Tuesday, November 28, 2023

​አደናጋሪው ኪራይ ሰብሳቢነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት›› ጽንሰ ሐሳብ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ መደመጥ ከጀመረ ከአሥር ዓመት ዕድሜ በታች ቢሆንም፣ አሁን ግን የመዋቅሩ ተዋናዮችና የመንግሥት ሚዲያዎች የዕለት ተዕለት መግባቢያ ቋንቋ እስኪመስል የሚደመጥ ተራ ሐረግ ይመስላል፡፡

‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ ውስጥ በአሜሪካ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ልሂቃን የተፈጠረ መሆኑን የተለያዩ የጥናት ጽሑፎች ያረጋግጣሉ፡፡ በተለይም ጎርደን ቱሎክና አርኖልድ ሐርብርገር የተሰኙ የኦኮኖሚ ምሁራን ኪራይ ሰብሳቢነት የሚለው ሐረግ፣ ‹‹ፖለቲከኞችና ጥቂት ባለፀጋ ኮርፖሬቶች ሕዝባዊ የሆነ የአገር ሀብትን ለራሳቸው ጥቅም የሚቀራመቱበት ሥርዓት፤›› የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ እንዲይዝ አድርገውታል፡፡

‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› በሌላ ጽንሰ ሐሳብ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ አስቀድሞ ግን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኪራይ ሰብሳቢነትን ጽንሰ ሐሳብ ቅርፅን በመቀየር ለአፍሪካ ተስማሚ ነው ያሉት ጥናታዊ ምርምር ‹‹Dead Ends and New Beginnings›› በሚል የጥናት ጽሑፋቸው አቅርበዋል፡፡

የዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ማጠንጠኛ የኒዮሊበራል የኢኮኖሚ ሞዴል ለአፍሪካ የማይጠቅምና የተሻለው አማራጭ የልማታዊ መንግሥት አማራጭ መሆኑን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ በዚህ ውስጥም በመንግሥት የሚፈጠር ‹‹ኪራይ›› ልማትን ማፋጠን ብሎም የተመጣጠነ የሀብት ክፍፍልን ማስፈን እንደሚቻል የሚገልጽ ነው፡

በበለፀጉት አገሮች ኪራይ በመንግሥት ሳይሆን በግል ባለሀብቶች የሚፈጠር፣ የሚፈጠረው ኪራይ ላይም ተወዳዳሪ ባለሀብቶች እሴትን እየጨመሩ የሚቀባበሉበት መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ውስጥ የመንግሥት ድርሻ የንብረት ባለቤትነት መብቶችን ማስከበርና ውሎችን ማጽናት ብቻ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሚና እጅግ ውስን እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡

በተቃራኒው አቶ መለስ እ.ኤ.አ. በ2006 ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በልማትና በኢኮኖሚ ኋላቀር የሆኑ የአፍሪካ አገሮች የልማታዊ መንግሥትን ሞዴል በመከተል ራሳቸው ‹‹ኪራይ››ን በፖሊሲና በተግባር ቅድሚያ ወደሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች በማከፋፈል፣ የኢኮኖሚ ልማትን እንዲሁም ፈጣን ዕድገትን ማምጣት እንደሚቻል ተከራክረዋል፡፡

የአቶ መለስ መከራከሪያን በምሳሌ ለማሳየት የታክስ ማበረታቻዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የታክስ ማበረታቻዎችን ለኢኮኖሚው ጠቃሚ ለሆኑ ዘርፎች ብቻ በመፍቀድ፣ ይህም ማለት ከታክስ ጋር የተገናኘ ኪራይን በመፍጠር ባለሀብቶች በተዘጋጀላቸው ኪራይ የተነሳ የኪራይ ዕድሉን ባገኘው ዘርፍ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ወደ ትርፋማነት፣ እንዲሁም የእነዚህ በኪራይ የተሳቡ ኩባንያዎች ኢንቨስትመንት ሌላ ኪራይን በመፍጠር ፈጣን ዕድገትን ማስመዝገብ እንደሚቻል የሚከራከር ነው፡፡

ከላይ የተገለጸው ምሳሌያዊ ኪራይ በፖሊሲ አማካይነት ብቻ የሚመጣ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተመረጡ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ መንግሥት በራሱ በሚያደርገው ኢንቨስትመንት ኪራይን በመፍጠር፣ ሌሎች ደግሞ የተፈጠረው ኪራይ ላይ እሴት በመጨመር ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚከራከር ነው፡፡

