Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የጂቡቲ መንግሥት 900 ሚሊዮን ዶላር ያወጣባቸውን አራት ወደቦች ዘንድሮ ሥራ እንደሚያስጀምር ይፋ አደረገ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የጂቡቲ መንግሥት ላለፉት ዓመታት ሲያስገነባቸው የነበሩትን አራት ወደቦች በስድስት ወራት ውስጥ ሥራ ለማስጀመር መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡ ለወደቦቹ ግንባታም 900 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን ይፋ አድርጓል፡፡

  የጂቡቲ ወደብ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቡባካር ሓዲ በቅርቡ በግብፅ የተካሄደው ጉባዔ በተካፈሉበት ወቅት ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ የጂቡቲ ወደብ አስተዳደር አራት ወደቦችን ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ለወደቦቹ ግንባታም 900 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባሉ የተባሉት ወደቦች ታጁራ፣ ዶራሌህ፣ ደመርጆግና ጉበት የተባሉት ናቸው፡፡ ታጁራ ወደብ በአብዛኛው የወጪና ገቢ ማዕድን ምርቶችን የሚያስተናግድ ሲሆን፣ በአብዛኛው የፖታሽ ማዕድን ይስተናገድበታል ተብሏል፡፡ የጉበት ወደብ የጨው ምርት ለማስተናገድ የተገነባ መሆኑን አቡባካር ሓዲ ተናግረዋል፡፡ ደመርጆግ ወደብ ለቁም እንስሳት ማስተናገጃነት የሚያገለግል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  በሌላ በኩል የጂቡቲ ወደብ አስተዳደር በወደብ የዕቃ ማንሳት ሒደት፣ በሰነድና በዕቃ አላላክ ሥርዓቶች ላይ አዲስ የዲጂታል ሥርዓት መተግበር መጀመሩን በማስመልከት የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ አዲሱ የዲጂታል ሥርዓት የወረቀት ሥራን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ያሉት የጂቡቲ ወደብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ በዚህ ሥርዓት አማካይነት ላኪዎችና አስመጪዎች ካሉበት ቦታ ሆነው ጊዜ ሳይገድባቸው የዕቃዎቻቸውን እንቅስቃሴ መከታተል ይችላሉ ብለዋል፡፡

  ይሁንና የጂቡቲ ወደብ ያመጣው አዲስ አሠራር በኢትዮጵያውያን አስመጪዎችና ላኪዎች ዘንድ ሲነቀፍ ቆይቷል፡፡ አብዛኞቹ ላኪዎችና አስመጪዎች ወደቡ ያመጣው አሠራር ተጨማሪ ዋጋ እንደሚያስወጣ፣ ለአብነትም በኮንቴይነር ከ30 ዶላር በላይ የሚከፈልበት አሠራር መሆኑን በመግለጽ ሲተቹ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካንም በጉዳዩ ላይ ለመምከር ደጋግመው ወደ ጂቡቲ ማቅናታቸው ተዘግቧል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሓዲ ግን አስተባብለዋል፡፡

  ከዚህ ይልቅ ዕቃ አስተላላፊዎች ከዚህ በፊት ይከፍሉት የነበረው ታሪፍ ላይ ቅናሽ መደረጉን ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በኮንቴይነር እስከ 200 ዶላር ይከፈል የነበረው አሁን ወደ 60 ዶላር ዝቅ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ እንዲህ ያሉትን ማስተካከያዎች ለማድረግና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ለመምከር ከኢትዮጵያና ከጂቡቲ ወገን የተውጣጡ ባለሥልጣናት በየሁለት ወራት እንደሚገናኙም አስረድተዋል፡፡

  ከዚህ በተጓዳኝ በቅርቡ ሁለት የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮች ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ ለመዘርጋት ስምምነት ላይ መድረሱ አዲስ ክስተት መሆኑን ሓዲ አብራርተዋል፡፡ አንደኛው የነዳጅ መስመር ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያገለግል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የተጣራ ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ይውላል፡፡ የነዳጅ መስመሮቹን ለመገንባት የአሜሪካ ብላክ ራይኖ እንደሚሳተፍ ይታወቃል፡፡

  በተጨማሪ በባቡር መስመር፣ በውኃና በመንገድ መሠረተ ልማቶች ሁለቱ አገሮች መተሳሰራቸውን ያስታወሱት ሓዲ፣ በጂቡቲ አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ የሚዘረጋውና መነሻው ከጃፓን የሆነው የባህር ውስጥ የቴሌኮም ኬብልም ኢትዮጵያን ከተቀረው ዓለም ለማገናኘት ጂቡቲን መሸጋገሪያው ያደርጋል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ለጂቡቲ ያበረከተችው የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክትም ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል፡፡ 

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች