Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ብቸኛውን ክሊኒክ ከሥራ ማገድ በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ የጤና ችግር ያስከትላል››

‹‹ብቸኛውን ክሊኒክ ከሥራ ማገድ በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ የጤና ችግር ያስከትላል››

ዶ/ር ጥላሁን ደምስ፣ የአዲስ ቪዥን ስፔሻሊቲ የውስጥ ደዌ ሕክምና

ክሊኒክ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ዶ/ር ጥላሁን ደምስ ተወልደው ያደጉት፣ እንዲሁም የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአማራ ክልል ብቸና ከተማ ነው፡፡ በጎንደር ኮሌጅ ኦፍ ሜዲካል ሳይንስም (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ) በሕክምና ሳይንስ የመጀመርያ ዲግሪ ሠርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ለሦስት ዓመታት ያህል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ተመድበው በሙያቸው አገልግለዋል፡፡ ሆስፒታሉን በሜዲካል ዳይሬክተርነትም መርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በደብረ ማርቆስ ከተማ አዲስ ቪዥን ስፔሻሊቲ የውስጥ ደዌ ሕክምና ክሊኒክ በግላቸው አቋቁመው ለከተማውና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በክሊኒኩ አገልግሎት አሰጣጥና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ዶ/ር ጥላሁንን አቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- አዲስ ቪዥን ክሊኒክ መቼና እንዴት እንደተቋቋመ ቢገልጹልን?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ክሊኒኩ የተቋቋመው በ2004 ዓ.ም. ሲሆን፣ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ያወጣውን ዝቅተኛ ደረጃ አሟልቶ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ያወጣውንም ባለ አረንጓዴ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል፡፡ ክሊኒኩ በደብረ ማርቆስ ሥር ለሚገኙ ወረዳዎች ከፍተኛ አገልግሎት እያበረከተ ለመሆኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ የሚመሰክርለትና የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማትም ምስክርነት የሚሰጡት ለመሆኑ በተለያየ ጊዜያት ከግልና ከመንግሥት የተበረከተለትን የምስክር ወረቀቶች ለማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ጥበቃ ቢሮ በክሊኒኩ ላይ አንዳንድ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰዱ ይነገራል፡፡ ይህ ለምን ሆነ?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የአገሪቱን የጤና ፖሊሲ መሠረት በማድረግ በርካታ የግል ጤና ተቋማት አገራዊ ስታንዳርድን (ደረጃ) መሠረት በማድረግ እንዲቋቋሙ፣ እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የፈቃድና ቁጥጥር ሥራ በቢሮው አማካይነት ለመሠራቱ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በዚህም መሠረት የክልሉ ጤና ቢሮ ቁጥጥር ቡድን ለቁጥጥር ሥራ በወጣበት ወቅት ክሊኒኩ መታየቱ ተገምግሟል፡፡

ሪፖርተር፡- ግድፈቶች የተባሉትን ቢዘረዝሩልን?     

/ር ጥላሁን፡- ይህን ጥያቄ ለመመለስ ነጥቦችን በሁለት ከፍዬ እመለከታቸዋለሁ፡፡ ተገኙ ለተባሉት ክፍተቶች የተሰጠው ትርጉምና ለክፍተቶች የተጠቀሰው የሕግ አግባብ ሲሆኑ፤ ገኙ ለተባሉ ክፍተቶች የተሰጠውን ትርጉም በማብራራት ልጀምር፡፡ ጤና ቢሮው ተገኙ ብሎ በቅጣቱ የጠቀሰብን ክፍተቶች ጠቅለል ብለው ሲታዩ በአራት ይከፈላሉ፡፡ አንደኛው በተቆጣጣሪ አካሉ ያልተመዘገቡ ባለሙያዎች ማሠራት የሚል ሲሆን፣ ይህ ከባለሙያዎች መረጃ ጋር ተያይዞ የተነሳው ጉድለት በተቋማችን በተጨባጭ ያለውን እውነታ አይገልፅም፡፡  በመሠረቱ በተቋማችን የሙያ  ምዝገባ ፈቃድ የሌለውም ሆነ የተሟላ የትምህርትና የቅጥር ማስረጃ የሌለው ባለሙያ የለምም፣ በኢንስፔክሽኑ ሰዓትም አልተገኘም፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ ማንኛውንም የጤና ባለሙያ ሲቀጥር ቀላሉና የመጀመሪው መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታና የተቋሙ የቅጥር መስፈርት ይህ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ የላቦራቶሪ ቴክኖሎጅስት ዶክሜንቶቹ በነበረው አሰራር መሠረት የባለሙያዎቻችንን ዶክሜንት እናሳውቅና እናያይዝ የነበረው በቅርባችን ባለው የክልሉ ጤና ቢሮ ተወካይ ተቋም በሆነው በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ በዚህም ተቋም የላቦራቶሪ  ባለሙያውን ዶክሜንቶች አያይዘን ነበር፡፡ ነገር ግን በኢንስፔክሽኑ ጊዜ እንደ ጉድለት የተጠቀሰው ባለሙያው በፊት ይሠራበት ከነበረው ድሬደዋ ላወጣው የሙያ ፈቃድ መሽኛ ደብዳቤ ማምጣት አለበት የሚል ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ የአንድ ክሊኒካል ነርስ ሠራተኛችን በወሊድ ምክንያት በወቅቱ የሙያ ፈቃድ ምዝገባዋን ሳታሳድስ በመቅረቷና አምስት ወር ያለፈው በመሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተወሰደውን የማስተካከል ሥራ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ጥላሁን፡-  እንደ አቅጣጫ ከክልሉ ጤና ቢሮ በመጡ የኢንስፔክሽን አባላት የላቦራቶሪ ቴክኖሎጅስቱንና ሌሎቹንም በከተማው ጤና ጽሕፈት ቤት የሚገኙትን የባለሙያ ዶክሜንቶች ወደ ጤና ቢሮ እንድናስተላልፍ በተሰጠን ትዕዛዝ መሠረት ክልል ጤና ቢሮ ወስደን አያይዘናል፡፡ በአጠቃላይ ባለሙያን በተመለከተ እንደ ክፍተት የተወሰደው የባለሙያዎች ማስረጃ አለመኖር ሳይሆን  በከተማው ጤና ጽሕፈት ቤት የተያያዙ የሁሉም ባለሙያዎቻችን ማስረጃዎች እንደ አዲስ የጤና ቢሮው አሠራር ለምን በክልል ጤና ቢሮውም አልተያያዙም የሚል ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ደረጃውን የጠበቀ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት አለመተግበር (ስሪ ቢን ሲስተም የለም) የሚል ነው፡፡  በመጀመሪያ ስሪ ቢን ሲስተም ማለት በጤና ተቋማት በሥራ ሒደት ላይ የምንገለገልባቸውና ከበሽተኞች የሚወጡ/ የሚወገዱ አላስፈላጊ ነገሮች እስከሚወገዱ ድረስ በሦስት ባልዲዎች ለያይተን የምናቆይበት ሥርዓት ማለት ነው፡፡ በዚህም አሠራር መሠረት ካሉን ቆሻሻ ለያይቶ ማስቀመጥ ከሚያስፈልጋቸው ክፍሎች ውስጥ በሁለት ክፍሎች አንዳንድ ባልዲ ጎድሎ ተገኝቷል፡፡ ሌሎች አራት ክፍሎች ግን የተሟላ ስሪ ቢን ሲስተም የነበሯቸው ነበሩ፡፡ በኢንፌክሽን ፕሪቬንሽን ወይም በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ማለትም በጤና ተቋማት ውስጥ ካንዱ ሕመምተኛ ወደ ሌላ ግለሰብና አካባቢ ምንም ዓይነት የበሽታ አምጪ ተዋህሲያን እንዳይተላለፍ በምንቆጣጠርበት ሳይንሳዊ አሠራር ተቋማችን ሞዴልና ምስጋና የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም በስፔሻሊስት ሐኪም የሚመራ የኢንፌክሽን ፕሪቬንሽን ኮሚቴ ያለው መሆኑና በራሱ ፕሮግራም ክፍተቶችን እየገመገመና እያቀደ እንዲሁም እያስተካከለ የሚንቀሳቀስ መሆኑንም ለኢንስፔክሽን ተቆጣጣሪ አካላቱ አስረድተን መተማመን ላይ ደርሰን ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ እነዚህን የሁለት ባልዲዎች ጉድለት ተቀብለን አዳዲስ ሐሳቦችን ለማግኘት ይቻል ዘንድ ከዞኑ ጤና መምሪያ በኢንፌክሽን ፕሪቬንሽን/ በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ አሠልጣኝ እንዲመደብልን ጠይቀን የሦስት ቀን ሥልጠና ለሚመለከታቸው ሠራተኞቻችን ከተሰጠ በኋላ በአዲሱ ግንዛቤና ዕውቀት መሠረት የውስጥ ቁጥጥር አድርገን መስተካከል ያለባቸውን ሙሉ በሙሉ አስተካክለን ለጤና ቢሮ የቅጣት ውሳኔው ከመሰጠቱ በፊት በግብረ መልስ ደብዳቤያችን አሳውቀናል፡፡

