Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​አልጋ በአልጋ ያልነበረው የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ ምሥረታ እውን ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ወቅት 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በገበያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ 16ቱ በአክሲዮን ኩባንያ የተዋቀሩ የግል ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ አንዱ በመንግሥት ባለቤትነት የተመዘገበ ነው፡፡ ሁሉም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጥቅል የሀብት መጠን ከአራት ቢሊዮን ብር የበለጠ አይደለም፡፡ እስከ 2007 መጨረሻ ድረስ ጥቅል ካፒታላቸው ሲመዘን ደግሞ 2.7 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

የኢንሹራንስ ባህሪ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውና በአገር ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማጠናከር ብሎም የሚሰጠውን የመድን ሽፋን ከፍ ለማድረግ ከአገር ውጭ ባሉ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያዎች ጋር ተባብሮ መሥራት የተለመደ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የአንድ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ያለው ቢሆንም፣ ይህን የጠለፋ ዋስትና የሚሰጥ ኩባንያ ባለመኖሩ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና የሚገዙት ከኢትዮጵያ ውጭ ካሉ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያዎች ነው፡፡

የጠለፋ ዋስትና አገልግሎቱን የሚያገኙትም በውጭ ምንዛሪ ክፍያ በመፈጸም ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓመት ከሚሰበስቡት ጠቅላላ አረቦን ውስጥ 30 በመቶውን ለጠለፋ ዋስትና አገልግሎት ያውላሉ፡፡ ይህንን አገልግሎት በአገር ውስጥ ለመጀመር እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከሰባት ዓመታት በላይ ቢሆነውም፣ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሪ ኢንሹራንስ አክሲዮን ኩባንያ በይፋ ተመሥርቷል፡፡

የኩባንያው አደራጅ ኮሚቴ በዕለቱ ባቀረበው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ባጠናው የአዋጭነት ጥናት መሠረት የኢንሹራንስ ኩባንያ መመሥረት አዋጭ መሆኑ የተረጋገጠ መሆኑ ታምኖ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑን ያሳያል፡፡

የሚመሠረተው አገር በቀል ሪ ኢንሹራንስ ኩባንያው እያንዳንዳቸው 10,000 ብር ዋጋ ያላቸው 100,000 አክሲዮኖችና አንድ ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ከዚህም ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር በመጀመሪያ ክፍያ እንዲከፈል፣ ቀሪው የአክሲዮን መዋጮ የኩባንያው ቦርድ ወደፊት በሚወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲከፈል በመወሰን ወደ ሥራ እንደተገባ የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኪሮስ ጂራኔ ገልጸዋል፡፡

ኩባንያውን እውን ለማድረግም በአደራጅ ኮሚቴው የቀረቡት አመልካቾች ሰነድ በጥልቀት የመረመረ ሲሆን፣ በአገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ይህን ትልቅ የኢንሹራንስ ኩባንያ ምሥረታን በፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነት ለመምራት ያላቸው ዝግጁነት አስተማማኝ ሆኖ ባለማግኘቱ አማካሪዎች ቀጥሮ ሲሠራ ነበር ተብሏል፡፡

የአክሲዮን ሽያጩ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ብቻ እንዲወሰንና አፈጻጸሙን በተመለከተም ‹‹ቀድሞ የጠየቀ ቀድሞ ያገኛል›› በሚል አሠራር እንዲስተናገድ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት በተለይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ጨምሮ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ፍላጐትና ተነሳሽነት ቃል በመግባት፣ ከሚፈረመው የአንድ ቢሊዮን ብር ውስጥ 669 ሚሊዮን ብር ተፈርሟል፡፡

በአክሲዮን ኩባንያ ውስጥ ከተቱት የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከማናቸው ባንኮች በመቅደም 200 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን በመፈረምና 50 በመቶ የአክሲዮን ድርሻውን ወዲያውኑ በመክፈል፣ ለኢትዮጵያ ሪ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ምሥረታ ቀዳሚ ባንክ መሆን ችሏል ተብሏል፡፡ እንደ አደራጅ ኮሚቴው ሪፖርት ከሆነ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ አክሲዮን ኩባንያ ውስጥ ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ ግለሰብ ባለሙያዎች ቢካተቱ በዕውቀታቸው ኩባንያውን ከማገዝ በተጨማሪ በቦርድ አባልነት በመሳተፍ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በማመን ውሳኔ አሳልፏል፡፡ እነዚህም በኢንሹራንስ ሙያ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያላቸው በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ የሚሠሩ ግለሰቦች በአክሲዮን ባለቤትነት መሳተፍ እንደሚችሉና የሚመዘገቡበት የካፒታል መጠንም የእነሱን አቅም ያገናዘበ እንደሆነ መደረጉን አመልክቷል፡፡ እነዚህ ግለሰብ ባለሙያዎችም የአክሲዮን ባለቤትነት 10 አክሲዮኖች እንዲሆን በመወሰን በባለአክሲዮንነት እንዲመዘገቡ ፈቅዷል፡፡

በአገሪቱ ካሉት ወደ 20 የሚጠጉ ባንኮች ውስጥ አብዛኛዎቹ በጊዜ ባለመወሰናቸው ወይም ውሳኔያቸውን በጊዜው ባለማሳወቃቸው፣ በዚህ ኩባንያ አክሲዮን ባለቤትነት ለመሳተፍ አለመቻላቸው ቅር የሚያሰኝ ሁኔታ ሆኖ እንዳለፈ ግን አቶ ኪሮስ ገልጸዋል፡፡   

እንደ አደራጅ ኮሚቴው ሪፖርት በጣም ጥቂት ፈራሚ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በፊት ከተደረሰበት ስምምነት በተቃራኒ የተሟላ የአዋጭነት ጥናት ካልተሰጣቸው የአክሲዮን መዋጮ ክፍያ ላይ ለመወሰን እንደማይችሉና የክፍያ ጊዜው እንዲራዘምላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ሆኖም አደራጅ ኮሚቴው በወቅቱ ባደረገው ስብሰባ የሚመሠረተው ኩባንያ አዋጭነት ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ባጠናው ጥናት የተረጋገጠ በመሆኑ፣ አደራጅ ኮሚቴው ባፀደቀው ፕሮስፔክተስ አዋጭነቱ የተረጋገጠ በመሆኑ  በዚህ መነሻነት ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት መወሰኑን በመጥቀስ ጥያቄው ተቀባይነት እንደሌለው እንዳሳወቃቸው ታውቋል፡፡ ከዚህ ውሳኔው ጐን ለጐንም የክፍያ ግዴታቸው እስከተወሰነው ቀን ያልተወጡ ፈራሚዎች እ.ኤ.አ. እስከ ሴፕቴምበር 30 ቀን 2015 ድረስ የሚፈለግባቸውን ክፍያ እንዲከፍሉ፣ ይህ ካልሆነ ግን ባልተከፈለባቸው የተፈረሙ አክሲዮኖች ላይ ምንም መብት እንደማይኖራቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያና ቀጠሮ በመስጠት ፈራሚዎች ግዴታቸውን እንዲወጡ ሊደረግ መቻሉንም ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ከ20ዎቹ ባንኮች በአክሲዮን ኩባንያ ውስጥ የተካተቱት ሰባቱ ባንኮች ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከኩባንያው የተፈረመ ካፒታል ውስጥ 669 ሚሊዮን ብሩ በ17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተፈረመ ሲሆን፣ 307.6 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ ከሰባት ባንኮች የተገኘ ነው፡፡ ቀሪው 22.4 ሚሊዮን ብር ደግሞ 81 ባለሙያዎችና ግለሰቦች የፈረሙት የአክሲዮን ግዥ ነው ተብሏል፡፡  

አደራጅ ኮሚቴው በተፈረሙ አክሲዮኖች ክፍያ ላይ የገጠመውን ችግር ለመወጣት ሲችል ሳይፈረሙ የቀሩት በተነጻጻሪት ጥቂት የሚባሉ አክሲዮኖች ሽያጭ በተመለከተ መጠነኛ ችግር አስተናግዷል ተብሏል፡፡ በወቅቱ ሳይሸጡ ቀርተው የነበሩትን ከ120,000 የማይበልጡ አክሲዮኖች ለባንክ ኢንዱስትሪው ለመሸጥ የተደረገው ጥረት በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት በታሰበው ጥናት ለማከናወን ባለመቻሉ፣ የተወሰነ የጊዜ መጓተት አስከትሎ እንደነበር የአደራጅ ኮሚቴው ሪፖርት አመልክቷል፡፡

እንደ አደራጁ ኮሚቴው ሪፖርት የምሥረታ ሒደት መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ካልተጠበቀ አቅጣጫና ባልተጠበቀ ሁኔታዎች ፈተናዎች እየተጋረጡበትና እነዚህን ፈተናዎች በሥራ አስፈጻሚና በአደራጅ ኮሚቴው ትዕግስት የተሞላበት አካሄድ ከሚፈለገው ግብ ለመድረስ ተችሏል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ የገጠመው አንዱ ትልቅ ችግር ጥናቱን በሚፈለገው ሁኔታና ደረጃ ለማጥናት የሚያስፈልግ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው መረጃ የሚገባና በሚፈለገው ሁኔታ ተደራጅቶ ለማግኘት አለመቻሉ ነበር፡፡ የመረጃው ባለቤት ኢንዱስትሪው ቢሆንም፣ ለጥናቱ የሚያስፈልገው መረጃ በከፊልም ቢሆን ለማግኘት የተቻለው ግን በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ከስድስት የማይበልጡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሰጡት መረጃ ነው፡፡ ይህንን የቆየ የኢንዱስትሪው ችግር የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት መንቀሳቀስ እንዳለበት የሚያስገነዝብ መሆኑን አቶ ኪሮስ ገልጸዋል፡፡

ብዙ ድካም ቢኖረውም ኩባንያው የተቋቋመ በመሆኑ፣ በቅርቡ ፍቃድ አውጥቶ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኩባንያውን ምሥረታ በሚመለከት በተሰጠው መግለጫም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና ግዥን ከአገር ውስጥ እንዲገዙ በማድረግ ለጠለፋ ዋስትና የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ያስቀራል፡፡ ለሌሎች አገሮች ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሪ መገኛ ይሆናል ተብሏል፡፡ ይህ ለኢንዱስትሪው ትልቅ ድል መሆኑንም አደራጅ ኮሚቴው ገልጿል፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐንም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ የጠለፋ ኩባንያ እንዲገለገሉ የሚያስገድድ ሕግ ይወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች