Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​‹‹የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ ቀድሞ አገሩ የመመለስ ተልዕኮ አለን››

ዶ/ር ደረሰ አየናቸው፣ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን

አዲስ አበባ ባለፈው ጥር ወር መገባደጃ ላይ ለሦስት ቀናት የዘለቀ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጽሑፎች ጉባኤ አስተናግዳ ነበር፡፡ በካፑቺን ፍራንቸስካዊ የምርምርና ጽሞና ማእከል ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው ጉባኤ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ምሁራንን ያሳተፈ ሲሆን በኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፎች፣ ሰነዶችና የመሳሰሉት ላይ ያተኮሩ ወረቀቶች ቀርበውበታል፡፡ በየሦስት ዓመቱ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የመካከለኛ ዘመን ታሪኳን የሚገልጹ በርካታ የጽሑፍ ቅርሶች በተለይ በግእዝ ቋንቋ እያላት በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ዐረፍተ ዘመኑን የሚመለከት የትምህርት ክፍል አለማቋቋሟ የውጭ ምሁራን ጉድ ያሉበት ነገር ነበር፡፡ ቀዳሚው ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የታሪክ ትምህርት ከሰጠባቸው አንዱ መካከለኛው ዘመን ታሪክ ቢሆንም አብዮቱን ተከትሎ በመጣው ማዕበል ደብዛው እንዳይታይ መደረጉ ይነገራል፡፡ አሁንም ከዚህ እምብዛም አልተለየም፡፡ ከአገሪቱ ይልቅ አውሮፓውያኑ በተለይም ጀርመንና ፈረንሣይ የኢትዮጵያን የመካከለኛው ዘመን ታሪክ በግእዝና ዓረቢኛ ላይ ተመሥርተው የሚያጠኑበት የራሳቸው ተቋም ሲኖራቸው በርካታ ሥራዎችንም ሠርተዋል፡፡ ሁሌም ‹‹ከሞኝ ደጃፍ…›› እንዳይሆን በሚል ከአገሩ ርቆ የነበረው የኢትዮጵያን የመካከለኛ ዘመን ታሪክ ትምህርት ለመመለስ የበቃው በ10 ዓመት ዕድሜው ዋዜማ ላይ የሚገኘው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የ600 ዓመት ዕድሜ ባስቆጠረችው የመካከለኛው ዘመንዋ ደብረ ብርሃን ከተማ የበቀለው ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የነገሩን በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር ደረሰ አየናቸው ናቸው፡፡ መሰንበቻውን በተካሄደው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጽሑፎች ጉባኤ ከቀረቡት 16 ጥናቶች አንዱ የእርሳቸው ሲሆን በ15ኛው ክፍል ዘመን የነበሩትን የመሬት ይዞታ ሰነዶችን አስመልክቶ  “Fifteenth Century Land Grant Documents of Wagada” በሚል የምርምር ሥራቸውን አቅርበው ነበር፡፡ ዶ/ር ደረሰ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን  ደግሞ በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ አግኝተዋል፡፡ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ በመንግሥት አስተዳዳር ላይ ያተኮረ መመረቂያ ጽሑፍ አዘጋጅተዋል፡፡ በዋነኛነት ከ1270 እስከ 1529 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ያለውን የኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ትኩረት አድርገው ይሠራሉ፡፡ በሦስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፋቸው የኢትዮጵያ መካከለኛ ዘመን ታሪክ በውስጥና በውጭ ያለውን አስተዳደር እንዲሁም በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚተሳሰሩ በምልዐት ዳሰዋል፡፡ ስለ ደብረ ብርሃን  ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል እንቅስቃሴ ዘንድሮ በሁለተኛ ሴሚስተር በሚጀምረው በታሪክ የዶክትሬት ትምህርት ዙሪያ ዶ/ር ደረሰ አየናቸውን ሔኖክ ያሬድ  አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪም ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ መካከለኛው ዘመን ታሪክ ትምህርትን በተመለከተ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተሰማ የምሥራች አለ፣ ስለ ጉዳዩ ቢያብራሩልን?  

ዶ/ር ደረሰ፡- ጥሩ የምሥራች ነው፡፡ የመካከለኛውን ዘመን ወደ ቀድሞ አገሩ የመመለስ ተልዕኮ አለን፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ማስተማር ሲጀመር የተጀመረው ከመካከለኛው ዘመን ታሪክ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና ፕሮፌሰር ሥርግው ሀብለሥላሴን የመሰሉ የመካከለኛው ዘመን መምህራንን ማንሳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ 1970ዎቹ አካባቢ ከአብዮቱ ጋር በተያያዘ  የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ጨርሶ እንዳይታይ ሆነ፡፡ እንዲያውም ዛሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለው የታሪክ አጠናን ክፍል ኮንቴፖረሪ ሒስትሪ (የአሁን ዘመን ታሪክ) ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል፡፡ ስለዚህ በመካከለኛው ዘመን የጀመረው ዩኒቨርሲቲ የጨረሰው ባለንበት ዘመን ነው፡፡ በመካከለኛው ዘመን ታሪክ ላይ ልዩ አስተያየት ነበር፡፡ ይህ ልዩ አስተያየት የመካከለኛው ዘመን ታሪክ እንዳይታይ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ወጣቶቹ ተማሪዎች ያተኮሩት የውጭ ፍልስፍና ወደዚህ ማምጣት ላይ ነበር፡፡ ይህ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስላሳደረ ሰዎችም ትምህርቱን እንደ ኋላ ቀር እንዲያዩት አደረገ፡፡ በተለይ ግእዝን የሰሜኑ ቋንቋ ብቻ አድርጎ የማየት ነገር አለ፡፡ እንዲያውም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካሪኩለም በማስተርስ ፕሮግራም እንዳይሰጥ ያደርጋል፡፡

የኢትዮጵያ አብዮት ራሱ የተጀመረው ከውጭ ፍልስፍና ጋር በተያያዘ ነው እንጂ ከኢትዮጵያ መካከለኛው ዘመን ወይም ከጥንቱ የኢትዮጵያ ዘመን ጋር የተዛመደ አልነበረም፡፡ ውጤታማ ያልሆነው በዚህ ምክንያት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በእኛ አገር ያለው ገጽታ ይሄ ሲሆን በውጭ አገር ግን ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡ ትኩረት ከሰጡት አገሮች ጀርመንን ማንሳት ይቻላል፡፡ ጀርመን በመካከለኛው ዘመን ጥናት ላይ ትልቅ ማዕከል ከፍቷል፡፡ ሀምቡርግ የሚገኝ ሲሆን፣ ሂዮብ ሉዶልፍ ሴንተር ይባላል፡፡ የተጀመረው በ17ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ በብራና ላይ በግእዝና በዓረብኛ የተጻፉ መጻሕፍትን ተተርጉመው በእነሱ ማዕከል ይገኛሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በፈረንሣይ ፓሪስ ፓንቲን ሶል በሚባል ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ጥናት ማዕከል ውስጥ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል አለ፡፡ በዛ ውስጥ ፈረንሣዮች ከፊሎሎጂ ውጭ በታሪክ ጥናት ላይ በማተኮር ከ15 ዓመት በላይ ሲመራመሩ ዘልቀዋል፡፡ በቅርቡ እዚህ አዲስ አበባ በተካሄደው ሁለተኛው የኢትዮጵያ መጻሕፍት ኮንፈረንስ ላይ ከተሳተፉት መካከልም ይገኙበታል፡፡ በመካከለኛው ዘመን ታሪክ ላይ ፒኤችዲ የሠሩ ተመራማሪዎች የፈረንሳይ ናቸው፡፡ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ ከክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖት አንፃር ሁሉንም ጥናት አጥንተዋል፡፡ በፈረንሣይኛ ቋንቋ ብቻ ከ20 የማያንሱ መጻሕፍትና የጥናት ወረቀቶች ታትመዋል፡፡ በሕትመት ዝግጅት ላይ ያሉም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ቀልብዎ እንዴት አረፈ?

ዶ/ር ደረሰ፡- ለከፍተኛ ትምህርት በ1993 ዓ.ም. ወደ ፈረንሣይ ሄጄ በሰባት ዓመት ውስጥ ማስተርስና ፒኤችዲ በሠራሁበት ጊዜ ነው፡፡ በትምህርት ሒደት ዘልቄ ስሄድ ባየሁት ነገር በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ እኛ አገር ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ እዛ ግን በደንብ ተጠናክሮ፣ ቤተ መጻሕፍት ተዘጋጅቶለት ብዙ ተማሪዎች በተለይም ነጮች በሚማሩበት ጊዜ ለኔ አዲስ ነገር ነበር፡፡ ትምህርቱን እንደጨረስኩ በ2003 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ ወደ አገሩ ለመመለስ ወሰንኩ፡፡ የደብረ ብርሃን የኒቨርሲቲ አስተዳዳርን አመሰግናለሁ፡፡ የመጀመሪያውን ዓመት ካሪኩለም በመቅረጽ ሁለተኛውን ዓመት ደግሞ በትምህርት ቤቱ የማስተርስ ፕሮግራም እንዲጀመር ተወሰነ፡፡ ካሪኩለማችን በሴኔትና በቦርድ ፀድቆልን ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ የማስተርስ ፕሮግራም አለን፡፡ ወደ ሁለት ባች አስመርቀናል፡፡ ደስ የሚያሰኘው ይኼ የማስተርስ ፕሮግራም በማታና በክረምትም ክፍለ ጊዜ አለ፡፡ ከአምና ጀምሮ ወደ 25 የሚደርሱ ተማሪዎች በክረምት ፕሮግራም፣ በተለይም ፕሪፓራቶሪ ማስተርስ በሚባለው ፕሮግራሙ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ወደፊት ለሚከፈቱት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ለማዘጋጀት ሲል ወደ 15 የማስተርስ ተማሪዎች ልኮልናል፡፡ አካዴሚው የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ጥናትን ለማስፋፋት መሠረት ጥሏል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ የፒኤችዲ ፕሮግራም እንድንጀምር ቦርድ አጽድቆልናል፡፡ ከፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በዚህ ሴሚስተር እንጀምራለን፡፡ ደስ የሚያሰኝ ዕርምጃ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በመካከለኛው ዘመን ታሪክ በአገራችን ብቸኛው ነው፡፡ ደብረ ብርሃን በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የመካከለኛው ዘመን ቋሚ ከተማ ነበረች፡፡ በዛ ዘመን ብዙ መጻሕፍት፣ ብዙ ሕጎችና ሥርዓቶች ተመሥርተዋል፡፡ ንጉሡ ደብረ ብርሃን 12 ዓመት ተቀምጠው የጻፉ ስለመሆኑ መረጃዎች አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ ማስተማር ለመጀመር የሚያበቃው መሆኑን ቦርዱ ወስኗል፡፡ ትምህርት ክፍሉ የዩኒቨርሲቲው አንድ የልቀት ማዕከል እንዲሆን ወስኗል፡፡ ከ40 ወይም 50 ዓመት በኋላ የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ ጥናት ወደ አገሩ መልሰናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ተማሪዎች አሉ?

ዶ/ር ደረሰ፡- በማስተርስ ወደ 25 የሚጠጉ የክረምትና ሦስት የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች አሉ፡፡ እነዚህ በሚቀጥለው ዓመት ይመረቃሉ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ አዲስ የገቡ አምስት የማስተርስ ተማሪዎች ይኖሩናል፡፡ በፒኤችዲ ደግሞ እስካሁን በእቅዳችን መሠረት አምስት ተማሪ እንጠብቃለን፡፡ እስካሁን ሁለት ተመዝግበዋል፡፡ በዚህ ሴሚስተር ትምህርት እንጀምራለን፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመሪያ ዲግሪ ያሏችሁ ተማሪዎችስ?

ዶ/ር ደረሰ፡- ከ40 የማያንሱ ተማሪዎች አሉ፡፡ በታሪክ ትምህርት ክፍል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ዓመት የሚማሩ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡-  እስካሁን የታሪክ ትምህርት ብዙ ትኩረት አላገኘም አሁን የታሪክ የማንሰራሪያ ጊዜ ነው ለማለት ይቻላል?

ዶ/ር ደረሰ፡-  ለኔ እንደሚገባኝ ጊዜው የታሪክ ማንሠራራት ነው፡፡ ዛሬ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለ አገሩ ለማወቅ ይጠይቃል፡፡ ብዙ ሰው የታሪክ መጻሕፍት የማንበብ ፍላጎት አለው፡፡ እኛም በየወሩ ሴሚናር እናዘጋጃለን፡፡ ይሄ ተነሳሽነት የመጣው ከጓደኞቻችንና ከሥራ ባልደረቦቻችን በመጣ ጥያቄ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ በአዲሱ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሚዘጋጁ ከታሪክ ጋር በተያያዙ ሴሚናሮች ላይ ብዙ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ ከግለ ታሪክ ጀምሮ ትልልቅ ዜና መዋዕሎች የተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ይተረጐማሉ፡፡ ሰዎችም ይገዛሉ፡፡ ብዙዎች ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ለማወቅ ይሻሉ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ድሮ ከተደበቀበት ዛሬ እያንሰራራ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች እየተከፈቱ ነው፡፡ በመቶሺ የሚቆጠሩ ተማሪዎችም አሉ፡፡ በሚያስገርም ሁኔታም ታሪክን የማወቅ ፍላጎት አላቸው፡፡ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሶሻል ሳይንስ ተማሪ ያልሆኑትንና ናቹራል ሳይንስ የሚማሩትን ስለ ታሪክ የማወቅ ፍላጎታቸው መጠይቅ አቅርበን ነበር፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ የመማር ፍላጎት አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ስም ያቋቋማችሁት ምንድነው?

ዶ/ር ደረሰ፡- አሁን ባለንበት ሁኔታ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በታሪክና ቅርስ አስተዳደር የትምህርት ክፍል ውስጥ የዘርዐ ያዕቆብ የጥናት ክፍል (ዩኒት) በሚል አደራጅተናል፡፡ የራሱ ቤተ መጻሕፍት አሉት፡፡ የማስተማሪያ ክፍሎችም ያሉት ሲሆን፣ ብዙ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ፡፡ ጥናትና ምርምር፣ ቁፋሮዎች፣ ሴሚናሮች እናደርጋለን፡፡ ከፓሪስ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎችም ጋር በጥምረት እናዘጋጃለን፡፡ ወደፊት ይኼንን ክፍል ወደ ማእከል ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ወደፊት ሰፊ ማእከል ሲሆን በሰፊው የኢትዮጵያ መካከለኛ ዘመን ታሪክ ጥናት ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ከአርኪዮሎጂ ጋር የተያያዘ ሥራስ አለ?

ዶ/ር ደረሰ፡‑ በአርኪዮሎጂ ላይ ጥናት የጀመርነው በ1990ዎቹ ገደማ ነው፡፡ መንዝና ይፋት የተሠሩ ጥናቶች አሉ፡፡ ወደ 16 ዓመታት የወሰዱ ሲሆን፣ በፈረንሣይኛ ቋንቋ ተተርጉመውና ታትመው ይገኛሉ፡፡ ወደ አማርኛ እንዲመለሱም ብዙ ጥያቄ አለን፡፡ ለሕዝቡ የምናደርስበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው፡፡ ማዕከሉም ይኼንን ሥራ ለወደፊት ይሠራል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡‑ ከታሪክ ጋር በተያያዘ ኅብረተሰቡ ሊያውቅ ይገባል የሚሉት ነገር ምንድነው?

ዶ/ር ደረሰ፡‑ ለማንኛውም አገር ታሪክ የሥልጣኔ መሠረት ነው፡፡ ታሪክ የፍልስፍና፣ የሃይማኖትና አስተሳሰብ መሠረት ነው፡፡ ታሪካችንንና ቅርሳችንን አጥንተን ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...