በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በቀን ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ እየሆነ ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡ በየዓመቱ ዕድገት የሚታይበት ይህ ዘርፍ፣ አሁንም ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ነው፡፡ ከዕድገቱ ጋር ተያይዞም የቱሪዝም ዘርፉ ከተለያዩ ክንውኖች ጋር ተቀናጅቶ እንዲዘጋጅና በአዲስ ጽንሰ ሐሳብ እየተሠራበትም ይገኛል፡፡ ይህም ‹‹ማይስ›› ወይም በእንግሊዝኛ ምኅፃረ ቃል (MICE) በሚል የሚታወቀው ይህ አዲስ የቱሪዝም ጽንሰ ሐሳብን ተቀብለው እየተገበሩ ያሉ አገሮች የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን እያሳደጉበት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ከሆኑ ስብሰባዎች ጋር ተጣምሮ የሚካሄደው ይህ የቱሪዝም ዘርፍ፣ በአፍሪካ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገሮች ቀዳሚ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በዚህ ዘርፍ ገና አንድ ብላ ልትጀምር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀትና በማማከር ሥራ ላይ የተሰማራው ኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ይህን አዲስ የቱሪዝም ጽንሰ ሐሳብ በኢትዮጵያ ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት እንዳጠናቀቀ፣ የኦዚ መሥራችና ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ይገልጻሉ፡፡ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተገለጸውን ቱሪዝም ዘርፍ ‹‹ማይስ ኢስት አፍሪካ ፎረምና ኤክስፖ›› በሚል ስያሜ ከሰኔ 2 እስከ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ ከሌሎች ኤግዚቢሽኖችና የቱሪዝም ዘርፍ በተለየ የሚታይ ነው ስለተባለው ኤክስፖና ማይስ ስላለው ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴና በአዲስ አበባው ዝግጅት ዙሪያ ዳዊት ታዬ አቶ ቁምነገርን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ ነው የተባለው የቱሪዝም ዘርፍ ወይም ማይስ ምን ማለት እንደሆነ ቢገልጹልን?
አቶ ቁምነገር፡- (MICE) ትርጉሙ ሚትንግስ፣ ኢንሴንቲቭስ፣ ኮንፈረንስ ኤንድ ኤግዚቢሽን ማለት ነው፡፡ ይኼ በዓለም ላይ አዲሱ የቱሪዝም ክንፍ ነው፡፡ ለምሳሌ ቱሪዝም ለሁለት ተከፍሎ የሚታይ ነው፡፡ ቢዝነስ ቱሪዝም የምንለው አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ሌዠር ቱሪዝሞች የሚባሉት ናቸው፡፡ ሌዠር ቱሪዝም የምንለው የቱሪዝም መዳረሻ የሚባሉትን መመልከት ነው፡፡ እኛ ስንከተል እንደነበረው አክሱምን፣ ላሊበላን የመሳሰሉትን የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደምናሳየው ማለት ነው፡፡ ይኼኛው ግን በፊት በፊት እንደ ቱሪዝም አይወሰድም ነበር፡፡ አሁን ራሱን ችሎ ወጥቷል፡፡ ኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚገባው ማይስ ውስጥ ነው፡፡ ኮንፈረንስ ቱሪዝም የማይስ አንድ አካል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኮንፈረንስ ቱሪዝም አይባልም፡፡ በዓለም ላይ የሚጠራው ‹‹ሚቲንግ ኢንዱስትሪ›› ተብሎ ነው፡፡ እዚህ እኛ ጋር ስለተለመደ ነው ኮንፈረንስ ቱሪዝም እያልን የምንናገረው እንጂ ሚቲንግ ኢንዱስትሪ ወይም ኢንዱስትሪ ማይስ ነው የሚባለው፡፡
ሪፖርተር፡- እስካሁን ግን ኮንፈረንስ ቱሪዝም እንጂ ማቲንግ ቱሪዝም ወይም ሚቲንግ ኢንዱስትሪ የሚል ነገር አልነበረም፡፡ ይህ እየተቀየረ ነው ማለት ነው? አዲሱ የቱሪዝም ዘርፍ የሚያስገኘውንስ ጥቅም እንዴት ይገለጻል? ይዘቱስ?
