Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲሱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክልላዊ አደረጃጀት የፍትሐዊነት ጥያቄ ቀረበበት

አዲሱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክልላዊ አደረጃጀት የፍትሐዊነት ጥያቄ ቀረበበት

ቀን:

የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በተሻለ ደረጃ ለማዳረስ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያካሄደው ያልተማከለ ክልላዊ የመዋቅር አደረጃጀት የፍትሐዊነት ጥያቄ ቀረበበት፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያካሄደው የመዋቅር አደረጃጀት የተጠሪነት ጉዳይና ግዙፉን አገራዊ ዕቅድ ለማሳካት ያካሄደው የባለሥልጣናት አመዳደብ ችግር ያለበት ነው ያሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ለፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለአገልግሎቱ ሥራ አመራር ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ አሠራሩ በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

      ቅሬታ አቅራቢዎቹ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ያልተማከለ ክልላዊ አደረጃጀት መዘርጋቱን ባይቃወሙም፣ በተጠሪነቱ ላይ ግልጽ መሆን የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      ‹‹የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ አመራር ቦርድና ተቆጣጣሪ የሆነው የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ያስቀመጧቸውን ግቦች የሚሸከም የሥራ አስፈጻሚና የማኔጅመንት አባል ተመድቧል ተብሎ አይታመንም፤›› በማለት የገለጸው የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ፣ ‹‹አመዳደቡ ችግሮችን ከማባባስ ባሻገር የሚፈይደው አንዳችም መፍትሔ ይኖራል ተብሎ አይታመንም፤›› በማለት፣ አሠራሩ ከወዲሁ መልክ ካልያዘ ድርጅቱ ተመልሶ ወደ ማጥ እንደሚገባ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በደብዳቤያቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

      ‹‹በአገልግሎት ድርጅቱ እየተካሄደ ያለው የኃላፊዎች ምደባ በውድድርና በብቃት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በአንፃሩ ከደንብና ከመመርያ ውጪ ምደባ እየተካሄደ ነው፡፡ የሰዎች አመራረጥና አመዳደብ ግልጽነት የጎደለው፣ ኃላፊዎች ከነበሩት ሲነሱ የተነሱበት ምክንያት ሳይገለጽ በደፈናው እየተካሄደ ነው፤›› በማለት ደብዳቤው አብራርቷል፡፡

      ‹‹መርህን መሠረት ያደረገ ወጥነትና ፍትሐዊነት ያለው የምደባ መመርያ ሳይኖር በግል ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም የማኔጅመንት አባላት ምደባ እየተካሄደ ነው፤›› ሲል የሚገልጸው የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ፣ ‹‹ይህም የሠራተኛው የተወዳዳሪነትና የአገልጋይነት መንፈስ በሚገድል መንገድ፣ በደቦ በመጠራራት ሹመትና ኃላፊነት እየተሰጠ ነው፤›› ብሏል፡፡

      ‹‹ቀድሞውንም ጥራት ላይ ቅሬታ እየቀረበ ነው፡፡ ይህንን አካሄድ ለማስተካከል የተተለመው ዕቅድ በትክክለኛ መንገድ ላይ እየተጓዘ ባለመሆኑ ከችግር ከመወጣት ይልቅ ወደ ሌላ ስብስብ ችግር እየተዘፈቀ ነው፤›› በማለት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በደብዳቤያቸው አሳስበዋል፡፡

      እየተካሄደ ያለው በጥቅማጥቅም ላይ የተመሠረተ ምደባ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀው፣ አሠራሩ መሥሪያ ቤቱን ለከፍተኛ ችግር የሚዳርገው በመሆኑ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ብለዋል፡፡

      የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሠራሩን ለማስተካከል ቀደም ሲል የነበረውን የዲስትሪክት አደረጃጀት በመለወጥ ክልላዊ መልክ አስይዟል፡፡ በዚህ መሠረት በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ያልተማከለ ክልላዊ መዋቅር ዘርግቷል፡፡

      አዳዲሶች 11 ቅርንጫፎች በምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች የሚመሩ ሲሆን፣ ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎቹ ራሳቸውን ችለው ግዥ፣ ግብዓት፣ የሰው ኃይል ቅጥር መፈጸም፣ እንዲሁም ከኅብረተሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቶላቸዋል፡፡

      ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎቹ ተጠሪነታቸው በማዕከል ደረጃ ለዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ እንዲሁም በክልል ደረጃ ደግሞ ለክልል ፕሬዝዳንቶችና ለአዲስ አበባና ለድሬዳዋ ከንቲባዎች ይሆናል፡፡

      የቀድሞውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ የተኩት አቶ ሽፈራው ተሊላ የቀረበውን ቅሬታ አይቀበሉትም፡፡ አቶ ሽፈራው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል መሥሪያ ቤታቸው ይከተል የነበረው የዲስትሪክት አሠራር የተማከለ ስላልነበረ ችግሮችንና ቅሬታዎችን ለመፍታት የራሱ ውስንነቶች ነበሩት፡፡

      ‹‹አሁን የተዘረጋው ክልላዊ አሠራርና የተዘረጉት መዋቅሮች ከክልሎች ጋር ተናበው፣ አብረው አቅደው የሚሠሩ በመሆኑ ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎቹ ተጠሪነታቸው ለክልል ፕሬዚዳንቶች መሆኑ ጠቀሜታ እንጂ ጉዳት የለውም፤›› ሲሉ አቶ ሽፈራው አስረድተዋል፡፡

      ከዚህ በተጨማሪ የኃላፊዎች አመዳደብ፣ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ አፈጻጸም እየታየና እየተመዘነ የተካሄደ ነው በማለት አቶ ሽፈራው ቅሬታውን አስተባብለዋል፡፡

      ነገር ግን ቅሬታ አቅራቢዎቹ በዚህ ጉዳይ ላይ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋማት ክትትል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የሥራ አመራር ቦርዱ ጣልቃ ገብተው ጉዳዩን በድጋሚ እንዲመረምሩ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...