Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናክሳቸው ያልተቋረጠ ተከሳሾች ቤተሰቦች አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል

ክሳቸው ያልተቋረጠ ተከሳሾች ቤተሰቦች አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል

ቀን:

መንግሥት ይቅርታ በማድረግና ክስ በማቋረጥ ከግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከ771 በላይ እስረኞች እንዲፈቱ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ፣ ክሳቸው ያልተቋረጠላቸው በርካታ እስረኞች ቤተሰቦች አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡

      ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር  ኤጀንሲና ከሌሎችም መንግሥታዊ ተቋማት በሙስና ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ ተከሳሾች ቤተሰቦች ሰኔ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመገኘት አቤቱታቸቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቅርበዋል፡፡

በሐምሌና በነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም. አገሪቱ የነበረችበትን የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሁከት አቅጣጫ ለማስቀየር በተደረገ ዘመቻ ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ቤተሰቦቻቸው በእስር ላይ መሆናቸውን፣ እነሱም ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን የታሳሪዎች ቤተሰቦች በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡ ተከሳሾች በተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ያገለገሉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በተመደቡበት የሙያ ደረጃና ኃላፊነት በታማኝነት ሲያገለግሉ በመኖራቸው አገሪቱ አሁን ለደረሰችበት የልማት ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባላቸው ዕውቀትና በተጣለባቸው የሥራ ኃላፊነት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሊያስመሠግናቸውና ሊያሸልማቸው ሲገባ፣ ‹‹የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መፈጸም›› የሚል ድፍን ያለ ጥፋትን እንኳን የማይገልጽ ክስ ተመሥርቶባቸውና ዋስትና የማያስፈቅድ የሕግ አንቀጽ በመጥቀስ ዋስትና ተከልክለው በእስር ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ ከክሱ ርዕስ ማለትም ‹‹የመንግሥትን ሥራ በሚያመች አኳኋን መፈጸም›› ከሚለው መነሳት ቢቻል ተከሳሾች ለግል ጥቅማቸው ወይም ሌላ አካልን ለመጥቀም የፈጸሙት ስህተት አለመኖሩን ከማሳየቱም በተጨማሪ፣ በእነሱ በኩል በአገር ላይ የተፈጸመ ጉዳት ሳይኖር ሌሎች ኃላፊዎችና ሠራተኞች ክሳቸው ተቋርጦ ሲፈቱ እነሱ በእስር ላይ መሆናቸው ተገቢ አለመሆኑን ተገንዝበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ እንዲሰጡላቸው ጠይቀዋል፡፡

የተከሳሾች ቤተሰቦች እንዳስረዱት ተከሳሾች የፈጸሙት ወንጀል ሳይኖርና በፍርድ ቤትም ጥፋተኛ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ደመወዛቸው እንዲቋረጥ በመደረጉ፣ የባንክ ሒሳባቸውና ንብረቶቻቸውም እንዲታገድ በመደረጉ የልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መክፈልና መመገብ ባለመቻላቸው፣ ከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ላይ መውደቃቸውን አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፣ ‹‹ይቅርታ ማድረግና ክስ ማቋረጥ ሒደት ኅብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜያት በፍትሕ ዙሪያ የሚያነሷቸውን የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች የሚመልስና አገራዊ መግባባትን፣ ሰላምና ደኅንነትን የሚያመጣ ነው፤›› ማለታቸውን ያስታወሱት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ይኼ የሚያሳየው መንግሥት ለጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠውና ሁሉንም ተከሳሾና ፍርደኞች የሚያካትት ዕርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በይቅርታና ክስ በማቋረጥ ተከሳሾችን መፍታት በኢትዮጵያ ወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ከበፊትም ጀምሮ የነበረ አሠራር መሆኑን የጠቆሙት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው መንግሥት የሚለየው ግን በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ሰዎች ያለአግባብ ይታሰሩ እንደነበር፣ የፍትሕ መጓደል በስፋት ይታይ እንደነበርና ኅብረተሰቡም በስፋት ሲያነሳው የነበረ በመሆኑ ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይቅርታው እንደተሰጠም መንግሥት መግለጹንም አክለዋል፡፡

በመሆኑም የእነሱንም ቤተሰቦች ማንገላታት የሕግ የበላይነትን የማያረጋግጥ በመሆኑ፣ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከእስር እንዲፈቱና መንግሥትም የጀመረውን የዕድገትና ልማት ጎዳና አብረው እንዲያቀኑ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጨባጭ ማስረጃ ሳይያዝ ያላግባብ የታሰሩ ዜጎችን መፍታትና ነፃ ማውጣትም የፍትሕ ምኅዳሩን ማስፋትና ቤተሰቦቻቸውንም ከእግልትና ችግር መፍታት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሌሎች ታሳሪዎች መፈታት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት በመሆኑ የእነሱም ቤተሰቦች ሌሎች ከተለቀቁ እስረኞች የተለየ ነገር ስላላደረጉ፣ መንግሥት በፈለገው መንገድ በማጣራት ክሱንና ማስረጃውን መርምሮ እንዲፈታቸው ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...