የአንድ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ያለው ቢሆንም፣ አገልግሎቱ የዕድሜውን ያህል የጐለበተ ነው ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡ በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻም እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በተለያዩ መመዘኛዎች ሲፈተሽ ኋላቀር መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ ዓመታዊ ዕድገቱም ቢሆን ቀርፋፋ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ ያለው ችግር ብዙ የሚተች ነው፡፡ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚሰጡት የኢንሹራንስ የአገልግሎት ዓይነቶችም እጅግ ውስን ሆነው መገኘታቸው ኢንዱስትሪው በተገቢው ደረጃ ዕድገት እንዳያሳይ አድርጓል፡፡ የባለሙያ እጥረት ያለበት መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታጥቆ ከመሥራት ይልቅ በተለመደው መንገድ መጓዝን የመረጡ እስኪመስል ድረስ አሁንም በዚያው መንገድ እየተጓዙ መሆኑም የኢንዱስትሪውን ደካማነት ያሳያል፡፡ አንድ በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት እንደሚየሳየው፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያልታጠቁ ናቸው፡፡ ከቴክኖሎጂው ራቅ ብለው የቆሙም ስለመሆናቸው አመልክቷል፡፡ በንፅፅርም ባንኮች አሁን የደረሱበትን ደረጃም አመላክቷል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባንኮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የተጓዙትን ርቀት ያህል እንኳን አለመጓዛቸውን ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የዕድሜውን ያህል አልጐለበተም የሚል እምነት የሚያስጨብጠው ሌላው መገለጫ ደግሞ፣ ከሌሎች አገሮች የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪዎች ጋር ያለው የሰፋ ልዩነት ነው፡፡ በተለይ በኢንዱስትሪው እጅግ መሠረታዊ የሚባለው የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ኢትዮጵያ ውስጥ በእንፉቅቅ የሚጓዝ ነው፡፡ በመቶ ዓመት ዕድሜው የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ስድስት በመቶ እንኳን አልሞላም፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን የሕይወት ኢንሹራንስ ከጠቅላላው የኢንሹራንስ ሽፋን 60 በመቶ ያህሉን ይይዛል፡፡ በኢትዮጵያ ከጠቅላላ የኢንሹራንስ ሽፋን ውስጥ 95 በመቶው የሚሸፈነው ከሕይወት ኢንሹራንስ ውጭ በመሆኑ፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ያለበትን ደረጃ በሚገባ ያሳያል፡፡
በአፍሪካ ደረጃም ቢሆን ከጠቅላላ ኢንሹራንስ ውስጥ የሕይወት ኢንሹራንስ በአማካይ ደርሶብዎታል ተብሎ ከሚጠቀሰው አኃዛዊ መረጃ ጋር ሲነፃፀርም የኢትዮጵያ ደረጃ ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ በዚህም ረገድ አገሪቱ አፍሪካውን ላይ እንኳን መድረስ ያለመቻሏን ይጠቁማል፡፡
እውነት እንነጋገር ከተባለ ዛሬም ድረስ ኢንሹራንስ ሲባል የተሽከርካሪና የእሳት አደጋን ብቻ የሚመለከት ሆኖ ዘልቋል፡፡ ይህንን የጠበበ አመለካከት አስፍቶ ለመመልከት ወይም አገልግሎቱን ለማሳደግ ያለው እንቅስቃሴም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ኢንዱስትሪው የሚገለጽበትን ደረጃ የሚያሳይ ሥራ እየተሠራ ያለመሆኑም ግልጽ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው አሁንም እየሰጠ ባለው ውስን አገልግሎትም ቢሆን የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አትራፊ ሆነው እየዘለቁ ናቸው፡፡
የበለጠ ቢሠሩ ግን የበለጠ ማትረፋቸው አይቀርም፡፡ ቢሆንም ይህንን እንኳን ታሳቢ አድርጐ ከመሥራት ይልቅ አሁንም በተሽከርካሪዎች ወይም በሞተር ኢንሹራንስ ሽፋን ላይ ብቻ ሲፏከቱ መመልከት የኢንዱስትሪውን ዕድገት ወደኋላ እየጐተተው ነው፡፡
የኢንዱስትሪው ወደኋላ መጐተት ብቻ ሳይሆን ዜጐች በኢንሹራንስ ሊያገኙ የሚችሉ ጥቅሞችን እንዳያገኙ ተደርጓል፡፡ ይህ በማን? በምን ምክንያት? የሚል ጥያቄ ቢቀርብ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ጣት ብንቀስር ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲያውም ኢንዱስትሪውን የሚመሩ ባለሙያዎችም ቢሆኑ አገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የተንቀረፈፈ ጉዞ ተጠያቂ አይሆኑም ልንል አንችልም፡፡ የእነሱም ድርሻ ቀላል አለመሆኑን መተማመን ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ለኩባንያዎች ዕድገትና ውድቀት የኩባንያ መሪዎች ድርሻ ወሳኝ ነውና የእነሱም ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡
የኩባንያዎች ባለቤቶችም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ በአገራችን ካሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች 40 በመቶ አካባቢ የሚደርሰውን የገበያ ድርሻ የያዘው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት መሆኑን ስናስብ ደግሞ፣ ለአገሪቱ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከፍታ አለመጨመር መንግሥትም ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ቀሪዎቹ 16 የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ በሺዎች በሚቆጠሩ ባለቤቶች ወይም ባለአክሲዮኖች የተፈጠሩ በመሆኑ፣ ባለአክሲዮኖችም ራሳቸው ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ኩባንያዎቻቸው እንዲመነደጉ ያደረጉት ጥረት ምን ያህል ነው? ካላሉ እነዚህም ተጠያቂ ናቸው፡፡ ስለዚህ መጠኑ ይለያይ እንጂ እነዚህ የተጠቀሱ አካላትን ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው በመሆኑ፣ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አዝጋሚ ጉዞ ተጠያቂዎች መሆናቸው አይቀርም፡፡
ስለዚህ ዘርፉን ለማሳደግ ቢያንስ ከአፍሪካውያን ጋር ተወዳዳሪ ለመሆንና የበለጠ እንዲሠራና የኢንሹራንስ ተጠቃሚ ዜጐች ለማሳደግ ከተፈለገ አሁንም ከፍተኛ ዕድል አለ፡፡ ይህንን ዕድል ለመጠቀም ደግሞ ኅብረተሰቡን ያገናዘበ አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍና የሠለጠነ የሰው ኃይል ያሻል፡፡
እጅጉንም ደግሞ ዜጎች የኢንሹራንስ አስፈላጊነትንና ጠቀሜታን ያውቁ ዘንድ በርትቶ መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ የኢንሹራንስ ጠቀሜታን በሚገባ ሳያሳውቁ አገልግሎቱን ለመስጠት መፍጨርጨር አንድ ዕርምጃ እንኳን ስለማይራመድ፣ ኩባንያዎች ይህንን አስቀድመው አገልግሎታቸውን ያስፉ፡፡ ተወዳዳሪ ይሁኑ፡፡