Wednesday, May 22, 2024

የዲሲፕሊን መመርያዎች የፍትሕ አካልን ትኩረት ይሻሉ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የእግር ኳስ ሜዳዎች የዲሲፕሊን ጥሰት እሰየው፣ ግፋበት የተባለ ይመስላል፡፡ ልጓም ያዥ፣ ሃይ ባይ ያጣ፣ ለያዥ ለገራዥ አልጨበጥ እስኪመስል ድረስ ሜዳ የሚጀምረው ብጥብጥና ግርግር በየመንገዱና በየመንደሩ መግባት ከጀመረ ሰነባብቷል፣ እንደቀጠለም ይገኛል፡፡ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ለአንዳንዶቹ ፈጣን ለአንዳንዶቹ ደግሞ እየዘገዬ፣ እያቆጠቆጠና ሥር እየሰደደ የመጣውን የስፖርታዊ ጨዋነት  መጓደል ከእንጭጩ ማድረቅ እንዳልተቻለ የሚናገሩ አሉ፡፡

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ ጀምሮ የዲሲፕሊን መመርያዎቹ፣ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ጨምሮ በፌዴሬሽኑ የተለያዩ ችግሮች ቢፈጠሩ፣ በወቅቱና በሰዓቱ ምንም ዓይነት ብዥታ ሳይፈጠር ነገሮች መፍትሔ የሚያገኙበት ከመሆን ይልቅ፣ በተቃራኒው ሲሆኑ ይታያል፡፡ ይባስኑ መተዳደሪያ ደንቡም ሆነ የዲሲፕሊን መመርያዎቹ በየጊዜው ስለማይሻሻሉ፣ ብዙዎቹ አንቀጾች እርስ በርስ የሚጣረሱ እየሆኑ ችግሮችና አለመጋባባቶች እንዲባባሱ ምክንያት መሆናቸውም እየተነገረ ይገኛል፡፡

ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ በሚለው የማይስማሙት እነዚሁ አካላት፣ የነበረው አመራር ባለውም ቢሆን ይህ ነው የሚባል ተግባሩን እየተወጣ አለመሆኑ ሲታከልበት ደግሞ ነገሩን ‹‹በእንቅርት ላይ. . .›› እያደረገው ስለመምጣቱ ጭምር ይናገራሉ፡፡ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ የፌዴሬሽኑ ካቢኔ ይህንኑ ከግምት አስገብቶ ከመተዳደሪያ ደንቡ የሚመነጨው የዲሲፕሊን ደንቡን ከማሻሻል ጀምሮ ነፃ የፍትሕ አካላት ማቋቋም እንዳለበትም ያምናሉ፡፡

በአቶ ኢሳያስ ጅራ የሚመራው አዲሱ የፌዴሬሽኑ ካቢኔ ቀልቡን ሰብስቦ፣ ሥርዓት አልበኝነት የነገሠበትን የእግር ኳስ ሜዳ መስመር ማሲያዝ እንደሚጠበቅበት ጭምር ይናገራሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ሰመራ ላይ ከምርጫው በኋላ ሲናገሩ እንደተደመጠው ከሆነ፣ ይህ ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት የመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት  ጉዳይ አንድ ቦታ ላይ ሊቆም ይገባል፡፡ ካቢኔያቸው ለዚህ ችግር ነፃ የፍትሕ አካላትን ከማቋቋም ጀምሮ በመንስዔነት የሚጠቀሰውን የፌዴሬሽኑን መተዳደሪያ ከዲሲፕሊን መመርያው ጭምር እንዲሻሻል ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡ ብዙዎችም ይህንኑ መነሻ በማድረግ እየተሠራበት የሚገኘው በተለይ የዲሲፕሊን መመርያውን በማሻሻል የፍትሕ አካላቱም ጥብቅና የማያሻማ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

እግር ኳስ በሚዘወተርባቸው ሜዳዎች ሁሉ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እየተስተዋለ፣ ከሰሞኑ ይኼው ጉዳይ ከማዘውተሪያ ሜዳዎች ውጪም እየተከሰተ፣ አገር ሰላም ብለው በሚንቀሳቀሱ ወገኖች ላይ ሳይቀር የአካልና የንብረት ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡ የጨዋታ ዳኞችና ታዛቢ ዳኞች የሚመሯቸው ጨዋታዎች በሕግና ሥርዓት መመራት ካቆሙ ሰነባብቷል፡፡ በእግር ኳስ ማሸነፍና መሸነፍ ያለና የሚኖር መሆኑ ቀርቶ ባለ ሜዳ ቡድን ማሸነፍ ብቻ በሕግ የተወሰነለት እስኪመስል ድረስ እንግዳ ቡድን ባለሜዳ ቡድን ላይ ቀድሞ ጎል ካስቆጠረ ነገሮች መልካቸውን እንዲቀይሩ በማድረግ የስፖርቱ መርሕ ትርጉም አልባ ሆኖ ይገኛል፡፡

አሁንም ቢሆን አመራሩ እግር ኳሱን ከተዘፈቀበት አላስፈላጊ ቢሮክራሲያዊ አሠራር ነፃ ለማውጣት ተቋማዊ ሥርዓትን ማስፈንና መገንባት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንዲሠራ እየተጠየቀ ይገኛል፡፡ ክለቦች በአንድም ሆነ በሌላ የብሔራዊ ቡድን መሠረት መናቸውን የሚናገሩት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎቸች፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከአህጉራዊም ሆነ ከኢንተርናሽናል መድረኮች እየራቀ መምጣቱ እንደ ዜጋ ሊያሳስብ ብቻ ሳይሆን ሊያስቆጭ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -