Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​ሙስና ውስጥ በተዘፈቁ የመሬት ዘርፍ ኃላፊዎች ላይ ክስ ለመመሥረት መረጃዎች ተጠናቀሩ

​ሙስና ውስጥ በተዘፈቁ የመሬት ዘርፍ ኃላፊዎች ላይ ክስ ለመመሥረት መረጃዎች ተጠናቀሩ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ዘርፍ የሚታየውን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታት በተወሰደው ዕርምጃ፣ ተጠያቂ ይሆናሉ በተባሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ ክስ ለመመሥረት መረጃዎች መጠናቀራቸው ታወቀ፡፡ በአመራሮችና በሠራተኞች ላይ የተጠናቀረው መረጃ ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መላኩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታው ኃላፊነት በተዘጋጀው ጥናት፣ 600 በሚሆኑ የመሬት መዋቅር አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ተጠያቂ ይሆናሉ የተባሉ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑ ታውቋል፡፡

በመሬት መዋቅር ሠራተኞች ላይ የሽግሽግ፣ የምደባና የማጥራት ሥራዎችን ለማከናወን በተካሄደው ጥናት በርካታ ሰዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

እነዚህን አመራሮችና ባለሙያዎች ተጠያቂ ማድረግ ያስችላል የተባሉ ተጨማሪ ማስረጃዎች እየተለቀሙና እየተጠናቀሩ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እየተላኩ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በተጨባጭ ተሳትፎ ያላቸው እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምንጮች እንደገለጹት፣ ተጠያቂ ከሚሆኑ ሠራተኞች በተጨማሪ ከነጭራሹ የሚሰናበቱ ሠራተኞችም አሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ በሌሎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች እንዲመደቡ ዝርዝራቸው ለሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ተልኳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በሥሩ ከመሬት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚያካሂዱ ስድስት ኤጀንሲዎች አሉ፡፡ አስተዳደሩ እነዚህን ዘርፎች ለማጥራት የመዋቅር ለውጦች፣ የሰው ኃይል፣ ሥልጠናና ፕወዛ በየጊዜው ቢያካሂድም ኅብረተሰቡ ግን በመዋቅሩ መርካት እንዳልቻለ ይነገራል፡፡

በተለያዩ መድረኮች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከማዕከል ጀምሮ እስከ ክፍላተ ከተሞች ድረስ ያሉ የመሬት መዋቅሮች የፈጠጠ ሙስና የሚታይባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ያለ እጅ መንሻ ጉዳይ ማስፈጸም የማይቻል መሆኑን እሮሮ ያሰማሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደላሎች የራሳቸውን ኔትወርክ ከሠራተኞች ጋር በመመሳጠር የዘረጉ በመሆናቸው፣ እጅግ አስቸጋሪ ቡድን እየተፈጠረ መሆኑ ነዋሪዎች በግል የገጠማቸውን በማንሳት አቤቱታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡

አስተዳደሩ ከዚህ በመነሳት በመሬት ዘርፍ ላይ አዲስ ጥናት ያዘጋጀ ሲሆን፣ ሠራተኞች ብዙም ተሳትፎ ያላደረጉበትን ጥናትና ግምገማ ማካሄዱ ታውቋል፡፡

በዚህ መሠረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ዕርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በበኩሉ በቅርቡ ተጠያቂ ይሆናሉ በተባሉት ላይ ክስ ይመሠርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...