አቶ ቁምነገር፡- ይህ በዓለም ላይ አዲሱ የቃል አጠቃቀም ነው፡፡ ሚቲንግ ኢንዱስትሪ ብሎ የሚጠቀም የለም፡፡ ‹‹ማይስ›› በዓለም ደረጃ ግን ይታወቃል፡፡ እዚህ አገር ግን ገና ነው፡፡ ራሱን የቻለ አንድ ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህ ያደጉ አገሮች ከሆነ ጊዜ በኋላ ከሌዠር ቱሪዝም ይልቅ የቢዝነስ ቱሪዝም ነው የሚያዋጣው ወደሚል ገቡ፡፡ ለምሳሌ በገንዘብ ፍሰት ደረጃ ከሚቲንግ ጋር በተያያዙ ኢግዚቢሽኖችና ኢቨንቶች የሚመጡት ሰዎች የሚያጠፉት ገንዘብ ከፍተኛ ነው፡፡ ከሌሎች ተመሳሳይ ዝግጅቶች ጋር ሲነፃፀርም ከ500 እስከ 600 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ስለዚህ ስብሰባዎች፣ የማነቃቂያ ጉዞዎች፣ ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን በጥምረት ይዞ የሚዘጋጀው ኤክስፖ ወይም ‹‹ማይስ›› ጥቅም ጎልቶ እየወጣ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አገሮች ማይስን የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጭ ማድረግ ጀመሩ፡፡ በነገራችን ላይ በእኔ እምነት እንደ ኮንስታልት፣ እንደ ኦርጋናይዘርና ይህንን ሐሳብ እንዳቀረበ ሰው የዚህች አገር የውጭ ምንዛሪን ክፍተት ይፈታዋል ብዬ የማምነው፣ የማይስ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማይስ ላይ ብትሠራ የውጭ ምንዛሪ ችግሯን ትፈታለች ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌሎች የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዘዴዎች እንዳሉ ሆነው የማይስ ኢንዱስትሪ ቢሠራበት የውጭ ምንዛሪ ችግርን ከመታደግ አኳያ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ማይስን በኢትዮጵያ በትክክል ለመተግበር መሠረተ ልማት አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ ኮንቬንሽን ሴንተሮች ዓይነት ማለት ነው፡፡ ሆቴሎች ያስፈልጋሉ፡፡ እንደሚታወቀው አሁን ሆቴሎች በብዛት እየመጡ ነው፡፡ ይህ መልካም ዕድል ነው፡፡ ሆቴሎች መምጣታቸው ብቻውን ግን ዋና ነገር አይደለም፡፡ እነሱን መመገብ የምትችለው በሚቲንግ ብቻ ነው፡፡ መቼም በአገራችን እንደ አንድ ምሳሌ የሚወሰደው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ነው፡፡ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ የሆቴሎች ገበያ የሚደራው በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወቅት ነው፡፡ ይህ ጊዜ ግን አሁን አብቅቶለታል፡፡
ሪፖርተር፡- ለምን?
አቶ ቁምነገር፡- የሆቴሎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ነው፡፡ የሆቴሎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ክፍሎቻቸውን መቶ በመቶ ማስያዙ ቆመ፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወቅት ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ አልጋቸው አልተያዘም፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ የሚገኙት ታዳሚዎች ቁጥር ከቀድሞ ላይለይ ቢችልም፣ አሁን ያሉት ሆቴሎች ስለበዙ የተፈጠረ ክፍተት ነው፡፡ ስለዚህ ድሮ 100 እና 150 በመቶ የሚሸጡ ክፍሎች አሁን ሙሉ ለሙሉ አልተያዙም፡፡ ትልልቅ የምንላቸው ሆቴሎች ሳይቀሩ 70 በመቶውን እንኳን ያልሸፈኑ ናቸው፡፡ 20 እና 30 ክፍሎቻቸውን ብቻ አስይዘው የተቀመጡ ሆቴሎች ነበሩ፡፡ ይህ የሚያሳየው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሆቴሎች ዋጋ የመቀነስ አዝማሚያ መኖሩን ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ሆቴሎቹ ይጨምሩና ሆቴሎቹ ሐሳብ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን ክፍተት ለመሸፈን ጭምር አገሪቷ ራሱን የቻለ የማይስ ቢዝነስ ቀርጾ ሥራ ላይ ማዋል አለባት፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ ናሽናል ኮንቬየሽን ቢሮ ያስፈልጋታል፡፡
ሪፖርተር፡- የዚህ ቢሮ ሥራ ምንድን ነው?
