Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይናው መድኃኒት አምራች በ1.6 ቢሊዮን ብር ያስገነባው ፋብሪካ ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓመት ከ5.3 ቢሊዮን በላይ ብዛት ያላቸው መድኃኒቶች ያመርታል

በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ በመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታው በ1.6 ቢሊዮን ብር ወይም በ85 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው ሳንሼንግ ፋርማሲውቲካል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ (ኤስኤስፒ) ሥራ ጀመረ፡፡

ፋብሪካው በኢንዱስትሪ መንደሩ እሑድ ሰኔ ቀን 2010 ዓ.ም. በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመረቀበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በእንክብልና በፈሳሽ መልክ የሚመረቱ ከ70 በላይ መድኃኒቶችን ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ አቅም አለው፡፡ ሚኒዲ ሊዩ፣ የሳንሼንግ መድኃኒት አምራች ኩባንያ ዓለም አቀፍ የንግድ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ የተገነባው ፋብሪካ፣ በአምስት ቢሊዮን በላይ እንክብሎችንና ዱቄት ነክ መድኃኒቶችን፣ ከ300 ሚሊዮን በላይ የክትባት መድኃኒቶችን ጨምሮ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ግሉኮስ የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱና ከውጭ የሚገቡትን የተለመዱ መድኃኒቶች ብቻም ሳይሆን አዳዲስና ገበያው ላይ ያልነበሩ የመድኃኒት ዓይነቶችንም በማምረት ገበያውን ይቀላቀላል ያሉት ሊዩ፣ ፋብሪካውን ዕውን ለማድረግ ከሁለት ዓመታት ያነሰ ጊዜ ወይም 600 ቀናት ብቻ ማስፈለጉን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለፋብሪካው ግንባታ የዋለው የቦታ ስፋት 56,823 ካሬ ሜትር ቦታ ቢሆንም፣ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደ ገበያው ሁኔታ የማስፋፊያ ግንባታ የሚካሄድበት 16.67 ሔክታር መሬት የሚሸፍን የፕሮጀክት ሐሳብ እንዳለው የኩባንያው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለመድኃኒት ግዥ ብቻ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ፣ ከዚህ የሚብሰው ደግሞ የአገሪቱ የመድኃኒት አምራች ዘርፍ ለመድኃኒት ግዥ ከሚያወጣው ውስጥ ላለቀላቸው ምርቶች ሥርጭት እንዲውል 85 በመቶውን የውጭ ምንዛሪ እንዲሚያውል ይህም ለአገሪቱ ከፍተኛ የወጪ ጫና ምክንያት ከሆኑ ዘርፎች አንዱ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ያለ የፋርማሲውቲካል ምርቶች መዳረሻ በመሆን፣ የ20 ቢሊዮን ዶላር የመድኃኒት ግብይት በሚፈጸምበት ቀጣና ውስጥ መገኘቷም የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚያጎላው ገልጸዋል፡፡ 

በመድኃኒት አምራቹ ኩባንያ የጥራትና የቴክኒክ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሬድ ሒርጶ በበኩላቸው የፋብሪካው ዕውን መሆን ከውጭ የሚገባውን የመድኃኒት መጠን ጥራት ባላቸው የአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ብቻም ሳይሆን ወደ ውጭ ለመላክ የሚረዳ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር 170 ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማሠልጠን የፋርማሲ፣ የኬምስትሪ፣ የምሕንድስናና የሌሎችም ለምርት ሥራው ሚና ያላቸውን ባለሙያዎችን እንደቀጠረ አቶ ያሬድ አስታውቀዋል፡፡ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም የሰው ኃይሉን ወደ 250 ከፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡

በቻይና የሚገኘው ኤስኤስፒ እህት ኩባንያ በፀረ ካንሰር መድኃኒት ለማምረት የሚያስችለውን አቅም እንደገነባ የገለጹት አቶ ያሬድ፣ ወደፊት ኢትዮጵያም እያደገ ከመጣው የካንሰር ታማሚ ቁጥር አኳያ የመድኃኒቱ አቅርቦት ሊኖር እንደሚችል አሊያም እዚሁ ሊመረት እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ መሠረታዊና አስፈላጊ መድኃኒቶችን ከውጭ ታስገባለች ያሉት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ሲሆኑ፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በሕክምናው መስክ የቆየ ትብብር ስለመመሥረቷም ጠቅሰዋል፡፡ አምባሳደሩ በጠቀሱት መሠረት፣ እ.ኤ.አ. በ1974፣ 300 አባላትን የያዙ 20 የሕክምና ቡድኖችን ወደ ኢትዮጵያ ልካ ነበር፡፡ እነዚህም በወቅቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ ማገዛቸውን ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች