Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​ትንሽ ገፋ!

እነሆ መንገድ። ከቦሌ ወደ ስታዲየም ልንጓዝ ነው። ከተማው ሳይፈርስ፣ ሰላም ሳይደፈርስ፣ ደዌ ሳያጠቃን፣ እግር መጓዝ ሳይታክተው ታክሲ አደመ ተብሎ አገር ይፋንናል። ላለመራመድ በቂ ስንቅ ይዘን በሽሙጥ እንታሻለን። ይኼው እንደለመድነው በየጥጋጥጉ ቆመናል። የከተማ ነዋሪው ዓይኑ ወዲያ ወዲህ ይቃብዛል። የታክሲ ዘር ጠፍቷል። ከሰማዩ በቀር ሰማያዊ ቀለም ራሱ የሸፈተብን ይመስላል። የማይሸፍትብን ግን ምን ይሆን? የማያድምብን ማን ይሆን? የማናድምበትስ? የማንነጫነጭበት ሕግና ሕግ አስከባሪስ? ጥያቄ ብቻ። ምፀቱ ጉድ። “ኧረ ዛሬስ በጤና አይመስለኝም። ኧረ አገሩ ሰላም አይመስለኝም?” ትላለች አንዲት ጠና ያለች ሴት በነጠላ ፊቷን እየሸፈነች። “ምንድነው ቀኑ ዛሬ? የዓደዋ ድል መታሰቢያ በዓል ዛሬ ነው?” ለነገሮች ደንታ አልባ መሳይ ወጣት ይጠይቃል። “ታዲያ ዓደዋ ቢሆንስ የዘመትነው የዛሬ መቶ ሃያ ዓመት። የተጓዝነው በእግር። ያሸነፍነው በባዶ እጅ። ወኔ ውሎ ይግባና፡፡ ታክሲና ዓደዋን ምን አገናኛቸው?” ብሎ ሌላ ወጣት ሲናገር “ምን ይታወቃል? ዘንድሮ እኮ ወራሪው በየአቅጣጫው ነው። ዓደዋም ወደ ብዙ ዓደዋዎች ተሸጋግራለች፤” ትላለች ሴትዮዋ።

“ጉድ ፈላ! በአንድነት ስንወደስ የኖርን ሕዝቦች እርስ በርስ ተጠማምደናል እያልሽ ነው? እንዴት እንዲህ ትያለሽ?” ወጣቱ ነገር ሲያበላሽ፣ “ያላልኩትን አለች እያለ ያነካካኛል እንዴ ይኼ? ምነው ሰው እንዲህ ነገር ለማቀጣጠል ከእንቢልታና ከመለከት ቀደመ?” ብላ አንገቷን ወዘወዘችበት። “እህ? ወደን መሰለሽ? ትብታባችን እያደር ባሰበታ። ሸምጋዩም ያለዘበ እየመሰለው እሳት ላይ ቤንዚን ያርከፈክፋል። በቀናነት የታሰበውና የታለመው ‘ፕላን’ ሁሉ ድምፁ ሳይሰማ መጣ ተብሎ ድምፁ ሳይሰማ ይሸኛል። ሥራችን ሁሉ በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ይተረጎማል። ሲተረጎምም ያለ ሞጋችና አሳማኝ ምክንያት ይታጠፋል። እስኪ በየት አገር ነው ወላጅ ልጁን ጡት ነከሰ ብሎ ወተት የሚነፍገው?” እያለ ፈንጠር ብሎ የቆመ ጎልማሳ የሚገባንም የማይገባንንም ስንክሳር እያጣመደ ይለፈልፋል። በዚህ መሀል አንድ ለሕዝቧ የሆነች ጃጉዋር ብቅ አለች። እልፍ ለመንገድ የሆንን ተጓዦች ተረጋግጠን ገባን። አንድ መንገድ፣ አንድ አማራጭ፣ አንድ ሐሳብ ግን ብዙ ተጓዥ!

ጉዞ ጀምረናል። “ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ’ እንዳልተባለላችሁ፣ ዕድሜያችን ቆሞ ሥራችን ቆሞ ምነው ጠፋችሁ ዛሬ? ለማን ተዋችሁን?” ጋቢና የተሰየሙ አዛውንት ሾፌራችንን ይጠይቃሉ። “ኧረ ተውኝ አባት። ምቀኛ! ምቀኛ ብቻ እኮ ነው የከበበኝ እኔንማ፤” ሾፌሩ የቆረቆረው ነገር እንዳለ ያስታውቃል። “ምቀኛ ከሩቅ አይመጣ፤” አዛውንቱ በጥበብ ያወጣጡታል። “ታዲያስ እኔ ዛሬ አድማ እንደሚደረግ አልሰማሁም። የነገረኝ የለም። ገና ለገና ሥራዬን በትጋት ስለምሠራና ጥሪት ለመያዝ ስለምባክን የመንግሥት ወገን ነው ለማስባል ‘አትንገሩት’ ተብሎ ይኼው አስገኙኝ፤” ሲላቸው “አሃ አድማው እርስ በርስም ነው?” አሉት። “አይገርምም? ቆይ ግድ የለም…” ሾፌሩ የእኛ መቸገር ሳይቸግረው የእሱ ስም በአግቦ ሽሙጥ መበላቱ ያብከነክነዋል።

 “ድሮስ ለእኛ ማን ያስባል? ሁሉም ለራሱ ጉዳይ ብቻ ነው የቆመው፤” ትላለች ከአዛውንቱ ጎን የተሰየመች ወጣት። “ዘንድሮ ራስ ለራስ ነው የእኔ ልጅ። አለበለዚያ በታክሲ ፌርማታው ቆመሽ መቅረትሽ ነው፤” ብለዋት ወደ ሾፌሩ ዞሩ። “እኔ የምለው? የመንግሥት የግል ብሎ ታርጋ ነው እንጂ ሰውም አለ አንዴ? ነው አዲስ የወጣው የትራንስፖርት ሕግ እንዲህ ያለ ነገር አካቶ ኗሯል?” ቢሉት፣ “ነገር ያለውስ እኛ መሀል ነው እንጂ፣ ቀድሞም መንግሥት የሕዝብ፣ ሕዝብም የመንግሥት ነበር ወጉ…” ብሎ መሪውንም ጨዋታውንም ጠምዝዞ ዳር ያዘ። ወያላው ላንዳች የመቀጮ ሥጋት ትርፍ አግበሰበሰ። “ምነው ታዲያ መደማመጥና መግባባት በአድማና በጩኸት ተለወጠሳ?” ብለው አዛውንቱ ለብቻቸው ሲያጉተመትሙ፣ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ጎልማሳ “ፈርዶብን! ገሎ በመሞት ካልሆነ በጨዋ ደንብ በሥልጡን አካሄድ ጠላት ማሳፈር አይቀናችሁ ሲለን፤” ሲል ተሳፈሪው የተስማማ መሰለ። ጥቃቅኑ ሽንፈት ታላላቅ ድሎችን ሲያደበዝዝ ማየት እንዴት ያማል፡፡

ወደ መጨረሻ ወንበር የተሰባሰቡ ወጣቶች ስለአነጋጋሪው የትራፊክ ሕግ የደራ ወሬ ይዘዋል። “ቆይ ግን . . .  ሕግ፣ ሕግ ነው አይደል ጎበዝ? . . .  ”  እያለ ይንጣጣል አንድ ባለአምባር። “ነው!” ይላል ጀማው። “ታዲያ ለምንድነው ሐሳብ ወይ መንገድ ይመስል እየተቆራረጠ የሚወጣው? አልያም የሚሻረው? ለምሳሌ በሁለት እጅ መሪ ይዞ ማሽከርከር ገና ተሽከርካሪው ሲሠራ የታለመ የተፈታ ጉዳይ ነው። አይደለም? ነው? . . . አዎ! ምንድነው ታዲያ ሀሞት እንደሚጋት ጥጃ እያሰለሱ ማወጅ?” ከማለቱ መሀል መቀመጫ አጠገቤ ያለችው  ባለ ነጠላ፣ “ጥጃ ሀሞት ሲጋት ዛሬ ገና ሰማሁ፤” ትለኛለች። “ሥራ ፈጠራ በሚለው ያዘው፤” ይለዋል ከጎኑ የተቀመጠ ባለ መነጽር ጥጃን ሀሞት ወደ ጋተው ዞሮ። “ፍሬንድ ያለው ተመችቶኛል። እኛስ ብንሆን ሥራ መፍጠር ሲያቅተን ሥራ በፈጠሩ የመንገድ ባለቤቶች ተንጨርጭረን ማደም መፍትሔ ነው?” ባዩዋ ደግሞ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ጥጓን ይዛ የተሰየመች ቀዘባ ናት።

