ሁለት የኦነግ አመራሮችንና እስረኞችን ይዘው ተመልሰዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ኢትዮጵያ ግብፅን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ሲገልጹ በመሃላ የታጀበ ንግግር አሰሙ፡፡ የግብፅ የውኃ ድርሻ እንዲጨምር እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካይሮ ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ከተናገሩት ውስጥ፣ ‹‹ወላሒ፣ ወላሒ ግብፅን በፍፁም አንጎዳም፤›› የሚል ሐረግ በንግግራቸው ማብቂያ ወቅት በዓረብኛ ጣል አድርገዋል፡፡ ይህ ንግግራቸው ፕሬዚዳንት አልሲሲን ከማስደሰቱም በላይ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስከ ዛሬ በዚህ ደረጃ ለግብፅ ቃል ሲሰጥበት ያልታየ ሆኗል፡፡
‹‹ለግብፅ ሕዝብ መናገር የምፈልገው እኛ ኢትዮጵያውያን ወንድምነትና ጉርብትና የምናውቅ፣ ደግሞም እግዚአብሔርን የምንፈራ ስለሆንን ወንድም ሕዝብ የሆነውን የግብፅ ሕዝብ በፍፁም የመጉዳት ሐሳብም ፍላጎትም የሌለን መሆኑን ነው፡፡ የዓባይን ወንዝ መጠቀም እንደምንችልና እንደሚገባን ብናምንም፣ ዓባይን በመጠቀም ኢትዮጵያን ስናለማ ግብፃውያንን በፍፁም እንደማንጎዳ፣ በዚህ የግብፅ ሕዝብ በመንግሥቴና በሕዝቤ ሙሉ እምነት እንዲኖረው እፈልጋለሁ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዓባይ ለሁለቱም ሕዝቦች የተሰጠ በረከት ስለሆነ ኢትዮጵያ የድርሻዋን ተጠቅማ ለግብፅ የሚገባትን ብቻም ሳይሆን፣ ወደፊት እየጨመረ የሚሄድ የውኃ ፍሰት ልታገኝ ስለምትችልበት ሁኔታም በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ዓባይ ለሁለቱም ሕዝቦች የተሰጠ በረከት ስለሆነ የእኛ ሥራ የእኛን ድርሻ መጠቀምና የእናንተን ድርሻ በተገቢው መንገድ ወደ እናንተ መላክ ብቻ ሳይሆን፣ መድረሱንም ማረጋገጥ ጭምር እንደሆነ አውቃችሁ በእኛ በኩል ሥጋት እንዳይገባችሁ፡፡ ዓባይን እንጠብቃለን፡፡ የእናንተን ድርሻ ሁሌም እንጠበቃለን፡፡ ድርሻችሁ እንዲያድግም ከወንድሜ ጋር በመሆን እንሠራለን፤›› በማለት የሁለቱ አገሮች ሚዲያዎች የሚያስተጋቡትን የጥላቻና የቅሬታ ስሜት እንዲያስወግዱ አሳስበዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ውስጥ አክራሪ ፖለቲከኞችና የሚዲያ አካላት ጥላቻና አለመግባባትን ሲነዙ ቆይተዋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ከአልሲሲ ጋር ከዓባይ ባሻገር በሌሎችም መስኮች ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን መግባባት እንደፈጠሩ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኢንዱስትሪ፣ በመንገድ፣ በባቡር ትስስርና በሌሎችም መስኮች የሁለቱን ሕዝቦች ለማስተባበር እንሠራለን ብለዋል፡፡
እስከሁን የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነትና ድርድር ሒደት ወቅት ሲታይና ሲነገር ከሚደመጠው በተለየ አኳኋን በመሃላ ጭምር ቃል የተገባበት የዓባይ ወንዝ ጉዳይ፣ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ከተጀመረ ጀምሮ ባለመግባባት የታጀበ አዙሪት ውስጥ ሲንሸራሸር የቆየበትን ዘይቤ ምን ያህል ሊቀይረው እንደሚችልና ሁለቱን አገሮች ምን ያህል ሊያስማማ እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ግብፃውያን ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መሃላ በጥርጣሬ መመልከታቸው አልቀረም፡፡ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሳባቸውን እየገለጹ የሚገኙት ግብፃውያን ምንም እንኳ በቅዱሱ የረመዳን ወር ከኢትዮጵያ መልካም ወሬ መስማታቸውን ቢገልጹም፣ የግድቡ ግንባታ የአገራቸውን የውኃ ድርሻ እንደሚቀንሰው ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ አንዳንዶቹም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቂት የዓረብኛ ቃላትን ትርጉማቸውን በቅጡ ሳይገነዘቡ የተናሩት ነው እስከማለት ደርሰዋል፡፡
ይህ ይባል እንጂ በሁለቱ መሪዎች ደረጃ የተደረገው ውይይት መግባባት የሰፈነበት እንደነበረ፣ ወደፊትም በዓባይ ወንዝ ላይ ተማምኖ ለመሥራት የሚረዳ መንፈስ እንደፈጠረ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሟሎች ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በግብፅ የታሰሩ ኢትየጵያውያን እንዲፈቱ በተደረገው ስምምነት መሠረት፣ 32 ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ በተጨማሪም የኦሕዴድ መሥራችና የኦነግ አመራር አባል የነበሩት አቶ ዮናታን ዱቢሳና ከመከላከያ ሠራዊት ከ100 ላይ ወታደሮችን በማስከዳት ኤርትራ ገብተው ነበር የተባሉት ኮሎኔል አበበ ገረሱም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተመልሰዋል፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች ከኃይል አማራጭ ይልቅ አገራቸው ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እንደሚፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ተጨማሪ የኢትዮጵያን መብቶች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የግብፅ መንግሥት አብሮ ለመሥራት ቁርጠኝነት ማሳየቱን በማመሥገን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብፅ ቆይታ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አግራሞትን የጫረ ሌላ ክስተትም ተስተውሏል፡፡ ንግግራቸውን በመንግሥት የሥራ ቋንቋ በሆነው አማርኛ ማድረጋቸውን በርካቶች የወደዱላቸው ሲሆን፣ ጥቂት የማይባሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ጸሐፊዎችና አስተያየት ሰጪዎችም ከቀድሞ የአገሪቱ መሪዎች ተርታ በማሠለፍ አሞካሽተዋቸዋል፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴና ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በኋላ በውጭ አገር በአገሩ ቋንቋ ንግግር ያደረገ መሪ ሲሏቸው ሰንብተዋል፡፡