ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርስን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበል መግለጹ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አስታወቀ፡፡
መኢአድ ይህን ያስታወቀው ማክሰኞ ሰኔ 5 ቀን 210 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ ‹‹አሳሪ የሆነውን የአልጀርሱን ስምምነት ያለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ተቀብያለሁ ማለት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፤›› በማለት በሰጠው መግለጫ ነው፡፡
መኢአድ በመግለጫው እንዳስታወቀው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት የወሰነው ውሳኔ፣ ሦስተኛው የአገር ክህደት ነው ብሎታል፡፡ ‹‹ከ27 ዓመታት በፊት ያለ ሕዝብ ፍላጎት አገራችንን ባህር አልባ ማድረጉ የመጀመርያው የአገር ክህደት ነው፡፡ የአልጀርሱን ስምምነት ፈርሞ በስምምነቱ ወቅት አሰብን ማስመለስ ሲቻል፣ ጭራሹን ተጨማሪ ቦታ ከኢትዮጵያ ለኤርትራ እንዲሰጥ መወሰኑ ሁለተኛው ክህደት ነው፤›› በማለት ገልጿል፡፡
‹‹ለ20 ዓመታት ገዥው ፓርቲ የተለያዩ ምክንያት በመስጠት የድንበር ኮሚሽኑ የወሰነውን ውሳኔ ሳይተገብር ቢቆይም፣ ሰሞኑን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሕዝብን ፈርቶ ተግባራዊ ለማድረግ ያልደፈረውን ፀረ ኢትዮጵያ ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ ሌላ ሦስተኛ የአገር ክህደት ነው፤›› በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
በመሆኑም መኢአድ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ መቀበል አንደኛ የአገር ክህደት ከመሆን ባለፈ፣ በምንም መሥፈርት በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ቀውስ የሚፈታ ሳይሆን እንዲያውም የሚያባብስ ነው ብሏል፡፡ ኢትዮጵያን መጀመርያ የወረረው የኤርትራ መንግሥት ሆኖ እያለ፣ የሻዕቢያን ፍላጎት ማሟላትና ለሻዕቢያ ባድመን መሸለም ወረራና ጥፋትን ማበረታታት ነው ብሎ እንደሚያምን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
‹‹በአጠቃላይ ይህንን አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ኢሕአዴግ ብቻውን የመወሰን ሥልጣን ስለሌለው፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያገባኛል ከሚሉ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፤›› በማለት መኢአድ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
‹‹በአልጀርሱ ስምምነት የቀረቡት ጭብጦች የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዱ በመሆናቸው እንደገና ሊጤኑ እንደሚገባ፣ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ በአካባቢው የሚኖሩትን ማኅበረሰቦች ማንነት አደጋ ውስጥ የሚጥልና ለሁለት ሊከፈሉ የማይችሉ የእምነት ተቋማትን፣ የመቃብር ሥፍራዎችን፣ መኖርያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ለሁለት የሚከፍልና ቤተሰብንና ዘመድ አዝማድን የሚበትን ነው፤›› በማለት ውሳኔውን አጥብቆ እንደሚቃወም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ምንም እንኳን ገዥው ፓርቲ እውነቱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመደበቅ ባድመን ጨምሮ አወዛጋቢ አካባቢዎች ለኢትዮጵያ እንደተሰጡ ቢገልጽም፣ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ግን ባድመን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶችን ሙሉ ለሙሉ ለኤርትራ የሰጠ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የደፈረ በወቅቱ በነበረው ጦርነት ደማቸውን ያፈሰሱ ከመቶ ሺሕ በላይ ዜጎችን መስዋዕት ያረከሰ ውሳኔ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው መኢአድ አስታውቋል፡፡