Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻነት ኢትዮጵያ ደረጃዋን እንዳሻሻለች የተመድ ሪፖርት አመለከተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ ማክሰኞ ማምሻውን ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የኢንቨስመንት ሪፖርት መሠረት፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ያስመዘገበችውን ከፍተኛ ውጤት አስጠብቃለች፡፡

በተመድ የዓለም ኢንቨስትመንት ሪፖርት መሠረት፣ ባለፈው ዓመት ወደ አፍሪካ ከመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህም ከአንጎላ፣ ከግብፅ፣ ከናይጄሪያና ከጋና በመከተል አምስተኛ ደረጃ በመያዝ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደነበረች ይታወሳል፡፡

በአዲሱ ሪፖርት መሠረት ግን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት መጠን ዓምና ከነበረው የአሥር በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ማደጉ ተመልክቷል፡፡ በዚህም አንጎላን በመከተል ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ያስመዘገበች አገር ሆናለች፡፡ ካቻምና የ2.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ መመዝገቡን ተመድ ሪፖርት አድርጎ ነበር፡፡ በጠቅላላው በምሥራቅ አፍሪካ የተመዘገበው የውጭ ኢንቨስትመንት 7.6 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የቀጣናውን የውጭ ኢንቨስትመንት ድርሻ ለመውሰድ እንደቻለች ተጠቅሷል፡፡  

ምንም እንኳ ከውጭ የሚገባው የኢንቨስትመንት መጠን ሳያቋርጥ እየቀነሰ ቢሆንም በኢትዮጵያ የታየው ጭማሪ ከ400 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠም ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች ከሚታየው ቅናሽ አኳያ ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ማሳየቷን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

ከጄኒቫ የወጣው ሪፖርት እንዳሳየው አፍሪካ በጠቅላላው ከካቻምናው የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን አንፃር የ21 በመቶ ቅናሽ የተመዘገበበት ውጤት አሳይታለች፡፡ ወደ 46 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን፣ ካቻምና 59 ቢሊዮን ዶላር የተመዘገበበት እንቅስቃሴ እየተዳከመ መምጣቱ ታይቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰታቸው ጭማሪ ካሳዩ አገሮች ውስጥ ሞሮኮና ኬንያ ይጠቀሳሉ፡፡ ሞሮኮ ከዓምናው የ23 በመቶ ጭማሪ ያሳየችበትን የ2.7 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት ስታስዘመግብ፣ ኬንያ በበኩሏ የ71 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየችበትን የ672 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት አስመዝግባለች፡፡ ናይጄሪያ የ21 በመቶ ቅናሽ የተመዘገበበትን የ3.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች፡፡

ምንም እንኳ ለተከታታይ ዓመታት በአፍሪካ የተመዘገው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እየቀነሰ ቢመጣም፣ በተያዘው ዓመት የ20 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 50 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሊል እንደሚችል የተመድ ሪፖርት አስፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች