Sunday, April 14, 2024

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት ፈተናና የተደቀነው ማኅበራዊ ቀውስ ሥጋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የ2011 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ይዘው የቀረቡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ያደረጉት የበጀት መግለጫ ንግግርን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ጠፍረው ያሰሩ ችግሮችንና ለችግሮቹ ፈጣን መፍትሔ ካልተገኘ ሊፈጠር የሚችለውን ማኅበራዊ ቀውስ ያመላከተ ነበር፡፡

politics

 

‹‹ያለፉት ዓመታት በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡባቸው ቢሆኑም፣ በዚያው ልክ ደግሞ በርካታ ተግዳሮቶች የተስተናገዱባቸው ነበሩ፤›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ሚኒስትሩ፣ በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በአገሪቱ የተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለመንግሥት ፈታኝ ሁኔታን ፈጥሮ ነበር ብለዋል፡፡ ችግሩን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት በተደረገው ሙከራ አሁን አንፃራዊ ሰላም መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

‹‹የፊስካል ፖሊሲው የአገሪቱን የልማት ግቦች ለማሳካት የሚያስችል ሆኖ የተቀረፀ ቢሆንም፣ ውጤታማ እንዳይሆን በተግባራዊነቱ በኩል በከፍተኛ ፈተናዎች የታጠረ ነበር፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በሚኒስትሩ ማብራሪያ መሠረት ግብርና ላይ ለዘመናት ተንጠልጥሎ የቆየውን የኢኮኖሚ መዋቅር በማሸጋሸግ የኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የአገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር መሠረት እንዲሆን፣ ከመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጀምሮ ላለፉት ስምንት ዓመታት የተደረገው ጥረት ውጤት ሊያስመዘግብ ይቅርና ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረውን ያህል ዕድገት በኢንዱስትሪና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ማስመዝገብ አልተቻለም፡፡

‹‹የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ በራሱ ጊዜ የሚከሰት ሳይሆን ልማታዊ መንግሥታት አቅደው የሚሠሩበት ሒደት ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከዚህ አንፃር መንግሥት ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚው ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ ከፍተኛ ሚና ቢጫወትም፣ የተደረጉት ጥረቶች ትርጉም ያለው ውጤት ላይ ለመድረስ ባለመቻላቸው የሚፈለገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል አዳጋች ሁኔታ ላይ እንደተደረሰ በአጽንኦት ያሳስባሉ፡፡

በ2008 ዓ.ም. ተከስቶ ከነበረው የዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ አጋጥሞ ከነበረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በፍጥነት በመላቀቅ፣ በ2009 ዓ.ም. 10.9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡን ይህም ለተከታታይ 14 ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ 10.6 በመቶ የተመዘገበ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ዓመታዊ የዜጎች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 863 ዶላር ከፍ ሲል፣ የአገሪቱ የድህነት ምጣኔ ወደ 23.5 በመቶ ዝቅ እንዲል ማስቻሉን ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን ለዓመታት የተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የኢኮኖሚውን ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚያስችለውን መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት አልቻለም፡፡ ለማሳያነትም በ2009 ዓ.ም. ለተመዘገበው 10.9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት የኢኮኖሚ ዘርፎቹ የነበራቸውን ድርሻ አቅርበዋል፡፡

በተጠቀሰው ዓመት ለተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት 68 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ያበረከተው የአገልግሎትና የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሲሆን፣ የግብርና ዘርፉ ደግሞ 23 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ የኢኮኖሚ መዋቅሩ መሠረት እንዲሆን ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲለፋበት የነበረው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያበረከተው ድርሻ 9.6 በመቶ ብቻ ነበር፡፡

ፈጣንና ፍትሐዊ ዕድገትን በማምጣት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠልና የኢኮኖሚውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን የማረጋገጥ ግብ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት ለዓመታት ጥረት ሲደረግ ቢቆይም፣ የተገኘው ውጤት በተቃራኒው መሆኑን ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ማስረጃዎችን በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ ለአብነት የሚጠቅሱትም በ2009 ዓ.ም. የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያስመዘገበውን ዝቅተኛ አፈጻጸም ነው፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ይህ ዘርፍ በ2009 ዓ.ም. ከተመዘገበው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ 6.4 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች አማካይ አንፃር እንኳን ሲታይ ግማሽ ያህል ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት የተደረገው ጥረትና ውጤቱ

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በራሱ ጊዜ የሚከሰት ሳይሆን መንግሥታት አቅደው የሚሠሩበት ሒደት ስለመሆኑ የሚናገሩት ሚኒስትሩ በዚህ መሠረት አምራች ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋትና ለዘርፉ ኢንቨስትመንት መጎልበት አመቺ ሁኔታዎችን የመፍጠር ግብ አስቀምጦ ለዓመታት ሲንቀሳቀስ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

ከጥረቶቹ መካከልም የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የመሠረተ ልማትና የኢነርጂ ልማት ፕሮግራሞችንና ሌሎች የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያዎችን፣ መንግሥት አጠናክሮ ሲተገብር መቆየቱንና መዋቅራዊ ለውጡን የሚያፋጥኑ አምራች ኩባንያዋችም በቀጥታ እየተሳተፉ ስለመምጣታቸው ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ የዘረዘሯቸው የመንግሥት ጥረቶች የቅንጅት መጓደል የሚታይባቸው፣ እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ የምርት ግብዓት በአገር ውስጥ በሌለበት የተጀመሩ በመሆናቸው የታቀደውን ውጤት ማስገኘት አልቻሉም፡፡

በሌላ በኩል የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡን ዕውን ለማድረግ፣ በከፍተኛ የውጭ ብድሮች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጎላ የፕሮጀክት አስተዳደር ችግርና ከሌሎች በርካታ የመንግሥት የአስተዳደር ውስንነቶች የተነሳ አስተጓጉለውታል፡፡

ከእነዚህም መካከል መንግሥት የስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ በማደራጀት የአገሪቱን ፍጆታ ከማርካት ባለፈ በዓለም የስኳር ገበያ ለመሳተፍ በመተለም፣ ከመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አስቀድሞ የጀመራቸው አሥር ግዙፍ የስኳር ፋብሪካዎች ፕሮጀክቶች አንዱንም (የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን) ሳያሟሉ ተጨናግፈዋል፡፡ መንግሥት እነዚህን የስኳር ፋብሪካ ሲጀምር ካስቀመጣቸው ግቦች መካከል ፕሮጀክቶቹን በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ማገባደጃ ላይ ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቅ፣ በዕቅዱ ዘመን ማብቂያ ላይም የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ ማቅረብ፣ እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማመንጨት ነበር፡፡ ለዚህም ስኬት ሲባል ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ብድር ውስጥ መግባቱን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይሁን እንጂ ከተጀመሩት ፕሮጀክቶች ውስጥ ሁለቱ ብቻ በ2011 ዓ.ም. ተጠናቀው ወደ ምርት ሒደት እንደሚገቡ በዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ ሌሎቹ በከፊል ሲጨናገፉ የተቀሩት ሁለት ፋብሪካዎች ደግሞ ዕጣ ፈንታቸው ሳይታወቅ በተጓተተ የግንባታ ሒደት ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ አሳዛኝ የፕሮጀክት አፈጻጸም ሒደት ውስጥ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ የመጣው ደግሞ፣ ለፕሮጀክቶቹ የተወሰደውን የውጭ ብድር ከእነ ወለዱ መንግሥት መክፈል መጀመሩ ነው፡፡ የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት ደግሞ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የማስገባት ግዴታ ውስጥ መውደቁ ነው፡፡

ከስኳር ፕሮጀክቶቹ በተጨማሪ የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በፍጥነት ገብተው ማምረት እንዲችሉ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመመሥረት ሒደት ነው፡፡ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የመጀመርያ የኢንዱስትሪ ፓርክ (ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ) ቦሌ ለሚ ተብሎ በሚጠራው የደቡብ አዲስ አበባ ጫፍ ላይ ከተገነባ በኋላ፣ ሌሎች ተጨማሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የማስፋፋቱ ሥራ ውስጥ መንግሥትት በሰፊው ገብቶበታል፡፡ ለዚህም ሲባል ለአገሪቱ በታሪክ የመጀመርያ የሆነው የዕዳ ሰነድ ለአውሮፓ ገበያ እ.ኤ.አ. በ2014 ተሽጦ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ተገኝቷል፡፡ ይህ ብድር በዋናነት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲውል ተወስኖ ወደ ተግባር ሲገባ በዚህም የሐዋሳ፣ የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተከናውኖበታል፡፡

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ250 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ እ.ኤ.አ. በ2016 ተመርቆ ለሥራ ዝግጁ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በፍጥነት ተገንብተው ለሥራ ከሞላ ጎደል ዝግጁ ሆነዋል፡፡ የመንግሥት ዕቅድ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ ገበያ ታዋቂ የሆኑ አምራቾችን በማስገባት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ዕውን ማድረግ አልተቻለም፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሰሞኑን ያቀረበው የኦዲት ሪፖርትም ይህንኑ አሳሳቢ አፈጻጸም ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ከሁለት ሳምንት በፊት ባቀረቡት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን የሚያስተዳድረው የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ላይ አተኩረዋል፡፡ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከተገነቡት 20 የማምረቻ ሼዶች ውስጥ 11 መከራየታቸውን፣ በ2008 ዓ.ም. የተከራዩት ኩባንያዎች ከሚያመርቱት ምርት 130 ሚሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ ለማግኘት አቅዶ የተገኘው 16.9 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 13 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ከዚሁ ከቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ2009 ዓ.ም. 40 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማግኘት የተቻለው ግን 23.8 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱ 59.7 በመቶ ብቻ ነበር፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስገኛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ዞን በ2009 ዓ.ም. 50 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው ግን፣ 1.4 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከዕቅዱ 2.9 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ከቻይናና ከሌሎች በተገኙ የውጭ ብድሮች ደግሞ በአዳማ፣ በድሬዳዋና በሌሎች በርካታ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና የጥራት ደረጃ እየተገነቡ መሆኑን ለማረጋገጥ በተደረገ አዲት፣ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ19 ሼዶች መሠረተ ልማት ሙሉ በሙሉ በ2009 ዓ.ም. ገንብቶ ለማጠናቀቅ ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም የተፈጸመው ግን 27.7 በመቶ ብቻ መሆኑን ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ 15 የፋብሪካ ሼዶችንና ተጓዳኝ የአገልግሎት መስጫዎችን ሙሉ በሙሉ በ2009 ገንብቶ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የተከናወነው ግን 22.4 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በጅማ ዘጠኝ ሼዶችንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የያዘ ኢንዱስትሪ ፓርክ 70 በመቶ ለማጠናቀቅ ታቅዶ 5.4 በመቶ ብቻ ነው መፈጸም የተቻለው፡፡

የቦሌ ለሚ ምዕራፍ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርክን በ2009 ዓ.ም. 50 በመቶ ለመገንባት ቢታቀድም መፈጸም የተቻለው 13.1 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 50 በመቶ ለማድረስ ቢታቀድም 6.4 በመቶ ነው መፈጸም የተቻለው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የተጀመሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮችም አፈጻጸም ተመሳሳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከወደብ ጋር በባቡር መሠረተ ልማት ለማግኘት በጀመረው ፕሮጀክት የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር በአራት ቢሊዮን ዶላር ተገንብቶ ቢጠናቀቅም፣ የባቡር መስመሩ በጂቡቲ ከሚገኙ ወደቦችና በኢትዮጵያ ከደረቅ ወደቦች ጋር ባለመገናኘቱ የታሰበውን አገልግሎት መስጠት አልቻለም፡፡ በመሆኑም ከዚህ የባቡር መስመር አገልግሎት በሚገኝ ገቢ ለባቡር የተገባውን የውጭ ብድር ለመክፈልና ሌሎች የባቡር መስመሮችን ለመገንባት የተያዘው ውጥን ተጨናግፏል፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንም 115 ቢሊዮን ብር ዕዳ ተሸክሞ መንቀሳቀስ እንዳቃተው የሪፖርተር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

መንግሥት የገባበት አጣብቂኝና የተደቀነው ቀውስ

በመንግሥት ዕቅድ መሠረት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ተላቆ መሠረቱን ኤክስፖርት ተኮር በሆነ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ በመጣል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማመንጨት፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ኢንቨስትመንት ውስጥ መግባት፣ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ለሚገኘው የአገሪቱ ሕዝብ ተመጣጣኝ የሆነ የሥራ ዕድል መፍጠርና እኩል የሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ነገሮች ሁሉ ተምታተው አገሪቱን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከተዋታል፡፡

‹‹የአምራች ኢንዱስትሪው ባለመጠናከሩ የኤክስፖርት ዘርፉም መዋቅራዊ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፤›› ሲሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የአገሪቱን ልማት ለማፋጠን የሚረዳውን የውጭ ፋይናንስ በተለይም የንግድ ብድር ለማግኘትና ለመጠቀም እንቅፋት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ሪፖርተር ያገኘው የሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሁለት ዓመት ተኩል ግምገማ ሪፖርትም፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚን ማስቀጠል አሳሳቢ ደረጃ መሆኑን በይፋ ይገልጻል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ዋስትና መበደር የቻሉትን እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመሳሰሉ የልማት ድርጅቶች የተበደሩትን ሳይጨምር፣ የአገሪቱ የውጭ ብድር በ2010 ዓ.ም. ስድስት ወራት እስካለው ጊዜ ድረስ 25 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የልማት ድርጅቶቹን ጨምሮ አገሪቱ ያለባት አጠቃላይ ዕዳ ደግሞ 45 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በሌላ አነጋገር የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 1.8 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ደግሞ 1.3 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚህም የውጭ ብድር ጫና መንግሥት ተጨማሪ ብድር ማግኘት አልቻለም፡፡ የዓለም ባንክ በአዳዲስ ብድሮች ላይ የገበያ ዋጋ የወለድ ምጣኔ ሲጥል ቻይናም ይህንኑ ትከተላለች፡፡ በሌላ በኩል ለፕሮጀክቶች ለሚለቀቅ ብድር ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው የሚያስገኙት ገቢ ለብድር ክፍያ መዋሉን ለማረጋገጥ፣ በሦስተኛ አገር ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥትና የቻይና መንግሥት የሚያዙበት የባንክ ሒሳብ እንዲከፈት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች፡፡

በዚህም ምክንያት አዳዲስ ብድሮችን ማግኘት ባለመቻሉ መንግሥት ኢኮኖሚውን ማስቀጠል እንዳዳገተው፣ ይህም ተዘዋውሮ የአገር ውስጥ የታክስ ገቢን በመቀነስ መንግሥትን የበጀት ጫና ውስጥ እንደከተተው ይታሰባል፡፡

ይህም ማለት በአንድ በጀት ዓመት የተያዙ ፕሮጀክቶች በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ ሌላ በጀት ዓመት እየተዘዋወሩ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር አለመቻሉንና በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከድህነት በታች እንዲገኝ ምክንያት መሆኑን ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ ይናገራሉ፡፡ በ2008 ዓ.ም. በተደረገው ጥናት መሠረት ደግሞ በከተሞች ያለው የሥራ አጥነት ምጣኔ ወደ 16.9 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

‹‹የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር የበኩሉን ድርሻ የሚጠበቀውን ያህል መወጣት ባለመቻሉ፣ ሥራ አጥነት የአገሪቱ ማኅበራዊ ቀውስ ይሆናል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ይህንኑ እውነት የሚናገሩት የኢትዮጵያ ፕላኒንግ ኮሚሽነር ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የአገሪቱን ዕዳ ለመክፈል ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ኢኮኖሚውን ለማስቀጠል ደግሞ 7 ቢሊዮን ዶላር የግድ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ማግኘት የሚቻልበት ምንም ዓይነት ዕድል ባለመኖሩ፣ መንግሥት ግዙፎቹን የልማት ድርጅቶቹን ለመሸጥ የመገደዱን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -