- የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንቡ ተግባራዊነት ለሦስት ወራት ተራዘመ
የአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች ሰኞ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. አድማ መቱ፡፡ ለአድማው ምክንያት የሆነው በ2003 ዓ.ም. የወጣው የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ በመደረጉ ነው፡፡
ለታክሲ አሽከርካሪዎች ሥራ ማቆም በምክንያትነት የተጠቀሰው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ደንብ 208/2003 ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተግባራዊ መደረግ ቢጀምርም፣ የከተማው ታክሲ ማኅበራትና አሸከርካሪዎች በደንቡ ላይ ክፍተቶች ስላሉ ለመሥራት አዳጋች ናቸው ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አድማው በመመታቱ የከተማው ነዋሪዎች ትራንስፖርት አጥተው ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በደንቡ ላይ ለአሽከርካሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያዎች ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት፣ ደንቡ ለሦስት ወራት ሥራ ላይ እንዳይውል መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ውሳኔ በኋላ የተወሰኑ ታክሲዎች መንገድ ላይ መታየት ጀምረዋል፡፡