ሪፖርተር፡- የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድኃኒቶች በተመለከተስ፤

ዶ/ር ጥላሁን፡-  በሦስተኛ ደረጃ እንደጉድለት የተጠቀሰው የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ‹‹HC-Control›› እና ‹‹HC-Calibrator for CBC›› የላቦራቶሪ ሪኤጀንት ይዞ መገኘት የሚለው ነው፡፡ በመሠረቱ በተቋማችን ላቦራቶሪ ውስጥ የተገኙት የላቦራቶሪ ሪኤጀንቶች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ከበሽተኛ ለሚወሰድ የደም ናሙና መመርመሪያነት ስለማያገለግሉ ነው፡፡ እነዚህን ግብዓቶች ክሊኒኩ በዉድ ዋጋ ገዝቶ ያቀረበበት ምክንያት የአጠቃላይ የደም ምርመራ (CBC/Complet Blood Count) በሚደረግበት ጊዜ የባለሙያውን ትክክለኛነት፣ የማሽኑን ትክክለኛነትና የሪኤጀንቶችን አለመበላሸት ለማረጋገጥና ተቋሙ ለሕሙማን ትክክለኛ (Reliable) ውጤት ለማውጣት ካለው የምንግዜም ጠንካራ አቋም የተነሳ ነው፡፡ እነዚህንም ተገኙ የተባሉ ግብዓቶች ያስቀመጥናቸው ለብቻቸው ከፍሪጁ የታችኛው ክፍል ሲሆን በቸልተኝነት ሳይሆን ከአገልግሎት ጥራትና የጥራት ቁጥጥር አንፃር እነዚህን ግብዓቶች እየተጠቀምን የነበረ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች እንዲሁም እንደነዚህ ያሉ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የላቦራቶሪ ኮንተሮሎች ለሚመለከተው አካል ሳናሳይና ሳናሳውቅ በራሳችን ማስወገድ ስለማንችልም ነው፡፡ በወቅቱም ለኢንስፔክሽን ቡድኑ ለማስረዳት የሞከርን ቢሆንም ከቡድኑ አባላት ውስጥ ሙያው የሚመለከተው የላቦራቶሪ ባለሙያ ባለመኖሩ የሚገባውን ያህል ባይሆንም ተስማምተን ነበር፡፡ በወቅቱ የኢንስፔክሽን ቡድኑ አባላት ባሉበት ተወግዷል፡፡ የመጨረሻው ደግሞ በድንገተኛ ክፍሉ ውስጥ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ይዞ መገኘት የሚል ነው፡፡ የተገኙትም የአምስት መቶ ሃያ ዘጠኝ ብር ጥቂት መድኃኒቶች የማንጠቀምበት ሸልፍ (Inactive Shelf) ውስጥ መሆኑና ለሕሙማን ታዝዘው ወይም ሲሠጡ በኢንስፔክሽን ቡድኑ ካለመያዛቸውም በላይ ይህ ተቋም እነዚህንና ሌሎችንም በክሊኒኩ ለኢንስፔክሽን ማሙያ ሳምፕልነት ብቻ የተቀመጡ ጥቂት መድኃኒቶችን ለሕሙማን እንደማይጠቀምባቸው በሦስት ምክንያቶችና በአንድ ማረጋገጫ ገልፀናል፡፡ አንደኛ ተቋሙ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ የተሟላ የራሱ መድኃኒት ቤት ስላለውና ለሕሙማን በድንገተኛ ችግር አስፈላጊ መድኃኒቶች ቢኖሩ ከዚያ መጠቀሙ፤ ሁለተኛ እነዚህ በክሊኒክ (በተለይ መድኃኒት ቤት ላላቸው ክሊኒኮች) ለስታንደርዱ ማሟያነት ይያዙ የሚባሉ አብዛኛው መድኃኒቶች በባህሪያቸው ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማን የሚሰጡ እንጂ ለእንደኛ ዓይነት በስታንደርዱ መሠረት ያስተኝቶ ማከም ሕክምና በማይፈቀድበት ተቋም ውስጥ ለተመላላሽ ሕሙማን የማይሰጡ መሆናቸውና ይህም በተቆጣጣሪ አካላቱ  በግልጽ የሚታወቅ መሆኑ፤ አስፈላጊ ድንገተኛ መድኃኒቶች በአቅራቢያ ከሚገኘው መድኃኒት ቤት እንጂ በክሊኒኩ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ካሉት ሳምፕል መድኃኒቶች እንደማይሰጥ ከላይ የተጠቀሱት ተጨባጭ ምክንያቶች ከማስረዳታቸውም በላይ ማረጋገጫውም ደግሞ በክሊኒኩ የካሽ ሪጅስተር/የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን የክፍያ ዝርዝር (Item List) ውስጥ አንድም የመድኃኒት ስም አለመኖሩና ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በዚህ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን አንድም የመድኃኒት ክፍያ ተፈፅሞ እንደማያውቅ ከሚመለከተው አካል በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ወሳኝ ጉዳይ  የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ማንም ክሊኒክም ሆነ ፋርማሲ በራሱ ማስወገድ ወይም ማቃጠል ቢፈልግ ሕጉ አይፈቅድለትም፡፡ ተቋሙ ማድረግ የሚችለው ለሚመለከተው አስወጋጅ የጤናው ተቆጣጣሪ አካል ሪፖርት አድርጎና ለይቶ ያስቀምጣቸዋል፤ የሚያስወግደው አካል ከመጣ በኋላ ብቻ ይህ አካል ባለበት መድኃኒቶቹ ይቃጠላሉ፤ እስከዚያው ግን እስከ ዓመት ወይም ዓመታት መድኃኒቶቹ በተቋሙ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ሀገራዊና የተቋማት እውነታ በክልል ጤና ቢሮ እየታወቀ እያለ ነው፣ ጊዜውን ጠብቆ ሪፖርት ተደርጎ ሊወገዱ በሚችሉ የ529.00 ብር ጥቂት መድኃኒቶች ያውም ላገልግሎት በማይውሉበት ቦታ በመገኘታቸው ሰበብ ተፈጥሮ በቀን ከ40 ሕሙማን በላይ የሚገለገሉበትንና ከ25 በላይ ቋሚ ሠራተኞችን በውስጡ የያዘውን ተቋም የመንደር ሱቅን የመዝጋት ያህል አቅልሎና በተገልጋዩ ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰውን እንግልት፣ አላስፈላጊ ወጪ ብሎም የሕይወትን ኅልፈት ፈፅሞ ባላገናዘበ መልኩ ነው ተቋሙ የተዘጋው፡፡

ሪፖርተር ፡- አሁን ከላይ በዝርዝር በገለፁት መሠረት እውነቱ ይህ ከሆነ ለክልል ጤና ቢሮ ቅሬታ አላቀረባችሁምን?

   /ር ጥላሁን ፡-  እውነታውን  እንደገለጽኩት ሆኖ ሳለ ከድርጊቱ ጋር የማይያያዝ አንቀጽ ተጠቅሶ ተቋሙ ለሦስት ወራት መዘጋቱና ለክልል ጤና ቢሮ የቅሬታ ሰሚ አካል በማስረጃ ተደግፎ የቀረበውን ቅሬታ ውድቅ መደረጉ ከድራማዊ ክስተትነቱም ባለፈ ትልቅ አስተዳደራዊ በደልን  የሚያመለክትና በተገልጋይ ማኅበረሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ያላገናዘበ ውሳኔ ነው፡፡ የተገልጋይ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ከ25 በላይ የተቋሙ ቋሚ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ጥቅም የሚነካ ነው፡፡ በክሊኒኩ የተወከሉ የተቋማችን ተወካዮች በአካል ባህር ዳር በመሄድ ያደረግነው ጥረት ሊሳካ አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- ክሊኒኩ ከዚህ በፊት እንዳሁኑ ዓይነት ዕገዳ ወይም ቅጣት ተጥሎበት ያውቃል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- በክሊኒኩ ላይ ከዚህ በፊት በተካሄደበት የኢንስፔክሽን ሥራ ምንም ዓይነት የቃልም ሆነ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት አያውቅም፡፡ እንዲያውም በክልሉ ከሚገኙ የግል ጤና ተቋማት ከፍተኛ ደረጃ (አረንጓዴ ላይሰንስ) ያለው ነው፡፡ ከ25 በላይ ቋሚና ከአምስት በላይ ተመላላሽ ባለሙያዎችንና ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ ይህም ከግንዛቤ ተያይዞ የተለመደውን አገልግሎት እንዲቀጥል በመወትወት ላይ ነን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ክሊኒኩ አገልግሎቱን እንዲቀጥል በማድረግ ከጎናችሁ የቆሙ የመንግሥት ተቋማት አሉ?

ዶ/ር ጥላሁን፡- አዎ አሉ፡፡ ለዚህም የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና ጥበቃ መምርያና የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ መንግሥታዊ ተቋማት ዕገዳው በማስጠንቀቂያ እንዲተላለፍ የሚገልጽ የውሳኔ ሐሳብ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጤና ቢሮ ሰጥተዋል፡፡ ድርጅቶቹ ይህንን የውሳኔ ሐሳብ ሊያቀርቡ የቻሉት ክሊኒኩ ፈጠራቸው የተባሉት ግድፈቶች በፍጥነት የሚታረሙና ተቆጣጣሪው አካል በግኝቶቹ ላይ አስተያየት በሰጡ በማግሥቱ የተስተካከሉ መሆኑን በመገንዘባቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ክሊኒኩ እስካሁን ካለው የመልካም ሥራ አፈጻጸም በተለይ ለማኅበረሰቡ በዕውቀትና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እየሰጠ ያለው አገልገሎት፣ እንዲሁም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች አሟልቶ በመሥራት በከተማችን ፋና ወጊ መሆኑንም ስለሚያውቁ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በተለይ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የክሊኒኩን ከሥራ መታገድ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ አስመልክቶ ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ እንዳለ ነግረውናል፡፡ የደብዳቤውን ፍሬ ሐሳብ በአጭሩ ቢገልጹልን?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል አሁን ባለበት ነባራዊ ሁኔታ ለከፍተኛ የሥራ መጨናነቅ የተዳረገ ከመሆኑም በላይ በሽተኞች ማረፊያ አጥተው ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን፣ በሆስፒታሉ ያሉ የሕክምና ባለሙዎች ከበሽተኛ ፍሰት የተነሳ ከአቅም በላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ መሆናቸው፣ ዞናችንን ጨምሮ ከአጎራባች ዞኖችና ከክልሎች የሚመጡ ተገልጋዮች የተለያዩ ምርመራዎችን ለማግኘት በተሟላ መንገድ የተደራጀ የጤና ተቋም በዞናችን የሌለ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በአዲስ ቪዥን የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ክሊኒክ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ካለው አጠቃላይ ጫና ጋር ተዳምሮ ሲወሰድ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም ለሦስት ወራት እንዲዘጋ የተወሰነውን ውሳኔ እንደገና በማየት ሌሎች የቅጣት አማራጮችን በመከተል ኅብረተሰቡ ከጤና ተቋሙ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት እንዲያገኝ ውሳኔውን እንደገና እንዲጠና የሚጠይቅ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቢሮው የቀረቡለትን አማራጭ የውሳኔ ሐሳቦችን እንዴት ተመለከተው?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የጤና ጥበቃ ቢሮ ለዚህ የሰጠው መልስ ጉዳዩን እንደገና እናየዋለን የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክሊኒኩ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው በክፍያ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የመክፈል አቅም የሌላቸው ታካሚዎች ሲመጡ ይመልሳቸዋል? ወይስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ይተባበራል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የአቅም ማነስ ችግር ላጋጠማቸው ታካሚዎች ካልከፈላችሁ አላክማችሁም የሚል አቋም የለውም፡፡ በተቻለ መጠን ሕክምናውን በነፃ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ግፋ ቢል ደሃ ለመሆናቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል እንዲያመጡ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ ያህልም አንድ የደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆነችውን በ2010 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በ1ኛው ሴሚስተር 96.9 በመቶ በማምጣት ከክፍሉ 1ኛ ከአጠቃላይ ተማሪዎች 2ኛ የወጣችውን ተማሪ በደረሰባት ሕመም ክሊኒኩ ነፃ ሕክምና በመስጠት ሕመሟ እንዲሻላት አድርጓል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...