አቶ ቁምነገር፡- ይህ ቢሮ ዋነኛ ሥራው የማመቻቸት ሥራ ነው የሚሠራው፡፡ በግል ዘርፉና በመንግሥት መካከል ገብቶ የሚቲንግ ኢንዱስትሪው የተመቻቸ ሒደት እንዲኖረው ነው የሚያደርገው፡፡ ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ጨረታ ይወጣል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጨረታ እንደሚወጣ ግን ብዙ ሰው አያውቅም፡፡ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት የሚወጡ ጨረታዎችን የሚከታተል አካል ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ አይታወቅም፡፡ በዚህ የሥራ መስክ ኢትዮጵያ ባለቤት የላትም፡፡ ስለዚህ ማን ሄዶ ይወዳደራል፡፡ እንዲህ ባለው ጨረታ ተወዳድሮ የአምስትና የአሥር ሺሕ ሰው ቢዝነስ እያለ፣ 30 እና 40 ሚሊዮን ዶላር በአንዴ ማግኘት እየቻልክ አልተሠራበትም፡፡ ሆቴሎቹን ይዞ እንደ አገር ጨረታ ውስጥ የሚገባ የለም፡፡ አሁን ያለው የቱሪዝም ኦርጋናይዜሽን በሥሩ ናሽናል ኮንቬሽን ቢሮ ወይም የማይስ መሥሪያ ቤት ማቋቋም አለበት የምንለውም እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን ለማሠራት እንዲቻል ነው፡፡ ይኼን ሲያቋቁም መሪው መንግሥት ይሆንና አንቀሳቃሾቹ ግን የግል ዘርፉ ይሆናል፡፡ ይህ አንደኛው መንገድ ነው፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ አገሪቷ የማይስ ኤክስፖ ያስፈልጋታል፡፡ የማይስ ኤክስፖ ደግሞ ትልቁ ጥቅም በዓለም ላይ ስብሰባዎችን የሚሰጡን ሰዎች፣ አሁን እኛ ከመላው ዓለም በማሰባሰብ ለማስመጣት እንደጀመርነው ዓይነት ሥራ መሥራት ነው፡፡ ለምሳሌ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ፍላጎት ያላቸው የማይስ ሚዲያዎች አሉ፡፡ የእነሱን ቻናል እንጠቀምና የስብሰባ አዘጋጆችን ወደዚህ በማምጣት መሥራት ነው፡፡ ለምሳሌ ከ50 እስከ 100 የሚሆኑ ሰዎችን በዚህ ዓመት ሰብስበን እናመጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ ሰዎች ሥራቸው ምንድን ነው? ወደ አዲስ አበባ ስታስመጡዋቸው በዋናነት ምን ለመከወን ይችላሉ ተብሎ ታስቦ ነው?
አቶ ቁምነገር፡- እነዚህ ሰዎች ከ300 እስከ 40,000 ሰው በዓመት ማሰባሰብ የሚችሉ ናቸው፡፡ የዚህን ያህል ሰዎች ማንቀሳቀስ የሚችሉ ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከምናስመጣቸው ውስጥ አምስቱን እንኳን ብንጠቀምባቸውና ለአገሪቱ 2,000 እንግዶችን ሊያመጡ ቢችሉ፣ አገሪቷ ከዚህ ኤክስፖ ከ50 ሚሊዮን እስከ 60 ሚሊዮን ዶላር ታገኛለች፡፡ ስለዚህ ይህ የአገሪቷ ቀጥታ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ይሆናል፡፡ መንግሥትም ሊጠቀምበት የሚገባው ነው፡፡ እኛ በበኩላችን ይህንን መልካም አጋጣሚ አገር በሚጠቅም መልኩ እንዲተገበር ለማድረግ ስንሠራበት ቆይተናል፡፡ በዚህ ረገድ ለአንድ ዓመት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ለማሳመን ብዙ ጥሬያለሁ፡፡ አሁን ከዚህ ወር ጀምሮ ሐሳቡን ተቀብለው ድጋፍ እንዲደረግልን እየተደረገ ነው፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ደብዳቤ ጽፎልናል፡፡ ደብዳቤው የዝግጅቱን አስፈላጊነትና በዚህም ዝግጅት የሚገኘው ጥቅምና መልካም ዕድል ጭምር ይገልጻል፡፡ በዚህ መነሻነትም የውጭ ጉዳይና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንም ደብዳቤ ጽፎልናል፡፡ ይህንን ሥራ መሥራት ያለበት የግል ዘርፉ ነው፡፡ መንግሥት ሊያስተዳድረው ወይም ለመሥራት ቢሞክረው ይቸግረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለኢስት አፍሪካ ፎረምና ኤክስፖ ዝግጅታችሁ እስካሁን ምን ያህል ኩባንያዎች ይመጡልናል ብላችሁ ታስባላችሁ? እስካሁንስ ትላልቅ ስብሰባዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ሚና አላቸው ከተባሉት ውስጥ ምን ያህል ለመሳተፍ የተመዘገቡ አሉ?
አቶ ቁምነገር፡- እስካሁን ወደ 60 የሚሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስብሰባዎች ላይ ወሳኝ ናቸው ከሚባሉ ሰዎችን በዚህ ዓመት እናመጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ ሰዎች ከኤግዚቢሽኑ ውጭ የሚመጡ ናቸው?
አቶ ቁምነገር፡- ኤግዚቢሽኑ ላይ ነው የሚመጡት፡፡ እዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ተገኝተው ስምምነት እንዲያደርጉ ነው የሚፈለገው፡፡ ከሆቴሎች፣ ከኢሲኤ፣ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ንግግር እንዲያደርጉ እ.ኤ.አ. ጁን 9 ቀን 2015 እዚህ እናስመጣቸዋለን፡፡ ምዝገባም ጨርሰናል፡፡ እነዚህን ሰዎች ወጪያቸውን ችለን ነው የምናመጣቸው፡፡ በነገራችን ላይ በአፍሪካ ትልቁ የማይስ ኤክስፖ የደቡብ አፍሪካው ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ የማይስ የሚባል ኤክስፖ የለም፡፡ ደቡብ አፍሪካው ብቻ ነው የሚደረገው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውሰጥ የሚመጣው መቶ ሰው ብቻ ነው፡፡ ይኼ ማለት አሥር ዓመት የሞላው ኤክስፖ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በማይስ ዝግጅት ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው? ለምን?
አቶ ቁምነገር፡- የእነዚህ ባለሙያዎች ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ውድ ናቸው፡፡ እነሱን አሳምኖ ወደዚህ ማምጣት ትልቅ ሥራ ነው፡፡ አሁን በእኛ ዝግጅት ላይ የሚገኙት እንዲህ ያሉት ናቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን አብዛኛዎቹ ሆቴሎች፣ የኮንቬንሽን ቦታዎች በኤክስፖ ላይ ይሳተፋሉ፡፡ እነ ኢሲኤ እና አፍሪካ ኅብረት ተሳታፊ ናቸው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሰዎች በሙሉ በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ አወንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ክልሎችም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ውድድሩ እንደዛ መሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ስብሰባ ባሸነፍክ ቁጥር ከክልሉ ጋር ነው የምንወዳደረው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ከሩዋንዳና ከታንዛኒያ ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ የማይስ ኢስት አፍሪካ ስብሰባ ሲሆን የደቡብ አፍሪካ ልዑካን፣ የሩዋንዳ፣ የኡጋንዳ፣ የዙምባብዌ፣ የሞዛምቢክ፣ የሱዳን የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች እኔ የማመጣቸውን ሰዎች አሳምነው ወደ አገራቸው ለመውሰድ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በእኔ ዕቅድ መሠረት እዚህ ኤክስፖ ላይ ኢትዮጵያ አሥሩን ሰዎች ማሸነፍ ብትችል፣ ስልስና ሰባ ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ትችላለች ማለት ነው፡፡ ይህ ነው የማይስ ኤክስፖ የሚባለው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚጠቅመው ይኼ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የግል ባለሀብቶች የማይስን ኤክስፖ መክፈት አለባቸው፡፡ የሥልጠና መርሐ ግብሮችን፣ መሠረት ልማቶችን ማልማት የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሥራ ነው፡፡ ይሄ ጎን ለጎን እሄደ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ማይስ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለማይስ ጠቀሜታነት የዚህን ያህል የሚነገር ከሆነ በእናንተ ዝግጅት ላይ ከሚመጡ የማይስ ባለሙያዎች ውስጥ የምትፈልጉትን ዓላማ ሊያሳኩ የሚችሉ ብላችሁ የምታስቡዋቸው አሉ? እነማንስ ይመጣሉ?
አቶ ቁምነገር፡- የኢንተርናሽናል ኮንፍረንስ ኤንድ ኮንግረስ ፕሬዚዳንቷ ትመጣለች፡፡ በእኛ ዝግጅት ላይ የጽሑፍ አቅራቢ ናት፡፡ የኮንፈረንስ አሶሴሽን የሚባለውና መሠረቱን አሜሪካን አገር ያደረገ ዋና ጸሐፊው ይመጣል፡፡ የአይኤምኤክስ ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዚዳንት ይመጣል፡፡ ይህ አይኤምኤክስ ማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ሄዶ የሚካፈልበት ትልቁ ኤክስፖ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ጀርመንና አሜሪካ አገር ያለው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ በጣም ታላላቅ ውሳኔ ሰጪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እኛ መሥራት የፈለግነው አገሪቷ የማይስ ኢንዱስትሪ ፕሮሞተር እንድትሆን፣ ከዚህ ተጠቃሚ እንድትሆንና የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷን መፍትሔ የምትሰጥበት ትልቅ ጉልበቷ እንዲሆን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በማይስና በአገራችን በሚታወቀው ኤግዚቢሽን መካከል ያለው ልዩነት እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
አቶ ቁም ነገር፡- አዎ ልክ ነህ ልዩነት አለው፡፡ ማይስ ኤግዚቢሽንና ሌላው የሚለየው የኤግዚቢሽኖች ኤግዚቢሽን ማለት ነው፡፡ ኤግዚቢሽን አዘጋጆችን የሚያመጣ ኤግዚቢሽን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖችን የሚያዘጋጅ የፈረንሣይና የእንግሊዝ ኩባንያዎች አሉ፡፡ አፍሪካ ውስጥ ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ሰው ነው የምናመጣው፡፡ ኤግዚቢሽኖች ሲዘጋጁ የሚያወጡት ወጪ እያደገ ነው የሚመጣው፡፡ እነሱ የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ ነው ማለት በተመሳሳይ ስብሰባውም እንደዚህ ነው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ እኛ ኤክስፖ ላይ የሚገቡት ሆቴሎች፣ አየር መንገዶች፣ የኮንፍረንስ አደራጅና አቅራቢዎች፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ ኤቨንት ማኔጅመንት ኩባንያዎችና ኤግዚቢሽን አዘጋጆች (እኔን ጨምሮ) ናቸው፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነቱ ዝግጅት የኤቨንቶች ኤቨንት ነው የሚባለው፡፡ እነዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ ባለሙያዎችና ኩባንያዎች በእጃቸው ያለውን ስብሰባ የት ማካሄድ ይኖርብኛል ብለው የሚመርጡበትና አገር የሚመርጡበት ሆቴሎችን የሚያወዳድሩበት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ለምሳሌ አንድ ስብሰባ ወይም ኤግዚቢሽን የሚያዘጋጅ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ይኼ ስብሰባ ኢትዮጵያ ውስጥ ይደረጋል ይላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረገው ስብሰባ ሆቴሎችን ያወዳድራል ማለት ነው?