“ይልቅ ይኼን እንተወውና እውነት ለመኪና አደጋ መንስዔ በሆኑና በሰለባዎቻቸው መካከል መፍትሔ የሚሆን ሕግ ለምንድነው የማይቀረፀው ወደሚለው እናምራ። ሲኖትራክ፣ አይሱዙ፣ ኤፍኤስአሮች እውነት ከአውቶሞቢሎቻችን እኩል በመኪና አደጋ ቀዳሚ እንድንሆን ያዋጡት መዋጮ እኩል ነው?” ይላል። “እንዴ የባለንብረቶቹ አልበቃ ብሎ ለግዑዛንም 8100 ተዘጋጀ እንዴ?” ሲል ጎማ ላይ የተሰየመ ተሳፋሪ ቀላቀለ። “ኧረ ጣቢያህን አስተካክል ወዲህ ነው፤” ስትለው ከጎኔ፣ “ጣቢያ በመቀያየር ከመዋጮ ማምለጥ አልቻልንማ፤” ብሏት አረፈው። “ሄይ! ሄይ! ከአጀንዳ ውጪ ውይይቱን እየጠለፋችሁ የምታስቸግሩ ሰዎች ዕርምጃ ይወሰድባችኋል። አብዮታችን የተጠለፈው ይበቃል! እንወያይበት፤” ጎልማሳው ተኮሳተረ። “አኼ! ዘንድሮ ማን ማንን ፈርቶ? ማን ማንን አክብሮ? ይሰሙኛል ብለህ ነው? እንዲያው እኮ ነው ያለፍሬ  . . .”  አዛውንቱ ነገሩን ይባስ አዳፈኑት። ብለን ብለን የማንታማበት ወሬ ጀምሮ መጨረስ አቅቶን አረፈው?  እንግዲህ ሌላ ሌላውን አለማሰብ ነው። መንገድ ያለ ሐሳብ ደግሞ  . . . !

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው በገዛ እጁ መድረኩን አጣቦ መፈናፈኛ ጠፍቶት አንዳችንን ካንዳችን ገንዘብ ያቀባብለናል። “አተርፍ ባይ አጉዳይ” ትላለች ከጎኔ። ወዲያ ሞተሩ ላይ ተቀምጦ ከሥር ወበቅ ከላይ ነፋስ እያጣፋው የተቀመጠ አንዱ ደግሞ፣ “ግን ይኼ ሁሉ ሰው ሲጓዝ የሚውለው ሥራ የለውም እንዴ?” ብሎ ይጠይቃል። “ካልተቀመጡ ሥራ አይሠራም በቃ? የቢሮ ሥራ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ቀረ። ተቀምጦ መብላት ግን አሁንም ያለ መሰለኝ፤” ይላል ከመጨረሻ ወንበር አንዱ። “እናንተ ሥራውን ትላላችሁ ኢትዮጵያ ራሷ ድሮ የቀረችውን?” ትላለች ሌላዋ። “እግዚኦ! ይኼ  ጭፍን ጥላቻ፣ ፍረጃ፣ ድጋፍና ተቃውሞ በቃ እያደር ይባስበት?” የሚለው ጎልማሳው ነው። “ሃይ ባይ ተሰሚ፣ ተናጋሪ ተብዬው ሁሉ ዝም ብሎ ድሮስ ምን ትጠብቃለህ?” አዛውንቱ ናቸው። “እህ በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ’ ሲሆን ታዲያ ምሁራኖቻችን ምን ያድርጉ?” የሚለው ሦስተኛ ተደርቦ ምቾት የሚነሳኝ ተሳፋሪ ነው።

