Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር ቅበላውን እንደሚቀንስ አስታወቀ

​አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር ቅበላውን እንደሚቀንስ አስታወቀ

ቀን:

አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር ተማሪዎች ቅበላን እየቀነሰ፣ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪዎችን ወደ ማስተማርና ወደ ምርምር እንደሚሸጋገር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ገለጹ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ይህን ያስታወቁት ዩኒቨርሲቲው ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚመራበትን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አተገባበርን አስመልክቶ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በእሸቱ ጮሌ አዳራሽ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ወቅት ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ወደፊት የምርምር ማዕከል እንዲሆን ከፍተኛ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ፣ ዕውቀት በማመንጨት ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ መካተታቸውን ዶ/ር አድማሱ አመልክተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚህ ጋር በተያያዘም ከዚህ ቀደም ሲል ያለውድድር የሚመደበው የምርምር ገንዘብ፣ ከአሁን በኋላ ውድድርን መሠረት ባደረገ መንገድ እንደሚመደብ ተገልጿል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዩኒቨርሲቲው የሴኔት ሕጉን እንዳሻሻለ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሴኔት ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆን ካለብን፣ እያንዳንዱ መምህር ምርምር መሥራት አለበት፡፡ የምርምር ውጤቱን በታወቁ ጆርናሎች ማሳተም አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር በድሮ የሴኔት ሕጉ ላይ ይህንን የሚያስገድድ ነገር የለም፡፡ አሁን ግን ይህንን አስገዳጅ የሚያደርግ ነገር እናካትታለን፤›› በማለት የሴኔት ሕጉን ለማሻሻል መነሻ ስለሆነው ጉዳይ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ሁሉም የዩኒቨርሲቲው መምህራን የኮንትራት ሠራተኞች ናቸው፡፡ ኮንትራታቸው ደግሞ የሚታደሰው በየሁለት ዓመቱ ነው፡፡ ስለዚህ መምህራን ኮንትራታቸው እንዲታደስ የግድ ምርምር ሠርተው ማሳተም አለባቸው፤›› ሲሉም በአዲሱ የሴኔት ሕግ ስለተካተተው አስገዳጅ መሥፈርት ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው ሁለተኛው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መጀመሪያ ዩኒቨርሲቲው ከተገበረው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ደካማና ጠንካራ ጎኖችን የገመገመ ከመሆኑም በላይ፣  ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜስን ዕቅድ ጋር የተያያዘ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ሲታቀድ ከመጀመሪያው ዕቅድ የተገኙ ድክመቶችንና ስኬቶችን ከማካተት አንፃር የተሠራ ሥራ ስለመኖሩ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ትልቁ ችግራችን ከመሠረተ ልማት ጋር የተያያዘ ነው፤›› በማለት እነዚህንም በሁለተኛው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለመቅረፍ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹የማስተማሪያ መሣሪያዎችና የምርምር ኬሚካሎች፣ የመምህራን ተነሳሽነት እንዲሁም የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን በሥራ ላይ ከማቆየት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለይተን፣ እነሱን እንዴት አድርገን ነው በሚቀጥለው ስትራቴጂካዊ ዕቅዳችን ላይ ማሳካት የምንችለው የሚለውን ተወያይተናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እንደሚጥር የገለጸው ዩኒቨርሲቲው፣ እ.ኤ.አ. በ2025 ከአፍሪካ ምርጥ አሥር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ለመሆን እየሠራ እንደሆነም በወቅቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም በቅርቡ የዓለም ባንክ ለአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የልህቀት ማዕከላትን ለማቋቋም ባዘጋጀው ውድድር፣ በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ ካሉ አገሮች ጋር ተወዳድሮ ዩኒቨርሲቲው በአራት የትምህርትና የምርምር መስኮች የልህቀት ማዕከል እንዲያቋቁም ገንዘብ ማግኘቱንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1942 ዓ.ም. 33 ተማሪዎችን በመቀበል ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በአሁን ወቅት ከ52 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ያስተምራል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ ከስምንት ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...