በሰለሞን መለሰ
‹‹ነብይ በአገሩ አይከበርም›› የሚባል አባባል አለ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ደግሞ፣ አለመከበር ብቻ ሳይሆን በአገሩ ውስጥም እንዲኖር አይፈቀድለትም፡፡ ‹ነብይ› ስል በሃይማኖታዊ አገላለጽ እንደ ሚታወቁት ትንቢት የሚናገሩትን ሰዎች ለማውሳት ፈልጌ አይደለም፡፡ እንዲያውም ትኩረቴ ሃይማኖታዊ ሳይሆን በተቃራኒው ፖለቲካዊ (ምድራዊ) ነው፡፡ በዚህ ጽሑፌ ልገልጻቸው የምፈልጋቸው ሰዎችን እንዲህ በጥቂት ቃላት ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም አገራቸውን የሚወዱ፣ ሕዝቧንም የሚያከብሩ፣ ተንኮል በውስጣቸው ያልበቀለ፣ ከፍቅረ ንዋይ የራቁ፣ በዕውቀት የላቁ፣ ወዘተ. . . ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካም ሆነ ከፍ ሲልም ለዓለም ሊተርፍ የሚችል ሐሳብና ራዕይ የነበራቸውንና ያላቸውን፣ የሚታወቁና የማይታወቁ ኢትዮጵያውያንን ነው፡፡ አንዳንዶች እንደዚህ ዓይነት ኢትዮጵያውያንን ማግኘት ይከብዳል ወይም እስከነ ጭራሹም የሉም ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳ ከላይ የተዘረዘረው አገላለጽ ከመላዕክት ዝቅ፣ ከሰዎች ደግሞ ከፍ ያሉትን የሚመለከት ቢሆንም በእርግጥ ዛሬም ቢሆን፣ እንደ ብርቅዬ የዱር እንስሳዎቻችን ቁጥራቸው ተመናምኖም ቢሆን ይገኛሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት 40 ዓመታት ገደማ (በጥቂቱም ቢሆን ከዚያም በፊት) ለእስርና ለእንግልት ዳርጋ ያልተጠቀመችባቸው፣ በስደት አገር ሌሎች እንደ ሸንኮራ ሲመጧቸው የቆዩና ያለፉ፣ ይባስ ብሎም በሞት የቀጣቻቸው ልጆቿ ቢቆጠሩ በከርሰ ምድሯ ውስጥ አምቃ ይዛዋለች ከተባለው የተፈጥሮ ሀብት በብዙ እጥፍ ሊበልጡ ይችሉ እንደ ነበር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ አገራቸው ቀና ብላ እንድትታይ፣ በዓለም መድረክ ላይም ስሟ እንዲጠራ፣ ከዚያም አልፎ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው የሚኮሩባትና የሚመኩባት አገር ሊያቆዩ ደፋ ቀና ባሉ፣ በምቀኞችና በመኃይማን የተናቁ፣ የተንገላቱ፣ አልፎ ተርፎም የተገደሉ ስንትና ስንት ዕንቁ ዜጋዎቻችንን አጥተናል፡፡ እገሌን ጠርተህ ለምን እገሌን ተውከው የሚል አተካራ ውስጥ ላለመግባት ለጊዜው ስም ጥሪውን ልተወውና አንባቢውያን ሁሉም በያሉበት እንደሚያውቋቸው መጠን ሊያወሱዋቸውና ሊወያዩባቸው ይችላሉ፡፡
እኔ እንደምገምተው የዚህች አገር መከራዋ የበዛውና ጣሯም የረዘመው ለእነዚህ ዕንቁ ዜጎቿ ፊት ነስታ ማንም እበላ ባይና አፈ ጮሌ ተደማጭና ተመራጭ ሆኖ በመቆየቱ ሳይሆን እንደማይቀር ብዙዎቻችን የምንስማማ ይመስለኛል፡፡ ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያን ከፍ አድርገው ስሟን ለማስጠራት ሲችሉ ንቃ በተወቻቸው፣ ከችጋርና ከድህነት አረንቋ ሊያወጧት ሲችሉ በየዘብጥያውና በስደት ዓለም ስታንከራትታቸው ኖራ ለቀጠፈቻቸው ልጆቿ ልትፀፀት (ንሰሐ ልትገባ) ግድ ይላታል፡፡ ታሪካቸውንም እያወሳች ማስታወሻ ልታኖርላቸው ያስፈልጋል፡፡
ታዲያ እንዲህ እንዳሁኑ ዓይነት የለውጥ እንቅስቃሴን እያሸተቱ፣ ለቤተ መንግሥቱ ቤተኛ ለመሆን በሚሞክሩ የግል ጥቅም አሳዳጆች መሪዎች በእጅጉ ሊታለሉ ይችላሉና ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ የእነዚህ መሰሪዎች ትልቁ መለያቸው በግል ሰብዕና ግንባታ ላይ የሚያተኩሩና ቁሳዊ ጥቅም የሚያጓጓቸው፣ ከሌሎች የሚያገኙት ክብር የሚያሰክራቸውና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ማንነታቸው እንዲታወቅላቸው የሚጥሩ መሆናቸው ነው፡፡ ጊዜ ሲጣላ አገር አዋቂ ሳይሆኑ ታዋቂ በሆኑ ሰዎች ትሞላለች፡፡ እነዚህ የዕውቀት ደሃ ሰዎች በምላሳቸው ቅልጥፍና፣ ባካበቱት ሀብትና ዝና ምክንያት ያላቸው ተፅዕኖም ቀላል ባለመሆኑ በርካቶች ሊቃወሟቸው ካለመፈለጋቸውም በላይ፣ ስህተቶቻቸውን እንኳ ለማረም አይሞክሩም፡፡ እየቆዩም ራሳቸውን እንደማይደፈር ተራራ ቆልለው የተቃወማቸውን ብቻም ሳይሆን የተቃወማቸው የመሰላቸው ላይም የፈሪ ብትራቸውን ያሳርፉበታል፡፡ ይህ እንዳያጋጥመው የሚፈራው አብዛኛው ሕዝብ ተራ ስህተቶቻቸውንና በግልጽ የሚታዩ ወንጀሎቻቸውንም ዓይቶ እንዳላየ ሲያልፈው ይስተዋላል፡፡ “ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፤” ብሎ የአገሬ ሰው የተረተውም ከላይ የተገለጹትን ሁለት ታሪካዊ እውነታዎች ተገንዝቦ ነው፡፡ ያለፈውን በዚህ መንገድ ካየነው በቀጣይ ምን እንድናደርግ ይጠበቃል ለሚለው መልስ ይሆን ዘንድ፣ የዛሬው ጽሑፌ ዋነኛ ማጠንጠኛ እንዲሆን ፈልጌ ነው ከላይ የተገለጹትን የሁለት ዓለም ሰዎች ለመጠቃቀስ የሞከርኩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲኖሯቸው ከምመኘው ነገር አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ጠንካራ የአማካሪ ቦርድ (ስሙ ምንም ሊሆን ይችላል) ነው፡፡ አሜሪካውያን ፕሬዚዳንቶች በፖሊሲ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚያማክሯቸውና ድጋፍም የሚሰጧቸው የመንግሥት ተሿሚ ያልሆኑ በየዘርፉ በርካታ አማካሪዎች አሏቸው፡፡ በእርግጥ እንደነሱ ሀብታሞቹን ብቻ የሚያካትት የልሂቆች ስብስብ ሳይሆን፣ ጉዳዩን አገርኛ አድርገነው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎችና ቢቻል በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ብሔረሰቦች የሚኖሩበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከውሳኔዎቻቸው በፊት የሕዝባቸውን ሐሳብ የሚያዳምጡበት (ሙቀት የሚለኩበት) አንድ ስብስብ ቢኖራቸው እሳቸውም አገርም ይጠቀማል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሐሳቤን በዝርዝር ላብራራው፡፡
ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉት አባላት ከ25 የማያንሱና ከ30 የማይበልጡ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአማካሪዎቻቸው የሚመረጡ (Handpicked) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስብጥራቸውንም ስናይ ከነጋዴዎች አራት፣ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አራት፣ ከሃይማኖት ተቋማት አራት፣ ከዳስያስፖራ አራት፣ ከምሁራን ሦስት፣ ከሴቶች ሦስት፣ (ሴቶች በሌሎች ዘርፎችም ለመወከል ያላቸው ዕድል እንደተጠበቀ ሆኖ)፣ ከወጣቶች ሦስት፣ ወዘተ. . . በማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላም በኩል የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች የሚወክሉ አማካሪዎችን ደግሞ በሕዝብ ብዛት ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ብሔረሰብ በአንድ በአንድ ሰው ተወክሎ ፍላጎቱንና ጥያቄውን የሚያቀርብበት መድረክ ይሆናል፡፡ እንደሚባለው ኢትዮጵያ የ80 ብሔረሰቦች አገር ብትሆን ሰማንያ የቦርዱ አባላት ይኖራሉ ማለት ነው፡፡
እነዚህን የብሔረሰብ ተወካዮች ለመምረጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው በአንድ ቀን ምክክር (ብዙዎቹ ተዘጋጅተው የሚጠብቁ ሽማግሌዎች አሏቸው) ሊያሳውቁ የሚችሉ ሲሆን፣ እንደ ኦሮሞና አማራ ዓይነት በርካታ አባላት ያሏቸው ብሔረሰቦች ሁሉም የየአጥቢያቸውን ተወካይ ከመረጡ በኋላ በጋራ በሚያደርጉት አንድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይህንኑ ተወካያቸውን ‹ለመሾም› ይችላሉ (በዚሁ አጋጣሚም እነዚህ ትክክለኛ ‹የሕዝብ አደረጃጀቶች› በቋሚነት የየብሔረሰቦቻቸውን ጥያቄዎች የሚወያዩበትና የአገሪቷንም ወቅታዊ ሁኔታ የሚመካከሩበት መድረክ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም የአማካሪዎች ቦርድ ተወካዮቻቸው ሪፖርት የሚያቀርቡለት አካል ይኖራቸዋል)፡፡
ከዚህ በላይ ያቀረብኩትን ሐሳብ ለመሰንዘር ያስገደደኝ መካሪ ማጣትን የመሰለ አለመታደል የለም ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ አገርን የሚያህል ጉዳይ ለማስተዳደር ደግሞ አማካሪ የግድ ይላል፡፡ ‹መካሪ የሌለው ንጉሥ ያላንድ ዓመት አይነግሥ› ይላል ተረቱም፡፡ መሪን ለማማከር የተለያዩ መጻሕፍትና አነቃቂ ንግግሮች ከፍተኛ ድርሻ ቢኖራቸውም፣ የፊት ለፊት ውይይትን የመሰለ ሐሳብ ማንሸራሸሪያ መንገድ ግን አይገኝም፡፡ ብዙውን ጊዜ እንደሚባለው ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንድ ጠንካራ ሴት ብትኖርም፣ ከእያንዳንዱ ስኬታማ ሰው (ወንድ ይሁን ሴት) ጀርባ ደግሞ አማካሪዎቻቸው (Mentors) እንደሚኖሩ ጥርጥር የለኝም፡፡ ከላይ ልገልጻቸው የሞከርኳቸው ‹መደበኛ ያልሆኑ የሕዝብ ተወካዮች› (የተሻለ ስም ስላጣሁላቸው ነው) ዋነኛ ተግባራቸው የአገሪቷን ርዕሰ ብሔር ማማከር ብቻ ሳይሆን፣ ከርዕሰ ብሔሩ የሚሰሙትንም መልዕክት ለሚወክሉት ሕዝብ በሚገባው ቋንቋ መልሰው በማስረዳት፣ የሁለትዮሽ ግንኙነቱንም በተሻለ መግባባት ያከናውኑታል፡፡ የፖለቲካ ሹመኞች ባለመሆናቸውና በፓርቲ ሽኩቻ ውስጥ የሌሉ በመሆናቸው፣ የሚቀርባቸው ጥቅምም ባለመኖሩ፣ ያለምንም ፍርኃትና መሸማቀቅ ትክክለኛውን መልዕክት ከላይ ወደታች፣ እንዲሁም ከታች ወደላይ በማድረስ ድርሻቸውን በአግባቡ ይወጣሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእነዚህን ጥቂት ሰዎች ንቃተ ህሊና (Consciousness) ማሳደግ ከቻሉ፣ ሁሉም ወደ ወከላቸው ኅብረተሰብ በመሄድ እንዲሁ የሕዝባቸውን ንቃተ ሕሊና ከፍ ለማድረግ ይችላሉ፡፡ በዚህም መሠረት የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ንቃተ ህሊና (Collective Consciousness) በአንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ ይቻላልም ባይ ነኝ፡፡ የአንድ ሕዝብ ባህሪ ዋና መመዘኛው የአስተሳሰብ ደረጃው በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያንስ በሁለት ወር አንድ ጊዜ የሚሰበስቧቸውን አንድ መቶ የሚያህሉ ኢትዮጵያውያንን እንደ ለውጥ ማዕከል ተጠቅመው፣ ለአንድ መቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ንቃተ ህሊና (Collective Level Of Consciousness) መጎልበት ቢጥሩ የራሳቸውንም ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ያቀልላቸዋል፣ ለሕዝቡም ዘለዓለማዊ ቅርስ ይተውለታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ዶ/ር ዴቪድ ሐውኪንስ የጻፉትን ”Power Vs Force” ማንበብ ብዙ ቁምነገር ያስጨብጣል፡፡
ኢሕአዴግ የሽግግሩን መንግሥት ሥልጣን በያዘ ማግሥት ቀዳሚ ካደረጋቸው ሥራዎቹ አንደኛው (በ1985 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ) 42 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን በጅምላ ማባረር ነበር፡፡ በወቅቱ የተሰጠው ምክንያትም የዕውቀት ማነስና በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባት የሚል ነበር፡፡ (ለደርግ ግብዓተ መሬት መፋጠን የ1981 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ሙከራና እሱንም ተከትሎ የተገደሉት ባለ ከፍተኛ ማዕረግ መኮንኖች ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ሁሉ፣ ለኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓት ውድቀት የእነዚህ ምሁራን ስንብት ከፍተኛውን ድርሻ የተወጣ ይመስለኛል፡፡) እነዚህ መምህራን ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ በሌሎች አገሮች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንቱ ተብለው ለመጠራት ብዙም ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ መቼም ለአገራቸው የደበቁትን ዕውቀት ለባዕዳን ያለስስት በማቅረባቸው ያገኙት ሙገሳ ነው ልንል አይቻለንም፡፡ ታዲያ በወቅቱ የውሳኔው አካል የነበሩ ባለሥልጣን በቅርቡ በአንድ የመገናኛ ብዙኃን በነበራቸው ቃለ ምልልስ ውሳኔው ትክክል እንደ ነበር፣ አሁንም ድረስ እምነታቸው እንደሆነ ሲገልጹ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በእንደነዚህ ዓይነት ሹሞች ሳይከለሉ በቀጥታ የሕዝባቸውን ሐሳብ ለማዳመጥና ለመለወጥ እንዲያስችላቸው፣ ይኼ የሁለትዮሽ ምክር ቤት ቢቋቋም ምኞቴና ፀሎቴ መሆኑን ደግሜ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ብዙውን ጊዜ ተሿሚዎች በይበልጥ ለፖለቲካ ዝንባሌያቸው የሚያደሉና ሥራቸው እንጀራቸው የሆነባቸው ሰዎች ስብስብ ስለሚሆን፣ ትክክለኛ ውሳኔያቸው በፍራቻም ሆነ በጥቅም የሚሸፈንበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡
ከዚህ በላይ በዝርዝር ያቀረብኳቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድ ወይም በሌላ የሚወከሉበት የርዕሰ ብሔሩ የአማካሪዎች ቦርድ ከተዋቀረ በኋላ፣ ቢያንስ በሁለት ወር አንድ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመገናኘት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ይወያያል፣ ቢቻል ውይይቱን በቀጥታ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ሕዝቡ እንዲከታተለው ይደረጋል፡፡ በዚህም ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ፖለቲካ ያልተቀላቀለበትን የሕዝባቸውን ቀጥተኛ ሐሳብ ለመስማትና የመንግሥታቸውንም የሥራ እንቅስቃሴ ለሕዝባቸው ለማብራራት ዕድሉን የሚያገኙበት መድረክ ይሆናል፡፡ አንድ መቶ ኢትዮጵያውያንን በሁለት ወር አንድ ጊዜ መሰብሰብ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ትልቅ ሥራ ይሆንባቸዋል የሚል ግምት በበኩሌ የለኝም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