“ኤድያ! ኢኮኖሚውን ግብርና እየመራውም እንኳን ምሁር ገበሬም አልተከበረም፤” ብላ ያያያዘች መስሏት አንዷ ስትሰርብ፣ “እህቴ ዋናው ቻፓው ነው። አቆጣጠሩን ለቻለበት ክብር ቀስ ብሎ ይመጣል። ይልቅ ጥያቄዬን ምናለበት በቅጡ ብትመልሱልኝ?” ብሎ ቱግ አለ ያ ሞተር ላይ የተቀመጠው። “ምን ነበር ጥያቄው?” ከመባሉ፣ “ጥያቄውማ ይኼ ሁሉ ሰው ቀኑን ሙሉ ሲጓዝ የሚውለው ምን እየሠራ ነው?” ጥያቄውን ደገመው። መልሱ ሁላችንንም ፈገግ አሰኘን። ለበጣው፣ “ሁላችን አድመን አልያም አድበን እንዴት ይሆናል ብለን ነዋ። ተወን እንጂ በመቀናጀት ቢያቅተን በመቃበዝ ተራ ገብተን አገራችንን እናሳድጋት፤” ተብሎ የተሰጠው መልስ የጫረው ነው። ግን ለስንቱ ተራ ገብተን ልንችለው ነው?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። “ብቻ . . . ኢትዮጵያዊ ባልሆን ይቆጨኝ ነበር፤” ብሎ ጎልማሳው ነገር በሆዱ መቋጠር ጀመረ። “ብቻህን’ ደስ አትልም። ምነው ዘርግፈው እንጂ ይውጣልህ፤” ከአጠገቡ የተቀመጠ የፌስቡክ ሱሰኛው ቆሰቆሰው። “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል…” ጎልማሳው ሳይጨርስ፣ “መቼስ ቢሆን ሆድ ሞልቶ ያውቃል እንዴ?” ቀዘቢት ስታቋርጠው፣ “አስጨርሱኛ! ስታስጨርሱኝ እኮ ነው የሚገባችሁ። እንዴ ወሬ እኮ ሥልጣን አይደለም ያልቃል። ሺሕ ዓመት አልገዛ . . .  ማለቴ አላወራ፤” እያለ ጎልማሳው ጥቂት አዋዛን። በኋላ፣ “እንዲያው ያን ጊዜ በአንድነት ነቅለን ወጥተን ዓደዋ ድረስ ተጉዘን ተባብረን በአንድ ክንድ ጠላትን አባረን ስናበቃ ምነው ዛሬ ለመበተን እጅ ሰጠን? ምነው ዛሬ ለቁርሾና ለቂም ጆሮ ሰጠን? ይኼው ነው ‘ብቻ’ የምትለዋል ውስጥ ያፈንኩት፤” ብሎ በቁጭት አንገቱን ደፍቶ ተብከነከነ።

“ይቅርታ ወንድም! አንድም ይኼ የጅምላ ውክልና ነው እውነትን አጥርተን እንዳናይ እያጥበረበረን ያለው። ለምሳሌ ለእኔ ዓደዋ እንደማንኛውም የሰው ልጅ አሳፋሪ የጥፋት ፍጅት ይታየኛል ብል አትደንግጡ። ምክንያቱም እኔ በፖለቲካና በመልከዓ ምድራዊ ክልል በተወሰነ ዜግነት ብቻ አላምንም። የሰው ልጅ ዘር ነኝ ብዬ አምናለሁ። ተሸናፊውም አሸናፊውም የእኔ ወገን ነው ብዬ አምናለሁ። ‘ኢት ኢዝ ማይ ራይት!’ ‘እንቢ! ዘራፍ! የሰው ዘር አባል ነኝ’ ነው ፉከራዬ። በአጭሩ  . . . እእ . . . የእኛ የእኛ አስተያየትና አቋምም ታሳቢ ቢደረግ፣ ከተቻለ ደግሞ ሁላችንም በመላው የሰው ዘር አባልነት ብናምንና ኬላ ብንጥስ  . . . እእ . . . የሚሻለው እሱ ነው፤” ብሎ መጨረሻ ወንበር ላይ አንገቱ ላይ እራፊ ጨርቅ የጠመጠመ ወጣት ተናገረ። ሁሉም ዓይኑን አጉረጥርጦ አየው። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ ታክሲያችን ጥግ ስትይዝ አዛውንቱ፣ “እናንተ ልጆች እባካችሁ እውነት አጠራን እያላችሁ እውነት እንዳታድበሰብሱ አደራ! አደራ ኋላ! ምንም ቢሆን ምን ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀለውም፤” እያሉ ወረዱ። ወጣቱ በተናገረው ነገር የቆመበት የጠፋው፡፡ ‘ከዓደዋ ወዲህ ነን ወዲያ?’ እያለ ግራ ገብቶት ቆሞ ቀረ። ገሚሱ የለመደውን ሙጥኝ ብሎ ገሚሱ ቀለም አልባ ገድል እስኪዘክር ናፍቆ ተመመ። እስኪ አንዳንድ ቀን ከቀለም በላይ ብናስብ ምን ይለናል? ዓደዋ ትናንትም ዓደዋ ነገም፣ ሁሌ የእኛ! ግን ትንሽ ገፋ! ትንሽ ገፋ! ምን ይመስላችኋል? መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት