Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​መንግሥት በታገቱት 80 ኢትዮጵያውያን ምክንያት በኤርትራ ላይ ተመጣጣኝ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

​መንግሥት በታገቱት 80 ኢትዮጵያውያን ምክንያት በኤርትራ ላይ ተመጣጣኝ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

ቀን:

  • ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል

በቅርቡ ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር አካባቢ በባህላዊ ወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 80 ኢትዮጵያውያን ታጋቾችን በተመለከተ፣ መንግሥት በኤርትራ መንግሥት ላይ ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንደሚወስድ የካቲት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡ የዕገታውን ጉዳይም ሆነ የታጋቾች ማንነት በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዓርብ የካቲት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ስለታገቱት ዜጐች ከጋዜጠኞች ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር፡፡

ነገር ግን ቃል አቀባዩ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ከመስጠት ይልቅ፣ የኤርትራ መንግሥት ቀጣናውን የማተራመስ ድርጊቱን ስለቀጠለበት ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንደሚወሰድበት ገልጸዋል፡፡

‹‹ዕገታው የፀረ ሰላም ኃይሎች ድርጊት ነው፡፡ እነዚህን የፀረ ሰላም ኃይሎች ድርጊት የሚያግዝ፣ የሚያደራጅ፣ የሚያዘምትና አካባቢውን በማተራመስ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ያለው የኤርትራ መንግሥት ነው፡፡ ይህ መንግሥት በተለይ በፀረ ሰላም አቋሙ የተነሳ የተባበሩት በመንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ የጣለበት መሆኑ በሰፊው ይታወቃል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ድርጊቶችን እንደሚፈጽም ይታወቃል፡፡ ቀደም ብሎም በመንግሥት እንደተገለጸው ለኤርትራ መንግሥት አፀፋዊ ምላሽ ይሰጣል፤›› በማለት ቃል አቀባዩ አብራርተዋል፡፡

ነገር ግን ታጋቾቹ የተያዙበትን ሁኔታና ማንነታቸውን የመለየት ሥራንና የመንግሥት አፀፋዊ ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ከሪፖርተር ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ከዚህ በላይ ምንም ዝርዝር ማብራሪያ ልሰጥ አልችልም፤›› በማለት መልሰዋል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ቀደም ብሎ ከቀናት በፊት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በድንበር አካባቢ በወርቅ ፍለጋ ሥራ ላይ የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ዜጐች ላይ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለው መሆኑንና አስፈላጊውን ዕርምጃ እንደሚወስድ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በተመሳሳይ የኤርትራ መንግሥት ከግንቦት 7 እና ከሌሎች የሽብር ኃይሎች ጋር በመተባበር በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን የማተራመስ ሙከራ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በታገቱት 80 ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የኤርትራ መንግሥትም ሆነ ሌላ አካል እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ የለም፡፡

የኢትዮጵያውያኑን መታገት አስመልክቶ ቀደም ብለው የወጡ ዘገባዎች ቁጥራቸው 85 እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...