Sunday, February 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ፈረሱን ወንዝ ድረስ መውሰድና ውኃውን ማጠጣት ለየቅል ናቸው!

እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 12 ቀን 2000 ዓ.ም. የተፈረመው የአልጀርስ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን በቅርቡ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ውሳኔ ከተሰማ ወዲህ በርካታ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ እጅግ በጣም ዘግናኝ የተባለውን የድንበር ጦርነት አድርገው ኢትዮጵያ በጦርነቱ የበላይነት ይዛ፣ ኤርትራ ደግሞ በተሸናፊነት ውስጥ ሆና የተፈረመው ይህ ስምምነት፣ ከ18 ዓመታት በኋላም ተግባራዊ መሆን ስላቃተው በኢትዮጵያ በኩል በአዲስ አቀራረብ አነጋጋሪ ጉዳይ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ወቅት ሰከን ባለ መንገድ ለመነጋገር የሚጠቅሙ ሐሳቦች ላይ ማተኮር የግድ ይላል፡፡ ወደኋላ ሄድ በማለትም ጭብጥ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የተካሄደው የ30 ዓመታት ጦርነት በወርኃ ግንቦት 1983 ዓ.ም. ከተቋጨ በኋላ የተከናወኑ ዋና ዋና ድርጊቶችን በማንሳት፣ ኢሕአዴግና ሻዕቢያ የጫጉላ ፍቅር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ የተበለሻሹ ክንውኖችን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኤርትራን እየመራ ያለውን ኃይል ባህርያትም በሚገባ ለመንዘብ ይረዳል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ለሰላም ያለው ፍላጎት ከመጠን በላይ ሲራገብ፣ በዚያ በኩል ያለውስ ምን ይመስላል መባልም አለበት፡፡

ኤርትራ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ በ1985 ዓ.ም. ‹‹ነፃነት ወይስ ባርነት?›› በተባለው አሳፋሪ ሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ኢትዮጵያውያን በተገለሉበት ጎጆ ስትቀልስ፣ በወቅቱ ኢሕአዴግን ይመሩ የነበሩ ኃይሎች መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮች እንዳይነሱ በመፈለጋቸው ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያለ ባህር በር ባዶ እጇን አጨብጭባ እንድትቀር መደረጉ ያበሳጫቸው ብዙዎች ሌላው ቢቀር የኢኮኖሚው፣ የድንበርና የዜግነት ጉዳዮች በጊዜ መላ ይፈለግላቸው እያሉ ሲወተውቱ ሰሚ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የሻዕቢያ ሰዎች አዲስ አበባ የነበረውን ኤምባሲያቸውን እንደ ዕዝ ማዕከል በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ አሻጥር ይፈጽሙ ነበር፡፡ ከኮንትሮባንድ እስከ ዶላር ጥቁር ገበያ ድረስ በመሰማራት ኤርትራን ቡና ላኪ አገር ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ በገፍ እህልና የቀንድ ከብቶች ከማጋዝ በተጨማሪ፣ በመንግሥት ቁልፍ ቦታዎች ውስጥ በመሰግሰግ ኤርትራውያንን የበለጠ ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡ ይህ ድርጊታቸው ከመጠን በላይ እየሆነ ሲመጣ ተቃውሞ በመብዛቱ እጅ ጥምዘዛ ጀምረው ነበር፡፡ ናቅፋ የተባለው ገንዘባቸው በሁለቱ አገሮች እኩል እንዲሠራና ተመኑም ተመጣጣኝ እንዲሆን የሚለው ሐሳባቸው ተቀባይነት ሲያጣ፣ ዓላማቸውን ለማስፈጸም እንዲረዳቸው ክፍተት የነበረበትን የድንበር ጉዳይ በመጠቀም ባድመንና አካባቢውን ወረሩ፡፡ ይህ የኤርትራ መንግሥት ባህሪ ነው ሁለቱን አገሮች ወደ ከባድ ጦርነት የከተተው፡፡

በወቅቱ የአገሪቱን የመከላከያ ኃይል በማዳከምና ውስጣዊ አንድነትን በመቦርቦር በተካሄደው አሳዛኝ ድርጊት ከፍተኛ ሐዘን የደረሰበት የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ቀፎው እንደተነካበት የንብ መንጋ በከፍተኛ ወኔ በመነሳቱ ከፍተኛ ዝግጅት ተደረገ፡፡ ይህ ዝግጅት እየተደረገ ግን የአካባቢው ሕዝብ ጦር ግንባር ገብቶ ወረራውን እየመከተ ነበር፡፡ ልጆቹን ስሞና መርቆ የላከው ይህ ጀግና ሕዝብ ጦር ግንባር ድረስ ቀለብ እየሰፈረና እያበረታታ፣ ሻዕቢያ ሲኩራራበት የነበረውንና በዓለም አቀፍ ሚዲያ ብዙ የተባለለትን ምሽግ ደረመሰ፡፡ የኤርትራ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ‹ካሁን በኋላ ባድመን መልሶ መውሰድ ማለት ፀሐይ በምሥራቅ ወጥታ በምዕራብ አትጠልቅም ማለት ነው› ሲሉም፣ በዘመቻ ፀሐይ ግባት አማካይነት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ጀግኖች መስዋዕት ሆነው ባድመ በቁጥጥር ሥር ዋለች፡፡ በወቅቱ ባድመ በወገን ጦር ቁጥጥር ሥር ስትውል የሻዕቢያ ዋና አዋጊ ጄኔራል ሳምሶናይታቸውን፣ የማስታወሻ ደብተሮቻቸውንና በትረ መኮንናቸውን ጥለው ሲፈረጥጡ ሠራዊታቸው ደግሞ በሽሽት ወደ አስመራ ገሠገሠ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊትም ከኋላ እያሳደደ ጉዞውን ሲቀጥል፣ ለሁለት ዓመታት ሲለመኑ የነበሩት ኢሳያስ አስጥሉኝ በማለት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለአፍሪካ ኅብረት ተማፅኖ አቀረቡ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የተደረገው ግን የሻዕቢያን እጅ ጠምዝዞና አስገድዶ ወደ ድርድሩ እንዲመጣ ከማድረግ ይልቅ፣ ከተሸናፊው እኩል ሆኖ አልጀርስ መገኘት ነበር፡፡ አሳፋሪ ተግባር ተፈጸመ፡፡

የአልጀርስ ባለ ስድስት አናቅጽት ስምምነት የተፈረመው አሸናፊውና ተሸናፊው በተለያየ የሥነ ልቦና ቁመና ላይ ሆነው ነበር፡፡ አሸናፊው ከባድመ በተጨማሪ ሌሎች ጥያቄዎችን ማንሳት ሲገባው፣ ተሸናፊው ደግሞ ከዚህ ቀደም በዘፈቀደ የወሰዳቸው እንደ ወደብ የመሳሰሉት ላይ ሸብረክ እንዲል መደረግ ሲኖርበት መስዋዕትነት የተከፈለበትን ድል የሚያደበዝዝ አሳዛኝ ስምምነት ተደረገ፡፡ በተለይ ድንበሩን በተመለከተ ይግባኝ የማይባልበት ስምምነት ከመደረጉም በላይ፣ የድንበር ኮሚሽኑ የይገባኛል ክርክሩን ሲሰማ እዚህ ግባ የማይባሉ ማስረጃዎች መቅረብ ጀመሩ፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንጋፋ ሰዎች፣ የታሪክና የሕግ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት ምክረ ሐሳብ ለማቅረብና ድጋፍ ለመስጠት ቢወተውቱም ሰሚ ጠፍቶ ባድመ ለኤርትራ መወሰኗ ተሰማ፡፡ በወቅቱ ባድመ ለኢትዮጵያ እንድትሰጥ ተወስኗል ያለው መንግሥት በኃፍረት አንገቱን ደፋ፡፡ ከፍተኛ ውግዘትም ደረሰበት፡፡ በወቅቱ የካሳ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ አሥር ሚሊዮን ዶላር ካሳ ቢወስንም፣ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት ድንበሩን ለማካለል በኢትዮጵያ በኩል ባለ አምስት ነጥብ የመደራደሪያ ሐሳብ ቀረበ፡፡ ‹በመርህ ደረጃ ተስማምተናል› ተብሎ ውሳኔውን ማስፈጸም ቢፈለግም አልተቻለም፡፡ ይህ የመንግሥት ውሳኔ በአገር ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በወረቀት በካርታ ላይ ያሰፈረውን መሬት ላይ ችካል ለመምታት ሁለቱንም ወገኖች አገናኝቶ በሰጥቶ መቀበል መርህ እንኳን እንዲደራደሩ ዕድል አልሰጠም፡፡ የኤርትራ መንግሥትም ደረቱን ነፍቶ ጓዛችሁን በፍጥነት ጠቅልላችሁ ውጡ አለ፡፡ ባድመና አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር አሰፈሰፈ፡፡

በካርታ ላይ የተወሰነውን በመሬት ላይ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት ችግሮች ስለሚኖሩ ነው፡፡ በካርታ ላይ እንደታየው አንድ ቤት ሁለት ቦታ ይከፈላል፣ መኖሪያና እርሻ ይለያያል፣ ቤተ እምነትና የመቃብር ሥፍራ ለሁለት ቦታ ይከፈላል፣ አባና እናት እንዲሁም የአንድ ቤተሰብ አባላትን ለሁለት ይለያያል፡፡ በሌሎች አገሮች እንደተስተዋለው ድንበር ሲካለል ተቀናቃኝ ወገኖች ሥፍራው ላይ በመገኘት ጥቅምና ጉዳታቸውን እየመዘኑ በሰጥቶ መቀበል መርህ ችካል እንዲመታ ያደርጋሉ፡፡ በእዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግሮ ወደ ሥራ መግባት ሲቻል፣ የኤርትራ መንግሥት ልክ በጦርነት እንዳሸነፈ የቀረበውን መደራደሪያ አጣጣለው፡፡ ይህ ሁሉ ስህተት የተፈጸመው ግን ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በግድ ወደ ኤርትራ የሚያካልለው የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ውስብስብ በመሆኑ፣ እንዲሁም የእነዚህን ወገኖች የማይገሰስ መብት የሚጥስ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄም ያስፈልጋል፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ አስቸጋሪነት የዜግነት መብትን ጭምር የሚጋፋ በመሆኑ ነው፡፡ በተለያዩ ወቅቶች ከኤርትራ ጋር ለመደራደርና ችግሩን መፍታት እንደሚያስፈልግ ሲነገር ተሰምቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዝህላልነት ታክሎበት የኤርትራ መንግሥት የነውጠኝነት ባህሪ ግን ብዙ ነገሮችን አበላሽቷል፡፡

የሁለቱ ዓመታት ጦርነት ከ70 ሺሕ በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ የኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ጦርነቱ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት የወደመበት ነው፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችን ሕይወት ከማናጋቱም በላይ፣ የነበሩትን መሠረተ ልማቶች ለመጠገን እንኳን አልተቻለም፡፡ አሁንም በድንበር ላይ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወታደሮች አሉ፡፡ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት አሁንም እየጠፋበት ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ሰርጎ ገቦችን እያሰረገ ኢትዮጵያዊያንን መግደል፣ አፍኖ መውሰድና የማሰቃየት ድርጊት ፈጽሞባቸዋል፡፡ ቱሪስቶችን ሳይቀር አግቶ ያውቃል፡፡ ይህ መንግሥት ሱዳንን፣ የመንንና ጂቡቲን በጦርነት ከመፋለም አንስቶ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን የውስጥ ጉዳይ እጁን በማስገባትም ይታወቃል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ ማዕቀብ ተጥሎበታል፡፡ በታንጎ ሥልት ለመደነስ ሁለት ሰዎች እንደሚያስፈልጉት ሁሉ፣ ስምምነት አድርጎ ለመደራደርም የሁለት ወገኖችን ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ለቀረበለት የሰላም ጥያቄ እንኳን ምላሽ አልሰጠም፡፡ ለአሁኑ ውሳኔም ይፋዊ ምላሹ አልተሰማም፡፡ ታዲያ ከዚህ ዓይነቱ ነውጠኛ ኃይል ጋር እንዴት ነው ሰላም መፍጠር የሚቻለው? ከበስተጀርባ እጁን የሚጠመዝዙ ጉልበተኞች አሉ? ወይስ ምን እየተደረገ ነው? ሕዝብ ለዚህ ጠብሰቅ ያለ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ‹ፈረሱን ወንዝ ድረስ መውሰድ ቢቻልም አስገድዶ ውኃ ማጠጣት ግን አይቻልም› የሚባለውን አባባል ማስታወስ ይጠቅማል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

በውጭ ባንኮች አገባብ ላይ ሥጋት እንዳደረባቸው የአገር ውስጥ ባንኮች ኃላፊዎች ገለጹ

መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በፖሊሲ ደረጃ ውሳኔ ማሳለፉ ትክክል...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...

ግመሎቹና ሰውዬው

በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ነበር። ታዲያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...