አቶ ቁምነገር፡- እኛ ነን የምናሳምነው፡፡ እሱ እጁ ላይ ቢዝነስ ይይዛል፣ ኤግዚቢሽን ሊያዘጋጅ ይፈልጋል አስተማማኝ ቢዝነስ አለው፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብህ በዓለም ላይ የሚካሄዱት አብዛኛዎቹ ኮንፈረንሶችና ኤግዚቢሽኖች ፈንድ አላቸው፡፡ ፈንዱ ወጪያቸውን የሚሸፈን ነው፡፡ ገንዘብ ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ ለምሳሌ እነ ቢልጌትስን እንጥቀስ፣ ቢልጌትስ አፍሪካ ውስጥ ስብሰባ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ስብሰባው ከሕክምና ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል እንበል፡፡ ለዚህ ስብሰባ ዓመቱ መጀመርያ ላይ በጀት ይመድብና 1,000 ሐኪሞችን አፍሪካ ውስጥ እንድትሰበስቡልኝ እፈልጋለሁ ይላል፡፡ ልክ እንደዚህ ሲል ፋይናንስ ነው የሚመደበው፡፡ በቢልጌት ስም ኮንፈረንሱን ማኔጅ የሚያደርጉ ኢንተርናሽናል ኩባንያዎች አሉና እነሱ ስብሰባውን አፍሪካ ውስጥ የት ነው የሚደረገው ብለው፣ ማይስ ኤክስፖ የት ነው ያለው ብለው ያጠናሉ፡፡ አንዷ ኢትዮጵያ ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይመጡና ሆቴሎችንና የማዕከላት ባለቤቶችን አንድ ላይ ማግኘት አለባቸው ማለት ነው፡፡ ከዚያ ስብሰባውን ያደርጋሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ማይስ ኤክስፖ ወሳኝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ ጊዜ ኢንተርናሸናል ስብሰባዎች ይደረጋሉ፡፡ እስካሁን እንዴት ነበር አዲስ አበባ ውስጥ የሚደረጉት? የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ሲደረጉ እናያለን፡፡ ይህ እንዴት የሚመጣ ነበር? ኢትዮጵያስ እንዴት ነበር ስትመረጥ የነበረው?
አቶ ቁምነገር፡- አብዛኛውን ጊዜ የእኛን አገር ስብሰባዎች ስትመለከት በመንግሥት በኩል የሚመጡ ናቸው፡፡ ኢኮኖሚ አድጓል ብለህ፤ ቡና ላይ እኔ ያለኝ ተሳትፎ ከፍተኛ ስለሆነ ዓለም አቀፉን የቡና ጉባዔ ለማዘጋጀት ማኅበሮችን አሳምነህ ጭምር ነው የምታመጣው፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በራሱ በኩል ያመጣቸው ስብሰባዎች ናቸው፡፡ እንዲህ የሚመጡ ስብሰባዎች አንዳንድ ጊዜ ወጪ ሁሉ አላቸው፡፡ ሆስት ለማድረግ ወጪ ትከፍላለህ፡፡ ለምን እኔ የመሪዎቹን ወጪ አልከፍልም ብለህ የምታመጣቸው ስብሰባዎች አሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ገንዘቡ በደኅንትና በገጽታ ግንባታ ያልቃል፡፡ እርግጥ ነው እንዲህ ባሉ ዝግጅቶች ገጽታ ትገነባለህ፣ ወጪ ግን ያስወጣሃል፡፡ በዚህ መንገድ የሚመጡ አሉ፡፡ በማይስ ግን በተለየ የሚመጣ ነው፡፡ የበለጠ ገቢ የሚገኝበትም ይሆናል፡፡ ዝግጅቱ በተለያየ ዘርፍ ጋር የተቀናጀ በመሆኑ ጥቅሙ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ እንደ ኖኪያና ሳምሰንግ ያሉ ኩባንያዎች ሁለትና ሦስት ሺሕ ሰው ይዘው ከአገር አገር ይዘዋወራሉ፡፡ እነዚህን የሚያንቀሳቅሱት ኢንሴንቲቭ ትራቭል ሆስት ባየሮች ናቸው፡፡ ይህንን ኮንትራት የወሰዱትን ሰዎች ለቅመን ነው የምናመጣቸው እንግዲህ፡፡ ይኼ መንገድ አንዴ ሥራ ላይ ከዋለ ምናልባት ይኼ ስብሰባ ሊመጣ ይችላል ብለህ ሳይሆን እንደ ቢዝነስ በወር ውስጥ አምስትና ስድስት ስብሰባዎች ይኖሩሃል፡፡ ይህም ለአገሪቱ ትልቅ ገቢ ያስገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በሰኔው ዝግጅታችሁ ኤግዚቢሽንም አለ፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን ምን ያህል ተሳታፊ ይኖራል?
አቶ ቁምነገር፡- በቂ ታሳተፊ ይመጣል፡፡ እኛ የምናስገባው ከ70 እስከ 75 ኩባንያዎችን ብቻ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሆስት ባየሮችና ውሳኔ ሰጪ ሰዎችን ደግሞ እስከ መቶ እናመጣለን፡፡ በአገር ውስጥ ቡኪንግ የሚሰጡ ሰዎች ደግሞ 350 እናመጣለን፡፡ ከምሥራቅ አፍሪካም የሚመጡ አሉ፡፡ ስለዚህ የሚፈለገውን ኔትወርክ እንፈጥራለን፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ባለው ኤግዚቢሽን ሕዝብ አይገባም፡፡ ማይስ ኤክስፖ ላይ አይፈቀድም፡፡ ከሚቲንግ ቢዝነስ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦችና ተቋማት ብቻ ነው የምናስገባው፡፡ 3,000 ሰው እንኳን ላይሞላ ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ቁምነገር፡- ሆስት ባየሮቹ በቀጠሮ የሚመጡ ስለሆነ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኤግዚቢሽን ለንግድና ኢንቨስትመንት መቀላጠፍ ወይም ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታመናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁነኛ የኤግዚቢሽን ሥፍራ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ለዚህ የሚሆን ቦታ የላትም፡፡ እናንተ ያሰባችሁት ዝግጅት ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም?
አቶ ቁምነገር፡- በትልቅም ሆነ በአነስተኛ ደረጃ ኤግዚቢሽኖች ማደግ አለባቸው፡፡ የኤግዚቢሽኖች መጠን ትልቅ መሆናቸው ሳይሆን ውስጣቸው ያለው የገንዘብ መጠን ነው ወሳኙ፡፡ ለምሳሌ 2,000 እና 3,000 ሰዎችን አምጥተን 50 ሚሊዮን ዶላር ልናገኝ እንችላለን፡፡ ኤግዚቢሽኖች ሆቴል ውስጥ ሊዘጋጁ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ብዙ ኤግዚቢሽኖች ሆቴል ውስጥ ነው የሚዘጋጁት፡፡ ፊት ለፊት የሚደረጉ የቢዝነስ ምክክሮች የሚደረግባቸው በመሆኑ ሚስጥራዊ ናቸው፡፡ ከሚመለከታቸው ውጭ ላይገቡ ይችላሉ፡፡ ቢዝነሱን የሚመለከታቸው ሰዎች ነው የሚከፈትላቸው፡፡ ይኽም ቢሆን ኤግዚቢሽን ማዕከላት በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አዲስ የአፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር ሊገነባ መሆኑ ተስፋ ነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደርም ትልቅ ኮንፈረንስ ሴንተር ሊገነባ በጀት ሁሉ አፅድቋል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እንደ ኢሲኤ ያሉ አዳራሾች አሉን፡፡ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽንም ልትጠቀምበት ትችላለህ፡፡ በነገራችን ላይ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባዶውን ነው ያለው፡፡ ሁለትና ሦስት ሺሕ ሰዎች የሚያስተናግደው ይህ አዳራሽ፣ በሳምንቱ ሦስት አራት ስብሰባዎችን መሥራት ነበረበት፡፡ ይህንን ልንጠቀም እንችላለን፡፡ ስለዚህ እንኳን አዲስ ባለንም መጠቀም አልቻለንም፡፡ መኖራቸው ግን ዘርፉን ያሳድጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን እዚህ ለማካሄድ በተቋም ደረጃ በጨረታ መሳተፍ ግድ ነው ብለዋል? ግን ምን ያህል ተጠቃሚ መሆን ይቻላል? እንዴት? ቢዝነሱስ አለ?
አቶ ቁምነገር፡- በዓለም ላይ የተለያዩ ማኅበራት አሉ፡፡ ለዚህ ዘርፍ ትልቅ ቢዝነስ የሚሰጡት እነዚሁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የሕግ፣ የሴቶችና ወጣቶች ማኅበራት የሚባሉ አሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ወደ አምስትና አሥር ሺሕ ሰዎችን የሚያሳትፉ ስብሰባዎችን ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት የሚያወጡት ገንዘብ የማኅበር ስለሆነ ስብሰባውን ለማካሄድ ጨረታ ያወጣሉ፡፡ ስብሰባው በምሥራቅ አፍሪካ የሚካሄድ ሲሆን ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ሩዋንዳን ሊመረጡ ይችላሉ፡፡ ከእኛ ወገን ግን ማንም ሄዶ የሚወዳደር የለም፡፡ ባለቤት የለውም፡፡ ኬንያና ሩዋንዳ ባለቤት አለው፡፡ ስለዚህ ቢዝነሱን ይወስዱታል፡፡ ይህንን ለማምጣት ነው የምንሠራው፡፡ ዘርፉ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስም ነው፡፡ እንደ አይሲሲኤ ትንበያ በዓለም ዙሪያ ሃያ አራት ሺሕ ቋሚ የማኅበራት ጉባዔዎች የሚካሄዱ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ለእነዚህ ስብሰባዎች በዓመት 280 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ የሚያደርጉ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ማኅበራት የተወሰኑትን እዚህ ማምጣት ብትችል የሚገኘውን ጥቅም አስብ፡፡ በዩኤፍአይ (UFI) የኤግዚቢሽን ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ አሶሴሽን ትንበያ መሠረት ደግሞ 400 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወጪ ያላቸው ስብሰባዎችና 760 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወጪ የሚደረግባቸው ኤግዚቢሽኖች የሚከናወኑ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ አዳዲስ የሚፈጠሩ ገበያዎች ጥንካሬ በዘርፉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚለውጡ ይሆናል፡፡ የአፍሪካም የገበያ ድርሻ 3.3 በመቶ እና ከዚህም በላይ የሚያድግ ስለመሆኑ የሚተነብይ በመሆኑ፣ እነዚህን ስብሰባዎች ወደኛ ለማስመጣት መሠራት አለበት፡፡ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ታይላንድ፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ አሜሪካ፣ ቻይናና ሌሎችም ከፍተኛ ገቢ እያገኙበት ነው፡፡ የጉባዔዎች የገበያ ድርሻ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች በሚስተናገዱባቸው አካባቢዎች መሠረት የገበያ ድርሻቸው አውሮፓ 55 በመቶ፣ እስያና መካከለኛው ምሥራቅ 21 በመቶ፣ ሰሜን አሜሪካ 11 በመቶ፣ ደቡብ አሜሪካ ዘጠኝ በመቶ፣ አፍሪካ ሦስት በመቶና አውስትራሊያ ሁለት በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡
በኢትዮጵያ ከቱሪዝም የሚገኘውን የገቢ መጠንና በውጭ ምንዛሪ ረገድ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ መጠነ ሰፊ አቅም ያለው ነው፡፡ በአገሪቱ የወጪ ንግድ ስትራቴጂ መሠረት የቱሪዝም መስህቦችን ለማስፋፋት ትኩረት በማድረግ የቱሪዝም ሀብቶቻችንን በማሳየት የገጽታ ግንባታ ሥራን ለማከናወን የውጭ ባለሀብቶችን ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድም የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊያን የግሉ ዘርፍ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ከቅንጦት ተጓዦች ወቅታዊነት አንፃራዊ በሆነ መልኩ የቱሪዝም ዘርፉ ቋሚና አስተማማኝ አቋም እንዲኖረው ለማስቻል ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