አቶ መለስ በጠቀሱት በዚህ የኢኮኖሚ ሞዴል ላይ ከቀረቡ ትችቶች መካከል፣ የተፈጠረውን ኪራይ የፖለቲካ መዋቅሩ ወይም ኪራዩን የሚቀበለው አካል ሊያባክነው እንደሚችል፣ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ መንግሥታት ታሪካዊ ባህሪ ይህ ላይፈጠር ይችላል ብሎ ማሰብ እንደማይቻል የሚገልጽ ክርክር ይቀርባል፡፡

ይህንን ክርክር ከግምት ውስጥ ያስገባ ምላሽ የሚሰጡት አቶ መለስ፣ የሚፈጠረውን ኪራይ የሚሰበስቡ ተቋማት ወይም ግለሰቦች ከኪራዩ ጀርባ ቅጣት መኖሩን እንዲያስተውሉ የማድረግ ሚናን አብሮ መንግሥት እንደሚወስድ ተከራክረው ነበር፡፡

‹‹በመጀመርያ ኪራዩን ያባከነ ይቀጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በቀጣይ በመንግሥት የሚፈጠረውን ኪራይ ለማግኘት የቀድሞ የአፈጻጸም ውጤቱ መለኪያ መሥፈርት ይሆናል፤›› የሚል መከራከሪያ ምላሽን ያቀርባሉ፡፡

በሌላ አነጋገር ቀደም ሲል በተገለጸው ማሳያ የፖሊሲ ማበረታቸውን ያባከነ ወይም ከቀረጥ ነፃ ያስገባውን የካፒታል ዕቃ የቀረጥ ነፃው ለማይገባው ያስተላለፈው እንደሆነ በሕግ እንደሚጠየቅ አድርጎ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል የሚቀርበው መከራከሪያ የፖለቲካ መዋቅሩ ራሱ በሚፈጥረው ኪራይ ቢጠለፍስ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ መነሻ ደግሞ የሰው ተፈጥሮ በየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮት ውስጥ ቢሆንም፣ የራስን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከፍ ማድረግ ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ከአሜሪካ ምርጫ ጋር በተያያዘ ፖለቲከኞች ለምርጫ ቅስቀሳ ወጪ መሸፈኛ ሲሉ በባለፀጋ ኮርፖሬቶች እንደሚጠለፉ፣ እስካሁንም ይህንን ኪራይ ሰብሳቢነት ማስቀረት አለመቻሉን የሚያንፀባርቁ ጥናቶች በመከራከሪያነት ይቀርባሉ፡፡

አቶ መለስ ግን ከዚህ ሥጋት ነፃ መሆን የሚቻለው ይህንን ኪራይ በሚፈጥረውና በሚያስተዳድረው የመንግሥት ተፈጥሯዊ ባህሪ እንደሚወሰን ተናግረው ነበር፡፡

ልማት የፖለቲካ ሒደት ውጤት እንደሆነ ያንፀባረቁት አቶ መለስ፣ ልማታዊ መንግሥት ለዚህ ልማታዊ ተልዕኮ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይከራከራሉ፡፡ የልማታዊ መንግሥትን ቅቡል እንዲሆን ሊያደርጉት ከሚችሉ መገለጫዎቹ አንዱ ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም የልማታዊ መንግሥት መዋቅር ከግሉ ዘርፍ ተፅዕኖ የፀዳ፣ አቅም ያለው ፖለቲካዊ አመራርና በሙያው ብቁ የሆነ ቢሮክራት፣ እንዲሁም ጠንካራ የፖሊሲና የመከላከያ ኃይል የሚኖረው በመሆኑ የሚፈጠረው ኪራይ ተመልሶ አይወጣም የሚል ዝርዝር ያቀርባሉ፡፡

አቶ መለስ ይህንን በምሥራቅ እስያ አገሮች በቻይና፣ በጃፓን፣ በኮሪያና የመሳሰሉት አገሮች ተግባራዊና ውጤታማ የሆነ የኢኮኖሚ ሞዴል ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማስተካከያ በማድረግ፣ ከጥናትነት ወደሚመሩት መንግሥት የፖለቲካ ኢኮኖሚ መርህነት አሸጋግረውታል፡፡ በዚሁ መሠረት ወደ ተግባር የገባው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሞዴል ላለፉት አሥር ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ፈጣን ዕድገትን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

ይህንኑ እውነታም እንደ ዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF)  የመሳሰሉ ተቋማት አረጋግጠውታል፡፡

እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2015 የዓለም ባንክ ‹‹Ethiopia’s Great Run the Growth Acceleration and How to Pace it›› በሚል ርዕስ ያወጣው ሪፖርት የዚሁ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

የጥናት ቡድኑ መሪና የዓለም ባንክ ኢኮኖሚስት የሆኑት ላርስ ክረስተን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የተመዘገበበትን መንገድ ‹‹The Ethiopian Way›› ወይም የኢትዮጵያ መንገድ ይሉታል፡፡

ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ከፍተኛ ፍጥነት የሰው ኃይል ፍሰቱ ከግብርናው ዘርፍ ወደ አገልግሎትና የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሄዱ፣ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ ላለው ከፍተኛ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡ ከፍተኛ የግብርና ምርት ዕድገት ድህነትን በከፍተኛ ደረጃ መቅረፉን ጥናቱ ይገልጻል፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ እያንዳንዷ ፐርሰንት የግብርና ዕድገት ድህንነትን በ0.9 በመቶ ለመቀነስ እንዳስቻለ ያስረዳል፡፡

የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት አሁን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እውነት ቢሆንም፣ የዕድገቱ ምንጭ የሆነው ኪራይ ጠልፎ ሊጥለው መሆኑን የሚያሳዩ ሥጋቶች እያንዣበቡ ነው፡፡

በኪራይ ሰብሳቢነት መጠለፍ

በምዕራባውያኑ ዓለም ኪራይ ሰብሳቢነት ጎንዮሻዊ ትስስር ማለትም በባለፀጋ ኮርፖሬት ኩባንያዎች መካከል የሚካሄድና ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አልፎ አልፎ በምርጫ ወቅት የሕግ አውጪ አካላት የሚጠለፉበት ሁኔታ እንደሚኖር፣ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ሀብታሙ አለባቸው ‹‹Ethiopian’s Context of Rent Seeking Behavior Sociological Perspective›› በሚል ርዕስ አጭር ጥናታዊ ጽሑፋቸው ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ግንኙነቱ ከላይ ወደታች መሆኑን፣ የዚህ ምክንያት ደግሞ በመጀመርያም ቢሆን ኪራዩ የሚፈጠረው በፖለቲካ አመራሩ በመሆኑ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

ብኩን የሆነ የኪራይ ሰብሳቢነት ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ በመላ ማኅበረሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ ነው የሚሉት አቶ ሀብታሙ፣ ብኩን የኪራይ ሰብሳቢነት ሥርዓት ውስጥ ከመንግሥት ጋር የሚመሳጠሩ ቡድኖችና ኔትወርኮች ብቻ የሚፈጠረውን ኪራይ በመላስ የራሳቸውን ኢኮኖሚ ብቻ የሚያበለፅጉበት፣ የሚፈጠረው ኪራይ ላይ ምንም እሴት ሳይጨመር ተበልቶ የሚጠፋበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ለአብነት ከሚያነሷቸው ማሳያዎች መካከል መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ የኤክስቴንሽን ሠራተኞችን ወደ ገጠር የደመወዝ ኪራይ በመፍጠር ቢያሰማራም፣ መንግሥት ለዚህ የተፈጠረ የሥራ ዕድል በሚያወጣው የደመወዝ ወጪና በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩት የኤክስቴሽን ሠራተኞች በምርታማነት ላይ ያመጡት ውጤት እጅግ የተራራቀ መሆኑ፣ አንዱ የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮጀክት በሀብት ክፍፍል ረገድ፣ እንዲሁም የቤት ችግርን በመቅረፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ፕሮጀክት ቢሆንም የኪራይ ሰብሳቢነት አሉታዊ ገጽታው የታየበትም እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ባለትዳሮች የቤት ዕድሉን ለማግኘት ሕጋዊ ፍቺ በመፈጸም የቤት ፕሮግራሙ ተመዝጋቢዎች መሆናቸው፣ አንዱ አስቀያሚ የኪራይ ሰብሳቢነት ገጽታ ነው ይላሉ፡፡

በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከፍተኛ የማስተማሪያ መሣሪያዎች እጥረት ተንሰራፍቶ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት በከፍተኛ ወጪ የመሰብሰቢያ አዳራሽና ዘመናዊ ቢሮዎችን የሚገነባ ከሆነ ይኼስ ምን ሊባል ይችላል? በማለት በአገሪቱ ውስጥ ከታክሲ አሽከርካሪ እስከ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ድረስ የኪራይ ሰብሳቢነት አሉታዊ ባህሪ እየተሰራጨ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከአቶ ሀብታሙ ባለፈም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራሱን የቁጥጥር ቡድን አሰማርቶ ማረጋገጥ የቻለው የፖለቲካ አመራሩ በኪራይ አሉታዊ ወጥመድ ውስጥ እየገባ መሆኑን ነው፡፡

በድብቅ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን የሚቀርቡ የሙስና ጥቆማዎች አፈትልከው ለተጠርጣሪው የሚደርሱ መሆኑን፣ በተቋሙ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ሀብት ማካበት መቻላቸው፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኩል ታክስ በመሰወር የሚተዳደሩ ኦዲተሮች መኖራቸው፣ በአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮጀክት ዲዛይን ላይ የጋራ መገልገያ ቤቶች ቢታይም፣ መሬት ላይ ግን እነዚህ ግንባታዎች አለመታየታቸውና ዋጋው ግን ወደ ተጠቃሚው መተላለፉ የመሳሰሉት ማሳያዎች ናቸው፡፡

ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ከሦስት ወራት በፊት ባካሄደው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማሳያ ጥናት ውይይት ላይ፣ ‹‹እስከ መቼ ስለመልካም አስተዳደር አወራለሁ? እናተስ እስከ መቼ ስለመልካም አስተዳደር እያወራችሁ ትቀጥላላችሁ?›› በማለት በምሬት ሲናገሩ የተሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት የህልውና ጉዳይ ነው በማለት የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ጀምረዋል፡፡

መልካም አስተዳደር ወይስ ኪራይ ሰብሳቢነት?

ኪራይን በመፍጠር ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በአፍሪካ ማስፈን ይቻላል በሚል ጽንሰ ሐሳብ ወደ ትግበራ የገቡት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ የፖለቲካ አመራሩ በሚፈጠረው ኪራይ የሚጠለፍ ከሆነ አደጋው የከፋ እንደሆነ በግልጽ በጥናታቸው አትተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ልማታዊ መንግሥት ለዚህ የማይመች ባህሪ እንዳለው ወይም እንዲኖረው ተደርጎ ስለሚዋቀር፣ የልማታዊ መንግሥት የሥልጣን ቆይታ ምንጩ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መሆኑን፣ ይህ ካልመጣ የልማታዊ መንግሥት ቆይታ አደጋ ውስጥ መሆኑን አሳይተዋል፡፡

የተለያዩ ባለሙያዎች በጥናት እንዳረጋገጡትና ገዢው ፓርቲው ኢሕአዴግና ሕግ አውጪ ፓርላማውም በይፋ እንደገለጹት፣ የፖለቲካ አመራሩ በኪራይ ሰብሳቢነት እየተጠለፈ ነው፡፡ በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሥልጣን ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ንቅናቄ ቢጀምሩም፣ የንቅናቄው ገጽታ ውዥንብር የሚፈጥር ነው፡፡

ንቅናቄው መልካም አስተዳደርን ማስፈን ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ተደምረው እየተሰሙ ያሉ ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት አንዳንዴም ኪራይ ሰብሳቢነትን ማድረቅ በሚሉ ትርክቶች ከመጠመድ ውጪ ተግባራዊ ዕርምጃ ሲወሰድ አይታይም፡፡

የታችኛው እርከን የፖለቲካ አመራሮች ኪራይ ሰብሳቢነትን ማድረቅ የሚሉ ነገሮችን በተለያዩ መድረኮች ሲደሰኩሩ ይዋሉ እንጂ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት እንጂ ጽንሰ ሐሳቡ በውል አይታወቅም፡፡ በመሆኑም ምኑን እንደሚታገሉት ግራ በመጋባት ከላይ የሚባለውን እየደገሙት ይገኛሉ፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት አሉታዊ ባህሪ መንግሥት ልማትን ለማፋጠን ያመጣው እንዳልሆነና ሊሆንም እንደማይችል በመግለጽ ኅብረተሰቡን ማንቃት ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ሀብታሙ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት እንዴት እንደሚቻልም ማሳየት ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ መልካም አስተዳደር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና የየራሳቸው ባህሪ ያላቸው የተለያዩ መሆናቸውን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሔ በበኩላቸው፣ ይህንን ሳያደባልቁ ለይቶ መሠራት የሚገባው ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ይጠቀማሉ፡፡

   

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -