Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​ናሽናል ሲሚንቶ ከግብፅ ኩባንያ ጋር አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት የወረረ አረም ወደ ኃይል ምንጭነት ሊቀይር ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ከግብፅ የደረቅ ቆሻሻ ማቀነባበሪያና መልሶ ጥቅም ላይ መዋያ ኩባንያ ጋር በጋራ በሚመሠርቱት ኩባንያ አማካይነት፣ በአፋር ክልል ከአንድ ሚሊዮን ሔክታር በላይ የወረረውን ‘ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ’ የሚባለውን መጤ አረም ወደ ኃይል ምንጭነት ለመቀየር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ፡፡

ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር በእህት ኩባንያው ኢስት አፍሪካ ማይኒንግ በኩል የሚያለማው ባዮማስ የኃይል ምንጭ፣ የአገሪቱ ሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች እየተጠቀሙበት የሚገኘውን የከሰል ድንጋይ ከ40 እስከ 60 ከመቶ ይተካል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህንን ለሪፖርተር የገለጹት፣ ሰሞኑን በግብፅ ሻርም አል ሼክ ከተማ በተካሄደው ከፍተኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ስምምነቱን የተፈራረሙት የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ኤክዘኪዩቲቭ ዳይሬክተር ኢንጂነር ባሱ አሰፋ ናቸው፡፡

ኢንጂነር ባሱ ከጥቂት ቀናት በፊት በግብፅ ‹‹አፍሪካ 2016፡ ቢዝነስ ለአፍሪካ፣ ለግብፅና ለመላው ዓለም›› በሚል ርዕስ በተካሄደው ጉባዔ ወቅት፣ ኢጂፕሺያን ካምፓኒ ፎር ሶሊድ ዌስት ሪሳይክሊንግ (ኢካሩ) ኩባንያ ኃላፊ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡

በሁለቱ ኩባንያዎች ስምምነት መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ ከባዮማስ ለሚቀነባበረውና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የኃይል ምንጭ ለሚሆነው ግብዓት፣ ኢካሩ ቴክኖሎጂውንና የአስተዳደር ክህሎቱን ያቀርባል፡፡ ናሽናል ሲሚንቶ በበኩሉ አረም የወረረውን መሬትና ሌሎችም ግብዓቶችን በማቅረብ፣ በጋራ ባለቤትነት የሚመሩትን አዲስ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ እንደሚመሠርቱ ኢንጂነር ባሱ አብራርተዋል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት አርባ በመቶ የሚሆነውን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የኃይል ፍላጎት ያለምንም ተጨማሪ ማስተካከያ በነበረው የኃይል አጠቃቀም መሠረት የሚጠቀሙበት አሠራር ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ መጠነኛ ማሻሻያዎችን በኃይል መመገቢያ ሥርዓቶቹ ላይ በማካሄድ በባዮማስ የሚመነጨው ኃይል እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን የከሰል ድንጋይ ኃይል መተካት እንደሚቻል ኢንጂነር ባሱ  ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ስለሚመሠረተው ኩባንያ አወቃቀርም ሆነ ሁለቱ ኩባንያዎች ስለሚኖራቸው የባለቤትነት ድርሻና ሚና ላይ ወደፊት ማብራሪያ እንደሚሰጡበት፣ በመሠረተ ሐሳቡ ላይ ስምምነት ማድረጋቸውን የኢካሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሒሻም ሸሪፍ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በኢንጂነር ባሱ ገለጻ መሠረት የባዮማስ ቴክኖሎጂው ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከሚያተርፈው ወጪና ከሚያበረክተው ዝቅተኛ የአየር ብክለት በተጓዳኝ፣ እጅግ አደገኛ የሆነውንና ለበርካታ ዓመታት የአፋርን አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት የወረረውን አረም በማረስና መሬቱን ነፃ በማውጣት ትልቅ ጥቅም የሚያስገኝ ፕሮጀክት ነው፡፡

ከፕሮሶፒስ አረም ባሻገር ከሌሎችም የግብርና ተረፈ ምርቶች የባዮማስ ኢነርጂ ማምረትም እንደሚቻል ያብራሩት ኢንጂነር ባሱ፣ የሰሊጥ ገለባን ጨምሮ ታሳቢ የሚደረጉ ሌሎችም ተረፈ ምርቶችን አመላክተዋል፡፡ ሒሻም ሸሪፍ በበኩላቸው እንደ መሰቦ ሲሚንቶ ያሉ ፋብሪካዎች በዓመት ከ100 እስከ 150 ሺህ ሜትሪክ ቶን ከባዮማስ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ይፈልጋሉ፡፡

በተያያዘ ዜና መሰቦ ሲሚንቶ ከኢካሩ ጋር የባዮማስ ኢነርጂ እንዲቀርብለት የአምስት ዓመት ስምምነት በመፈራረም ለመነሻው አሥር ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን ሒሻም ሸሪፍ ገልጸዋል፡፡ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የሚያመርተው መሰቦ ሲሚንቶ፣ ከሰሊጥ ተረፈ ምርት የሚመነጭ የባዮማስ ኃይል እንዲቀርብለት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች